ስሕተቴ ሊቃውንቱን ከድንጋይ ራሶች ጋር ለማስተዋወቅ መሞከሬ ነው ( ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

ብልግና ከደንቆሮነት ደንቆሮነት ከብልግና ይወለዳል፤ አነዚህ ሰሞኑን የሚንጫጩት ዱሮ አሳዳጊ የበደላቸው ሲባሉ የነበሩ ዛሬ ግን አሳዳጊያቸውን የበደሉ በማያውቁት ነገር ሁሉ ከልክ ያለፈ ኩራት የሚሰማቸው ናቸው፤ እውቀት በየመንገዱ ወድቆ የሚለቃቀም ነገር ይመስላቸዋል፤ እውነት በጫጫታና በማደናበር የሚተከል ይመስላቸዋል፤

እንደዚህ ዓይነቶቹን አንድ ጊዜ አንድ መምህር በቲቪ ሲናገር ፊደላውያን ሲላቸው ሰምቻለሁ፤ ፊደልን በመከራ ተምረው ትምህርት የሚባል ነገር የጨረሱ የሚመስላቸው ናቸው፤ ያሳዝናሉ፤ የወደፊትዋ ኢትዮጵያ ይበልጥ ታሳዝናለች፤ ሆኖም በነዚህ ሰዎች ተስፋ አልቆርጥም! የእነሱው ዓይነት ሰዎች ወይ በገንዘብ፣ ወይ በዱላ ያስተምሯቸዋል፤ ትምህርት የሚገባቸው በነዚያ መንገዶች ብቻ ነው! ወያኔ ሲዘለዝላቸው መቼ ይናገራሉ፤ ምን አፍ አላቸው!
ለእውቀትና ለእውነት ደንታ የሌላቸው ሰዎች መሆናቸውን፣ ሌላው ቀርቶ የተጻፈውን እንኳን በትክክል ሳያነቡና ሳይገባቸው እንደየበር ላይ ውሻ የሚጮሁ መሆናቸውን ለማሳየት ሁለት ማስረጃዎችን አቀርባለሁ፤ አንደኛ አማራ የለም አላልሁም የትም ቦታ አላልሁም፤ ያልሁት አማራ የሚባል ጎሣ የለም ነው፤ በዚህ ትርጉሙ ድርጅቶች ተቋቁመው ሲፈልጉት ሁለት ዓመታቸው ነው፤ ገና አላገኙትም፤ አማራ የሚለውን ቃልም ሆነ ጎሣ የሚለውን ቃል በትክክል የማያውቁት ፊደላውያን ጩኸታቸው የብዙ ሰዎችን ጆሮ ስለጎዳ ለማብራራት ወሰንሁ፤ የኔ የግል አስተያየት እንዳልሆነም ለማሳየት ታላላቅ ሊቃውንትን በአስረጂነት ደርድሬ ነበር፤ ስሕተቴ ሊቃውንቱን ከድንጋይ ራሶች ጋር ለማስተዋወቅ መሞከሬ ነው፤ አይለምደኝም፤ የለመዳችኋቸው እንደለመዳችሁት ያስተምሯችኋል፡፡
ሁለተኛ፣ አማራ ለሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ለመስጠት አልሞከርሁም፤ ግን ሊቃውንቱ ከጻፉት ውስጥ ይነበብ ነበር፤ ከድንጋይ ራሶቹ አንድም የተጠቀሱትን አንብቦ የተረዳ የለም፤ ያሳዝናል፤ የአማራን ትክክለኛ ትርጉም ለመቀስቀስ የዞረባቸው የወያኔ ከድሬዎች ሥራ የጀመሩ ይመስላል፤ እስላም ጠቀላይ ሚኒስትር ሊሆን ነው እየተባለ ይወራል፤ ይኸ ወሬ አማራን ሊቀሰቅስ የሚችለው እስላም አማራ ሳይባል፣ አማራ ጎሣ ሳይባል ነበር!

ዛሬ ልወቅስ ነው። (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ዛሬ ልወቅስ ነው። ራሴን ጨምሬ በጽሁፍ ጅራፍ ልጋረፍ ነው። በእውነት ይህን ጽሁፍ ስሞነጫጭር ውስጤ በእልህና ቁጭት ድብን እያለብኝ ነው። በዚህም አሰብኩት። ወደዚህም ወሰድኩት። አገለባብጬ ተረጎምኩት። ዝምታችን ከፍርሃት በቀር ምክንያታዊ አልሆንልህ አለኝ። መቼም የትግራዩ አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የሞራል ልኬታችን ፈሩን ስቷል። የህሊና ፍርዳችን ተዛብቷል፡፡ ሰው የመሆን ሚዛናችን ጎድሏል። አገዛዙ ይዞብን የመጣው እሴት አልባ፡ ራዕይ የለሽ፡ ክብረ ነክ ወረርሽኝ ውስጣችንን ገዝግዞ፡ እንደምስጥ ስጋችንን በልቶ፡ ዝም ብለን የምንከላወስ፡ በልቶ ማደር፡ ጠጥቶ መነሳት መኖር የሚመስለን ሆነን ቀርተናል። ስንቱን በጎነታችንን፡ የሞራል ልዕልናችንን አራግፈን ጥለን ፡ በፍርሃት ቆፈን በተቀፈደደ፡ በእንጭፍጫፊ ሰበብና ምክንያቶች በተለበጠ፡ ኢትዮጵያዊ ክብርና ሞገሱን በተገፈፈ ማንነት ደረታችንን ነፍተን፡ ልክ ነን ብለን ልክ አጥተን የምንኖር ዜጎች ሆነናል።

አዎን! ለሃይማኖቱ ቀናዒ፡ ለእምነቱ ክብር አንገቱን ለሰይፍ ከመስጠት ወደኋላ አይልም በሚባልለት ኢትዮጵያዊ አፈር ላይ በዚህ ዘመን የሃይማኖት አባቶች ተዘቅዝቀው አርባ ይገረፋሉ። የነጭ ወራሪ ባንዳ ሶላቶ ባህር ተሻግሮ ሊወረን በመጣ ጊዜ ታቦት ተሸክመው፡ በማርያም ምለው ዘምተው፡ በጊዮርጊስ ቀን ድል አድርገው ለመላው ጥቁር ህዝብ የነጻነት አክሊል ያጎናጸፉ ኢትዮጵያውያን በበቀሉባት ምድር ላይ ዘንድሮ መነኮሳት፡ ወፌ ላላ እየተገረፉ፡ መሬት ለመሬት እየተጎተቱ፡ ሰውነታቸው ደም እስኪያዥ በኤሌክትሪክ ሽቦ እየተጠበሱ፡ ታላቁን ስቃይና ሰቆቃ ይጋታሉ። ለሀገር ነጻነት ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው፡ መራሯን ሞት በአደባባይ ተጎንጭተው ሃይማኖቷንም፡ ሀገራቸውንም አስከብረው፡ በክብር የተሰዉትን የታላቁን ፓትርያርክ አቡነ ጴጥሮስን አጽም በተሸከመችዋ የአሁኗ ኢትዮጵያ መስቀልና መጽሀፍ ቅዱስ ብቻ ይዘው ዓለምን ተጠይፈው ገዳም የገቡ መናኞች የክህነት ልብሳቸውን አውልቁ ተብለው ግፍ ይፈጸምባቸዋል።

ይሄ ሁሉ ጉድ ይሰማል። ድብቅ አይደለም። መሀል ኢትዮጵያ፡ ከአዲስ አበባ እምብርት እየተፈጸመ ያለ ሰቆቃ ነው። ኸረ ለመሆኑ የታላቁ መንፈሳዊ አባት
ልጆች ይህን መከራ አልሰሙም? እነዚያ ለእምነታቸው ክብር እስከሞት ዋጋ የሚከፍሉ ናቸው የሚባልላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ከማዕከላዊና ቂሊንጦ በመናኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ስቃይ እንዴት በዝምታ ተመለከቱት? ምን ነካቸው? ከነክህነት ልብሳቸው እጆቻቸው በብረት ካቴና ተቆላልፎ በአጋዚ ቅልብ ወታደሮች ተከበው በአደባባይ የሚታዩ የመንፈስ አባቶቻቸው ሁኔታ ምን ስሜት ሰጣቸው? በእውነት የኢትዮጵያ የተዋህዶ ልጆች ከየት ነው ያላችሁት? እነዚህ የዋልድባ መነኮሳት ታላቅ ግፍ እየተፈጸመባቸው እንዴት አስቻላችሁ? እንዴትስ እንቅልፍ ይወስዳችኋል? የእምነት ትርጉሙ ምንድን ነው? መንፈሳዊ ህይወት ሲባል እንዲህ ነውን? ግፍ እያዩ ዝም። አባቶች ሲዋረዱ ጸጥ። ቋርፍ በልተው የሚኖሩ፡ ስጋቸውን ለመንፈሳዊ ዓላማ ሲሉ ያደከሙ መናኞች ተዝቅዝቀው ሲገረፉ እንዳላየ፡ እንዳልሰማ ሆኖ ማለፍ።

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፈተናዋ በዝቷል። የቤተመንግስት አጋንንት ከቧታል። በቅጥሯ የተሾሙት አባትና በየሀገረ ስብከቱ የተሰገሰጉት የትግራይ ገዢ ቡድን አባላት ቤተክርስቲያኒቱን አፍነው ይዘዋል። ለስለላ ብለው ገብተው ቆብ ደፍተው በዚያው እስከ ጵጵስና የደረሱ የትግራይ ገዡ ቡድን አባላት የአባይ ጸሀዬንና ስብሃት ነጋን ቃል እንጂ የመጽሀፍ ቅዱስን መንፈሳዊ ህግ የሚያከብሩ እንዳልሆነ ይታወቃል። ይህ በመሆኑም ከቤተክህነት የሚጠበቅ አንዳች ተስፋ የለም። በጉልበት የተሾሙት ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ የዋልድባ አባቶች መከራና ስቃይ ሲደርስባቸው፡ ቤተክርስቲያኒቱን የሚያዋርድ ተግባር ሲፈጸምባቸው፡ አንዲትም ቃል ሳይተነፍሱ ስልጣን አልባው ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ሲለቅ ቤተመንግስት ድረስ ዘልቀው ውዳሴና ቡራኬ የሚያቀርቡ፡ ከንቱ አባት በመሆናቸው ከእሳቸውም የሚጠበቅ ነገር የለም። ምዕመኑ ግን ምን ነካው? ከዚህ ልቆ የሚያስፈራ ምን አለ?

ማህበረ ቅዱሳን የት ነው ያለው? የቤተክርስቲያኒቱን ገዳማትና ነዋየ ቅድሳት ከትውልድ ትወልድ ተጠብቆ እንዲቆይ እስከ ገጠር ቀበሌ ድረስ የዘለቀ መጠነ ሰፊ ተግባራትን በመከወን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ዘብ ጠባቂ እንደሆነ የሚነገርለት ማህበረ ቅዱሳን የእነዚህን መናኞች ግፍና ስቃይ አልሰማ ይሆን? ወይስ ለመናኞች፡ ለመነኮሳት ደህንነትና ክብር እንዲጮህ መተዳደሪያ ደንቡ አይፈቅድለትም? ቢያንስ ክሳቸው በአግባቡ እንዲታይ፡ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ለመጠየቅ የሚያስችል ወኔ ማህበረ ቅዱሳን ዘንድ እንዴት ሊጠፋ ቻለ? ገዳማት ያለመናኞች ምንድን ናቸው? ለገዳማት ተጨንቆ ለመንፈሳዊ አባቶች ግድ ማጣት ምን የሚሉት መንፈሳዊ መስመር ነው?

በእውነቱ እነዚህ አባቶች በማዕከላዊና ቂሊንጦ የደረሰባቸው ግፍ ለሃይማኖታቸው እስከመጨረሻው ዋጋ ይከፍላሉ በሚባሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በሆኑ ኢትዮጵያውያን መኖሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ መፈጸሙ ያስደነግጣል። አንድም ቀን በዚያ የግዞት ስፍራ ማደር አልነበረባቸውም። እንኳን ተዘቅዝቀው ሊገረፉ፡ ሰውነታቸው ላይ አንዲትም ዱላ ማረፍ አልነበረባትም። ምን ጉድ እንደመጣብን አላውቅም። እንዲህ ዓይነት ሰቆቃ እየተፈጸመ ዝምታችን ግራ ያጋባል። ለምን አባቶቻችን ታሰሩ ብሎ መጠየቅ እንዴት አልተቻለም? ለምን እንዲህ ክብራቸው ይነካል የሚል ድምጽ እንዴት ለጆሮአችን ይናፍቀናል? አባቶቹ እኮ አይደሉም የተዋረዱት። ማዕከላዊ ተዘቅዝቅው የተገረፉት መናኞቹ አይደሉም። እጆቻቸው በካቴና የተቆላለፈባቸው የዋልድባ መነኮሳት እኮ አይደሉም። አዎን! የተዋረደችው ቤተክርስቲያኒቱ ናት። ወፌ ላላ የተገረፈችው የአቡነ ጴጥሮስ ቅጥር የሆነችው የኦርቶዶክስ ቤት ናት። እጆቿ የታሰሩት እናት ቤተክርስቲያናችን ናት። ይህ ካላመመን፡ ይህ ካልቆጨን፡ ይህ ካልተሰማን በእውነት እኛ የተዋህዶ ልጆች ነንን?

ድምጽ ይሰማል። የአባቶች የሲቃ ጩኸት።አብያተ ክርስቲያናት በየጸሎታቸው ሊያነችሷቸው ይገባል። ምዕመናን ዘውትር ከጸሎት ባሽገር የእምነት አባቶቻቸው ላይ ጫና በመፈጠር ስለተዋረደችው ቤተክርስቲያን ሲሉ ከፍርሃት ቆፈን ተላቀው ተቃውሞአቸውን ሊያሰሙ ግድ ይላል። እያሪኮም በጩኸት ፈርሳለች። እንጩህ! የግፈኞች ግምብ መፈረሱ አይቀርም። የቤተመንግስት አጋንንት ይለቀን ዘንድ በአንድነት እንጩህ። ልቦና ይስጠን።

ቄሮ ቃሉን አያጥፍም። (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የነዳጅ አቅርቦት ማስተጓጎል ዘመቻ

ቄሮ ቃሉን አያጥፍም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በቄሮ ተጠርቶ ያልተሳካ የአድማም ሆነ የተቃውሞ ሰልፍ ከነበረ አላስታውስም። ከሁሉ የሚደንቀኝ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት፡ የኦሮሚያን ክልል ከዳር እስከዳር ባናወጠው ህዝባዊ እምቢተኝነት በቄሮዎች እጅ ህይወቱን ያጣ ሰላማዊ ሰው አለመኖሩ ነው። የሚጠራው አድማ፡ የሚካሄደው ዘመቻ፡ የሚወሰደው እርምጃ የአገዛዙን የማፈናና የመግደል አቅም ከማላሸቅ ያለፈ የትኛውንም የህብረተሰብ ክፍል ለጉዳት የዳረገበት አጋጣሚ አልተፈጠረም። በእውነት የቄሮዎች ትግል እነመሀተማ ጋንዲ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ዘመን እንዲጨልምና ከነግሳንግሱ ከምድር ገጽ እንዲጠፋ ያደረጉበትን አስደናቂ የእምቢተኝነት ትግል የሚያስታውስ ነው።

በእርግጥ ቄሮዎች ዛሬ ላይ ላቀጣጠሉት እምቢተኝነት እርሾው ቀደም ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑን እዚህ ላይ መጥቀስ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይ አገዛዝ ቤተመንግስት ከገባ ጀምሮ ትግል ነበር። በተለያዩ አካላት ሲደረግ የነበረው እልህ አስጨራሽ የነጻነት ተጋድሎ በቅብብሎሽ እዚህ ዘመን ላይ ደርሷል። በተናጠልና በጋር የተደረጉ ንቅናቄዎች ያበሰሉት የኢትዮጵያውያን ትግል ለቄሮዎች መንገዱን በመጥረግ ረገድ አስተዋጽኦው በታሪክ በደማቁ የሚመዘገብ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል ምንጊዜም የሚታወስ፡ በሰላማዊ እምቢተኝነት የኢትዮጵያውያንን የነጻነት ትግል አንድ ምዕራፍ ወደ ፊት የወሰደ ታላቅ ተጋድሎ መሆኑን መጠቀስ ግድ ይላል። እናም ቄሮዎች እንደዱላ ቅብብል የተጀመረውን የነጻነት ተጋድሎ አድምቀው ተያይዘውታል።

የቄሮዎች ትግል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መስመሩን በትክክል ይዞ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከሚጋብዝበት መድረክ ላይ ወጥቷል። ክልላዊ ስሜት ያጠላበት፡ ለሌላው የሚጎረብጥ የሚመስለው፡ በመልዕክቱና በእንቅስቃሴው ሁሉን አሳታፊ ያልነበረው የቄሮዎች ትግል ወሳኝ ለውጥ አድርጓል። አዳማ፡ ጂማ፡ አምቦ በቄሮዎች የተላለፉት የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች የሌላውን ኢትዮጵያዊ ልብ የሚከፍቱ፡ ለአብሮነት ትግል መደላድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው በቄሮዎች ትግል ብዥታ ውስጥ ለነበረ፡ በጥርጣሬ የዳር ተመልካች ሆኖ ለሰነበተ ምላሽ የሰጠ የትግል አቅጣጫን ይዟል። እንግዲህ ሜዳውም ፈረሱም አለ። አብሮ ከመታገል ውጪ ምርጫ የለም። ለጋራ ድል በእኩል መስዋዕትነት መክፈሉ ለቀጣዩ አብሮነታችንም ዋስትናው እንደብረት የጠነከረ ይሆናል።

ለነገ የተጠራው ዘመቻ በቄሮውች እስከዛሬ ከተደረጉት አድማዎች የበለጠ ውጤታማና አገዛዙን ሽባ በማድረግ ረገድ ክፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር እንደሆነ ይሰማኛል። የቄሮዎች ትግል እያደገ፡ እየተመነደገ፡ በዕውቀትና ብልሃት እየተመራ ለመሆኑ የነገው ዘመቻ ትልቅ ማሳያ ነው። ነዳጅ ላይ የሚጠራ አድማ ውጤቱ የአገዛዙን የስልጣን ወንበር እስከመፈንቀል የሚደርስ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ነዳጅ ያልገባበት የህይወታችን እንቅስቃሴ የለም። ነዳጅ ደምስር ነው። የአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት፡ የሁለንተናዊ መዘውር አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። እናም የነገው ዘመቻ ሀገሪቱን ቀጥ አድርጎ፡ ከየትኛውም እንቅስቃሴ ገድቦ፡ የሚያስቀር እንደሚሆን ይታመናል። በተለይ ለአገዛዙ ብርቱ ፈተና ከመሆን ባለፈ ሀገሪቱን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አቅም የሚያሳጣው፡ ከቆየና ከጠነከረ ደግሞ እስከወዲያኛው የሚያሰናብተው ስለመሆኑ ከቶም አልጠራጠርም።

ነገ ተጀምሮ ለሳምንት የሚዘልቀውን የነዳጅ ዝውውርን የማስተጓጎል ዘመቻ እንዲሳካ የቄሮዎች ጥረትና መስዋዕትነት ብቻውን በቂ አይደለም። ውጤታማም አይሆንም። ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፡ ከከቤንሻንጉል ጉምዝ እስከ ሀረር የተዘረጋ፡ ሁሉን ያሳተፈ፡ በሁሉም ክልል ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። የነዳጅ አቅርቦቱ በአብዛኛው በሱዳን በኩል የሚገባ በመሆኑ ከመተማ ጀምሮ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ የነገውን ዘመቻ በባለቤትነት ሊመራው ይገባል። በመተማ መስመር ከዚህ በፊት ከ5በላይ የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪዎች እንደጧፍ የነደዱበትን አደጋ የጣሉት የሰሜኖቹ ፋኖዎች የነገውን ዘመቻ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚገድባቸው ነገር ይኖራል ብዬ አላምንም። ከመተማ ጎንደር፡ ከመተማ ሁመራ የሚወስዱትን መንገዶች ለነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ዝግ ማድረግ፡ ለባለንብረቶችም መልዕክት በማስተላለፍ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ከማስጠንቀቂያ ጋር ማሳወቅ ይገባል። ተደርጓልም ብዬ አምናለሁ።

የነገው ዘመቻ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በወደቀችው፡ ደም በጠማቸው የአጋዚ ወታደሮች በታፈነችው፡ የትግራይ አገዛዝን የዕልቂት አዋጅ ለማስፈጸም በተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት ማንቁርቷን በተያዘችው ኢትዮጵያችን የሚከናወን በመሆኑ መስዋዕትነቱ ከባድ ሊሆን ይችላል። ቄሮዎች ዘመቻውን በትንሽ መስዋዕትነት፡ በግዙፍ ስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዕቅድ እንዳላቸው ስለማምን በዚህ በኩል ብዙም ስጋት አይኖረኝም። በዚህ ላይ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ቢያንስ ንብረቶቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲሉ፡ ገፋ ካለም ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ለመደግፍ ብለው ተሽከርካሪዎቻቸውን ከስምሪት ውጭ ያደርጋሉ የሚል ተስፋም ውስጤ አለ።

ጥንቃቄም ያስፈልጋል። የትግራይ አገዛዝ ከቄሮዎች ጥሪ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ግን የእርስ በእርስ ግጭትንና ጥፋትን የሚጋብዝ መልዕክት አሰራጭቷል። በቄሮ ስም የተበተነው መልዕክት የነዳጅ ማደያዎችን በእሳት ማጋየት፡ በትግራይ ተወላጆች ንብረቶች ላይ ጥቃት መፈጸምና ሌሎች እርምጃዎች እንዲወሰዱ የሚጠይቅ ነው። ቄሮዎች እንዲህ ዓይነት ጥሪ አላደረጉም። እውነተኛው ጥሪ ግልጽና ጥርት ያለ ነው። የነዳጅ ተሽከርካሪዎች እንዳይዘዋወሩ ማድረግ ብቻ ነው። ወደ ሀገር ቤት የሚገቡና በውስጥም ነዳጅ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች ለአንድ ሳምንት ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነው እንዲቆሙ የተጠራ ዘመቻ ነው። ከዚህ የሚጨምርም የሚቀንስም ዓላማ የለውም።

ከደህንነት አከባቢ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም በአዲስ አበባና በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች በተለይ በነዳጅ ማደያ አከባቢዎች ፍንዳታ ለመፈጸም አገዛዙ በስውር ተዘጋጅቷል። ይህን ሴራ ማክሸፍ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው። አጥፍቶ ለመጥፋት ቆርጦ የተነሳው የትግራዩ አገዛዝ የቄሮውችን ትግል ጥላሸት ለመቀባትና የነገውን ዘመቻ በኢትዮጵያውያን ዕልቂት እንዲጠናቀቅ ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ ሊወስድ መሆኑ ሾልኮ የወጣ መረጃ ላይ ተመልክቷል። በመሆኑም ህዝባችን ይህን አውቆ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

ነገ ሁላችንም ቄሮዎች ነን!!!!!!

የበረከት የአትርሱኝ ተማጽኖ (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም)

የበረከት የአትርሱኝ ተማጽኖ

ሰሞኑን በረከት ስምዖን በኢቢሲ ብቅ ብሎ የአትርሱኝ ተማጽኖውን አቅርቧል። አምና በረከት ስምዖን ከአባይ ጸሃዬና አባዱላ ጋር የኢቢሲን ሰዓት ለአንድ ሳምንት ያክል ተቆጣጥሮት ነበር። ብዙም ሳይቆይ እሱና አባ ዱላ “ስራ ለቀናል” በማለት ትንሽ አቧራ አስነሱ። ኩርፊያቸው ሲያበቃ ደግሞ “ተመልሰናል” አሉ። የበረከትን የተለመደ የመልቀቅና የመመለስ ባህሪ የሚያውቁ የድርጅቱ አባላት “ በረከት ቢሸፍት ከጓሮ አያልፍም” እያሉ ተሳለቁበት። በረከትም ሃፍረቱን ውጦ ዝም አለ። አባዱላ፣ በረከትና አባይ ጸሃዬ ድርጅታቸውን ለቀው እንደገና የተመለሱ በመሆናቸው የሚመሳሰል ባህሪ አላቸው። ድርጅትን ለቆ መመለስ ደግሞ በወላዋይነት፣ ጽናት ማነስና ተስፋ ቆራጭነት ያስፈርጃል። የኢህአዴግ አባላት ሶስቱንም ሰዎች በዚህ መልኩ እንደሚያዩዋቸው ግልጽ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሶስቱም ራሳቸውን የፖለቲካ አዋቂ አድርገው ይመለከታሉ።

ትናንት በድርጅቱ ተስፋ ቆርጦ መልቀቁን ያስታወቀው በረከት፣ ዛሬ በቴሌቪዥን ቀርቦ ትንተና ልስጥ ቢል የሚሰማው የድርጅት አባል እንደማይኖር ያውቃል። በረከት በዚህ ወቅት ከቴሌቪዥን መራቁን አይፈልገውም ። በቀጥታ በቲቪ ቀርቦ ትንተና ልስጥ ቢል ደግሞ “አንተ ማን ስለሆንክ ነው ከሌሎች ተለይተህ ትንተና የምትሰጠው” የሚል ከራሱ አመራር ጥያቄ ይቀርብበታል። በተለይ ከህወሃት በኩል የሚመጣውን ትችት የሚችለው አይሆንም። ስለዚህ በረከት የዶ/ር አብይ ጉዳይ ወደ ኢቢሲ ለመቅረብ ብቸኛ መንገድ እንደሆነ አይቷል ። በረከት ዶ/ር አብይን ተችቶ በስሙ ጽሁፍ ቢጽፍ ህወሃቶች እንደሚደሰቱ ያውቃል፤ በጽሁፉ ላይ ስሙ መውጣቱም ጽሁፉ ትኩረት እንዲያገኝ ያደርገዋል። ነገር ግን የጽሁፉ ባለቤት “እኔ ነኝ” ብሎ በድፍረት ቢናገር ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ያላትመዋል። ስለዚህ በረከት ጽፎ በማስተባበል በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፎችን ይመታል፤ ኦህዴድን ሳያስከፋ፣ ህወሃትን አስደስቶ፣ ጸሁፉም ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎ፣ እሱም በቴሌቪዥን የሚፈልገውን ተናግሮ እና የውሸት ገጽታ ገንብቶ ተልዕኮውን ይፈጽማል። በረከት በዶ/ር አብይ ላይ ጽሁፍ ጽፎ በህወሃት ደህንነቶች በኩል እንዲሰራጭ ማድረጉን አልጠራጠርም። ወዲያውኑ በብአዴንና ኢህአዴግ ፌስቡክ ገጾች ላይ “ በረከት አልጻፈም” የሚል ማስተባበያ እንዲሰጥ ያስደረገውም እሱ ነው። በረከት ለፌስቡክ ጽሁፍ በፌስቡክ የሚሰጥ ማስተባበያ በቂ እንደሆነ ቢያውቅም፣ አላማው እሱ አልነበረምና፣ በማግስቱ በቴሌቪዥን ቀርቦ የሚፈልገውን ነገር ተናግሮ ፣ አሁንም ራሱን የህግና ፖለቲካ አዋቂ የድርጅቱ ጠቃሚ ሰው አድርጎ አሳይቶ፣ ለድርጅቱ አባላትም የአትርሱኝ ተማጽኖውን አቅርቦ ግቡን አሳክቷል።

በረከት የጠ/ሚኒስትር ምርጫ በሚስጢር ድምጽ አሰጣጥ እንደሚካሄድ የተናገረው ከራሱ ያመነጨውን ሳይሆን ከህወሃት የተሰጠውን ተልዕኮ ነው። እንደሚታወቀው ኢህአዴግን ለረጅም ጊዜ የመራው መለስ ዜናዊ አንድም ቀን በሚስጢር ድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት መመረጡን ለህዝብ ሲነገር አልሰማንም።ሃይለማርያምም መለስን ይተካል ተብሎ በበረከት የተነገረው የኢህአዴግ ምክር ቤት ውሳኔ ሳያሳልፍበት ነው። በየትኛው ጠ/ሚኒስትር ምርጫ ላይ ተግባራዊ የሆነውን ህግ ነው ዛሬ በረከት ህግ ብሎ የሚጠቅሰው? ጨዋታው ሌላ ነው። ስውሩ መንግስት የዶ/ር አብይን ወይም የእነ ለማን ቡድን ወደ ፊት መምጣት አይፈልገውም። ይህን በገሃድ መቃወም ደግሞ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በቀጥታ ያላትማል። ከህወሃት በስተቀር ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደኢህዴን ለጠ/ሚኒስትርነት እጩዎችን ያቀርባሉ። ሁሉም የምክር ቤት አባላት ለራሳቸው የድርጅት እጩ ድምጽ እንደሚሰጡ ይታወቃል። የመጨረሻው ወሳኝ ድምጽ እጩ ያላቀረበው የህወሃት ድምጽ ይሆናል። ህወሃት ደግሞ ለአንዱ በግላጭ ድምጽ ቢሰጥ ከሌላው ጋር ይላተማል። አብይን “ የትግሬ ጥላቻ አለበት” በሚል እንደማይደግፉት ወስነዋል ፤ በግላጭ “አንደግፍህም” ማለት ደግሞ ከኦሮሞ ጋር ያጋጨናል ብለው ይፈራሉ። ስለዚህ ይህን ወሳኝ ድምጻቸውን በሚስጢር መስጠት ይፈልጋሉ። የሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓቱን ደግሞ እነሱ ከሚናገሩት ገጽታውን ለመገንባት የጓጓውን በረከት ስምዖንን አቅርበው እንዲናገር ቢያደርጉት ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በቀጥታ ሳይላተሙ ግባቸውን ያሳካሉ። ይህ ሁሉ ጨዋታ የእነ ለማን ቡድን ወደ ማእከል እንደይመጣ ለመከላከል የሚደረግ ነው። በረከትም የሚፈልገውን “ ኢጎውን” አበጥሮ ያው የአጫዋችነትና የተጫዋችነት ሚናውን አስጠብቆ ይቆያል። አባ ዱላም ነገ የበረከትን መንገድ ተከትሎ በቴሌቪዝን ባይቀርብ ከምላሴ ጸጉር ይነቀል።

ኦህዴድ ብልጥ ከሆነ የጠ/ሚኒስትር ቦታ ካልተሰጠኝ በሚል ከስውሩ መንግስት ጋር መላተም ያለበት አይመስለኝም። በሶማሊ ክልል የደረሰበትን ጥቃት በብልጠት እንዳለፈው ሁሉ ይህንንም ወቅት በብልጠት ካላለፈው በስውሩ መንግስት የመመታቱ እድል ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ለኢትዮጵያ ህዝብ ግን ስውሩ መንግስት ተነቅሎ ይፋዊ መንግስት በህዝብ ምርጫ እስኪቆም ድረስ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል ብቸኛ አማራጩ ነው።

ከፀፀት ለመዳን ነገ ”አይሆንም“ ድምጽ መስጠት ( ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

ከፀፀት ለመዳን ነገ ”አይሆንም“ ድምጽ መስጠት

ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርላማ አባል መሆን እንደ አሁን ሰቆቃ የሆነበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም። የፓርላማ አባላት ድምጽ ሲሰጡ ”የመረጣቸውን ሕዝብ“ እና ህሊናቸውን አዳምጠው ሳይሆን “ጠርናፊያቸው” ባዘዘው መሠረት መሆኑ መቸም ቢሆን ምቾች የሚሰጥ ነገር ባይሆንም ነገ እንደምናየው አሸማቃቂ ጉዳይ አልነበረም። “በጠርናፊ ትዕዛዝ” ድምጽ መስጠት ነገ በዚህ ሰዓት በብዙዎች ህሊና ውስጥ የሚያደርሰውን መሸማቀቅ ያህል ያደርስ ነበር ብዬ አላስብም።

የነገው መሸማቀቅ ከእስከ ዛሬው ሁሉ ይለያል። ነገ ህግ ሆኖ እንዲያልፍ የይሁንታ ድምጽ የሚሰጡለት አዋጅ ሳሞራ የኑስንና ጌታቸው አሰፋን ከፓርላማው በላይ የሚያደርግ፤ የሳሞራና ጌታቸው ሎሌዎች በዜጎች ላይ ለሚያደርሱት ፍጅት ሽፋንና ከለላ የሚሰጥ ህግ መሆኑን ህሊናቸው ስለሚረዳ ድምጽ ሰጥተው ከአዳራሹ ሲወጡ የሚደርስባቸው ውስጣዊ መሸማቀቅ ይታየኛል። የፓርላማው አባላት ነገ የሚያፀድቁት ህግ አንድ ፋሽስታዊ ቡድን መላውን የመንግሥት መዋቅር እንዲቆጣጠር በድምጽ ብልጫ በይፋ የወሰኑበት ቀን ሆኖ ይመዘገባል። ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በመዋሉ ምክንያት ዜጎች እየተገደሉ ነው፤ ድጋፋቸውን ሰጥተው ካፀደቁበት ደቂቃ ጀምሮ በርካታ ዜጎች ይገደላሉ፣ ይገረፋሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ። ችግሮች ሳይፈቱ ግልጽ ሁከቶችን ብቻ በማስወገድ ወይን በማፈን የሚገኝ አሉታዊ ሰላም ዘላቂ እንዳልሆነ እንዲያው እጅግ አደገኛ መዘዝ እንዳለው ልቦናዎቻቸው ይነግሯቸዋል።

ለዚህ አዋጅ የድጋፍ ድምጽ መስጠት ከራስ አልፎ ለልጅ ልጆች የሚተርፍ ፀፀት ነው። ከዚህ ፀፀት መዳን የሚቻለው የሚያስከፍለው ዋጋ በጀግንነት ተቀብሎ ”አይሆንም“ የሚል ድምጽ መስጠት ነው። በነገው ዕለት የሚሰጥ የአንድ ሰው እንኳን “አይሆንም” ድምጽ ከፍተኛ ዋጋ አለው፤ ያ ሰው ከገዳዮቻችን አንዱ አይደለም።

ወደ ስራችን እንመለስ ( ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ወደ ስራችን እንመለስ

ጉዳዩ ከሚገባው በላይ መጦዙ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ደጋፊዎችና የፌስቡክ ሰራዊት ሰርግና ምላሽ የሆነላቸውን የሰሞኑን ፍጥጫ እናርግበውና ወደ ዋናው ስቱዲዮ እንመለስ። አንድን ጉዳይ ደጋግሞ ማኘክ ለውጥ አያመጣም። ከዚህ በላይ እንዲሄድ መፍቀድ የለብንም።

ትግል ከባድ ነገር ነው። ውስብስብ ነው። ማናችንም ገጻችንን ከፍተን ስሜታችንን እንደምንገልጸው አይነት ቀላል ነገር አይደለም። ውጣ ውረድ የበዛበት፡አባጣና ጎርባጣ የበረከተበት፡ ጠመዝማዛ መንገድ የሞላበት፡ መውደቅና መነሳት የማይጠፋው፡ ወዳጅ የሚንሸራተትበት፡ ጠላት የሚማረክበት፡ ስህተት የሚሰራበት፡ ስህተትን የሚተራረሙበት፡ ሰፊና ጥልቅ የህይወት መስክ ነው – ትግል። የተጀመረው ፍጻሜ ማግኘት አለበት። ትግሉ ከዳር መድረስ ግድ ይለዋል። ኢትዮጵያ ትጠብቀናለች። ጊዜ የለንም።

አራት ነገሮችን ላንሳ። የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሚመራው መንግስት የኮሚኒኬሽን ቀውስ ውስጥ መግባቱን አምኗል። መንግስት ውስጥ ያሉ አካላትና መዋቅሮች መግባባት እንዳልቻሉ ሰሞኑን የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ በይፋ ገልጸዋል። በክልልና ፌደራል መንግስት መሀል መግባባት የለም። ቋንቋው ተለያይቷል ነው የሚሉን ሰውዬው። ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው። አንድ ስርዓት እዚህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ ከገባ አደገኛ ነው። እርስ በእርሱ የመበላላት እድሉ ሰፊ ነው።

ሰዎቹ ለምን መግባባት አቃታቸው? መልሱ ቀላል ነው። የህዝብ ትግል ውጤት ነው። በስርዓቱ መሀል ሁለት አካላት መኖራቸውን ያመለክታል። የህዝብ ትግል ሙቀቱ ሲጨምር አሰላለፋቸውን ከህዝብ ጋር ያደረጉ ሰዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ያሳያል። እነኚህ ወገኖች ቋንቋቸውን ቀይረዋል። መረጃ ሲያቀብሉ አዛብተው ነው። የኮሚኒኬሽን ቀውስ መፍጠር ችለዋል። ይህ ለአንድ ስርዓት ፍጻሜ ሁነኛ ምልክት ነው። ይህ እንዳይቀለበስ ወደ ስራችን እንመለስ።

ሁለተኛው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር(ትህነግ) በወታደራዊ ሹመት ሰራዊቱን እያንበሸበሸ መሆኑ ነው። ባለፈው ዓርብ ካጠለቀለቀው የጄነራልነት ሹመት በተጨማሪ ለአብዛኛው የሰራዊቱ አባላት በየደረጃቸው ማዕረግ ሊሰጣቸው መሆኑ ተሰምቷል። በዚህኛው ዙር ማዕረግ የማያገኝ የሰራዊቱ ክፍል እንደሌለ ይነገራል። ገንዘብና ስልጣን የሌለው ባዶ ሹመት መሆኑ እርግጥ ነው። ጥያቄው ትህነግ አሁን የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት በማዕረግ ማጥለቅለቅ ለምን ፈለገ የሚለው ነው። መልሱ አጭር ነው። በሰራዊቱ ውስጥ ጫፍ የደረሰው ምሬትና ብሶት ነው። የህዝባችን ትግል ሰራዊቱ ውስጥ ግለት ፈጥሯል። ከላይ በአንድ ብሄር ተወላጆች የበላይነት የተያዘው የሰራዊቱ ክፍል ሲቀር ከመካከለኛው እስከ ታች ያለው ብዙሃኑ የሰራዊቱ አባላት ውስጥ መከፋቱ ከገደብ አልፏል።

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሚመራው አገዛዝ በህዝብ ተተፍቷል። በዙሪያ በጥቅም ከተሰባሰቡ ጥቂት አገልጋዮቹ በቀር ከዳር እስከዳር ተቃውሞ ተነስቶበታል። ህልውናው የቆመው በደህንነቱና መከላከያው ነው። መከላከያው ውስጥ የተፈጠረው የሰራዊቱ ምሬትና ብሶት በዚሁ ከቀጠለ ወደ ህዝብ የተነጣጠረው አፈሙዝ ወደ አገዛዙ መዞሩ አይቀርም። ይህ መሆኑ አገዛዙን ከነጥቁር ታሪኩ ከኢትዮጵያ ገጽ ላይ የሚፋቅበትን አጋጣሚ ይፈጠራል።

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የሰራዊቱ ብሶትና ምሬት እንዲዳፈን እየተሯሯጠ ነው። ሰራዊቱ አንድ ላይ ለብዙ ጊዜ እንዳይቆይ(ከቆየ የአመጽ ሴራ ይጎነጉናል ከሚል ፍራቻ) በየቀኑ የመበታተንና የማጓጓዝ ዘመቻ ላይ ተጠምዷል። ከዚህ በተጨማሪ ገንዘብና ስልጣን በሌለው ሹመትና ማዕረግ የሰራዊቱን አፍ ለማዘጋት በሰፊው መንቀሳቀስ ጀምሯል። ሰሞኑን የወታደራዊ ሹመቶች ዜና በሽ ይሆናል። በዘመቻ ማዓረግ ይሰጣል። ከንቱ ድካም ነው። ሰራዊቱ የደረሰበት የምሬት ደረጃ በውሸትና ባዶ ማዕረግ የሚዳፈን አይደለም። የህዝብ ትግል በሰራዊቱ ውስጥ የፈጠረው ግለት የሚበርድ አይሆንም። እናም ይህ እንዳይቀለበስ ወደ ስራችን እንመለስ።

ሶስተኛው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሚመራው አገዛዝ የተደቀነበት የውጭ ምንዛሪ ቀውስ ነው። ሀገሪቱ ቀጥ ብላ ቆማለች። ወደፊት መሄድ አልተቻለም። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ብቻውን የትህነግን አገዛዝ ወደ ውድቀት ሊወስደው እንደሚችል ምልክቶች እየታዩ ነው። ከአዲስ አበባ የሚወጡ መረጃዎ እንደሚያመለክቱት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ባንኮችን ጾም እያሳደራቸው ነው። ስራ የለም። ጠዋት በር ይከፈታል። ሲመሽ ይዘጋል። ምንም የለም። አገዛዙ ጭንቀት ሲይዘው የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ነገሮች ፍለጋ እየማሰነ ነው። የአሰሪና አገናኝ አዋጅ ላይ ጥሎ የነበረውን እገዳ ያነሳው ዶላር ፍለጋ ነው። ዕቃ ያለቀረጥ እንዲገባ የፈቀደውም የምንዛሪው እጥረት የፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ ነው። በየሀገራቱ ያሉ ኤምባሲዎች ከእንግዲህ ከአዲስ አበባ የሚላክ ደምወዝ አይኖራቸውም። እዚያው በተለያዩ መንገዶች ዶላር ፈልገው ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ውስጣዊ ሰርኩላር ማሰራጨቱ ይነገራል። የተበደረውን ገንዘብ የሚክፍለው በማጣት ከአበዳሪዎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል። በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው።

ይህ አንድም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የከፈቱት ዘመቻ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ ላይ እቀባ እንዲያደርጉ የተከፈተው ዘመቻ አንድ ወር ሆኖታል። ውጤት እያሳየ ነው። ከብሄራዊ ባንክ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ዘመቻው ከተከፈተ ወዲህ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ መጠን ቀንሷል። ይህም ስርዓቱን አስደንግጧል። እናም ይህ እንዳይቀለበስ ወደ ስራችን እንመለስ።

አራተኛው የአሜሪካን መንግስት ሰሞኑን ቀነ ገደብ አስቀምጦ ለትህነግ አገዛዝ ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያ ነው። ኤች አር 128 የተሰኘው ረቂቅ ህግ ለኮንግረስ ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ከጫፍ ደርሷል። ረቂቅ ህጉ ከጸደቀ ለትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አገዛዝ ትልቅ አደጋ ይሆናል። በተለይ የአገዛዙ ባለስልጣናት ላይ የሚጣለው ገደብ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ የሚደረግበት ነው። የትህነግ አገዛዝ ረቂቅ ህጉ ለኮንግረስ እንዳይቀርብ በብዙ ሚሊዮን ዶላር ሎቢስቶችን በመቅጠር የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ገብቷል። በአንጻሩ ኢትዮጵያውያንም ከምንግዜውም በላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ዘመቻውን አጠናክረው ገፍተውበታል።

ባለፈው ሀሙስ የአሜሪካን መንግስት ለትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አገዛዝ ማስጠንቀቂያ ልኳል። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ኢትዮጵያ ገብተው ያለምንም ገደብና ክልከላ በፈለጋቸው ቦታና ጊዜ ምርመራ እንዲያከናውኑ እንዲፈቅድ ፡ ይህንንም እስከ የካቲት 28 ድረስ ምላሽ እንዲሰጥ አሜሪካ አሳስባለች። በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የትህነግ አገዛዝ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ረቂቅ ህጉ ለኮንግረስ እንደሚቀርብ የኮንግረሱ አብላጫ ወንበር የያዘው የሪፑብሊካን መሪ አስጠንቅቀዋል። ረቂቅ ህጉ ለኮንግረስ ከቀረበ የማለፍ አድሉ ሰፊ እንደሆነ ይነገራል። ያ ከሆነ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር(ትህነግ) አገዛዝ ዶላሩም፡ የፖለቲካ ድጋፉም ይነጥፍበታል። በሂደት ባለስልጣናቱ በግል የመዘዋወር መብታቸው ገደብ ይጣልበታል። ዘርፈው ከሀገር ያሸሹት ሀብትና ንብረታቸው ይታገዳል። ይህ ህዝባችን እያደረገ ላለው ትግል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እናም ይህ እንዳይቀለበስ ወደ ስራችን እንመለስ።

መሀል ላይ ነን

እኛ ኢትዮጵያውያን መሀል ላይ ነን። መንገድ ላይ። ነጻነትን ፍለጋ ወጥተናል። መድረሻችን ከሀገራችን ነጻነት ነው። መሀል ላይ ብዙ ነገሮች ይገጥማሉ። ወጀብ ይኖራል። ማዕበል አይጠፋውም። እሳት፡ ነጎድጓድ፡ ይገጥማል። መሀል ላይ መከራው ብዙ ነው። ስቃዩ አይጣል ነው። መሀል ላይ ብናጠፋ አይፈረድብንም። ብንሳሳት ሃጢያት ሆኖ አይቆጠርብንም። መሀል ላይ ባለ አይፈረድም። መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ንጉስ ዳዊትም መሀሉ ላይ አትብላ የተባለውን የካህን እንጀራ በልቷል። መሀል ላይ የሚሆነው አይታወቅም። የሚገጥመንንም እንደዚያው። ለነጻነት መውጣታችን፡ መዳረሻችንም የት እንደሆነ ማወቃችን እንጂ በመሃል መንገድ ላይ የሚሆነውን አናውቅም። ጉዙአችን ይቀጥላል። ወጀቡን አልፈን፡ ማዕበሉን ተሻግረን፡ እሳቱን ዘለን ለመዳረሻችን የኢትዮጵያ ነጻነት እንበቃ ዘንድ ወደ ስራችን እንመለስ።

ለትግሉ ወገናዊ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ፣-የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የደሚሂት የጋራ መገለጫ በሚመልከት (ነአምን ዘለቀ)

ለትግሉ ወገናዊ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ፣-የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የደሚሂት የጋራ መገለጫ በሚመልከት

1. ማናቸው ድርጅት አርበኞች ግንቦት 7 ጨምሮ ከአባላቱም ፣ከደጋፊዎቹም። ከህዝብም የሚመጣ ትችት መቀበል የግድ ነው (ግዴታው ነው)። ፍጹም ሰው እንደሌለ ሁሉ ፍጹም ድርጅት ሊኖር አይችልም። የሚሰሩ ደግሞ ይሳሳታሉ። ስህተቶችን በአግባቡና ገንቢ በሆነ መልኩ በልዩ ልዩ መስመሮች ሲገለጽ አንድን ድርጅት የሚማርና ስህተቶቹንም እየረመ የሚሄድ ያደርገዋል። በዚህ አመለካከት ያለውን ለትግሉ ወገናዊ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ይስማማሉ ብዬ እገምታለሁ።

2. ሰሞኑን የወጣውና ብዙ ውዝግብ ያስነሳው የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የደሚሂት የጋራ መገለጫ በጣም አስፈላጊና ወቅታዊ እንደ ሆነ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም። ስርዓትን መለወጥ ብቻ ሣይሆን የተረጋጋ ሐገር ለመፍጠር እንደሚንቀሣቀስ የፖለቲካ ሃይል በበደል ብዛት የተቆጡ ኢትዮጵያውያን ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ዉስጥ እንዳይገቡ ማሣሠቡ ተገቢ ይሆናል።በመግለጫው እንደተቀሠው ሠማን እንጂ አረጋገጥን ተብሎ አልተጻፈም፤ በሐገሪቱ ክልሎች የሕወሐት አባላትና የሕወሐት መልዕክተኞች መኖራቸውንም በመግለጫው በግልፅ ያመለክታል፤ በአጠቃላይ የመግለጫው ይዘት ትናንት ከተከሠተው ይልቅ ሥለነገው የሚጨነቅ መሆኑንም ማስታወሡ ተገቢ ነው፡፡ የመግለጫው ዓላማ ይህ ቢሆንም በአንድ በተሻለና እወነታውን በተጨባጭ ከማሳየት ይልቅ አሻሚ በሆነ ቋንቋ በተጻፈ አንድ አንቀጽ ( በአንዱ ዛፍ) .ጫካው በመሸፈኑ ውዥንብር ተከስቷል፡፡

3. በዋናው ጭብጥና መንፈስ (በጫካው) ወስጥ የተካተተው መልክት ሕዛብዊ ወያኔ አርነት ትግራይ (ህወአት) በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ኢትዮጵያን ካልገዛሁ ኢትዮጵያን አፈርሳታላሁ ብሎ የሚንቀሳቀስ፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድርግ የትኛውንም ስልት ከመጠቀም ወደሁዋላ እንደማይል፣ ከነዚህም መሰሪ ስልቶቹ ወስጥ በዋነኘት የትግራይን ህዝብ ምሽግ ለማድረግ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ማናከስና ወደ የማይታረቅ ቅራኔ ወስዶ የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያ ህዝብ መነጠል ብሎም መገነጠል በመሆኑ

ሀ) “የትግራይ ህዝብና ህወአት አንድና የማይነጣጠሉ ናቸው” የሚለውን የ 26 አመታት የወያኔ ትረካና ፕሮፕጋናዳ መናድ፣ ማፍረስ ወሳኝ የትግሉ አካል መሆኑን ።

ለ) የትግራይ ህዝብ ፣ የትግራይ ምሁራን፡ የትግራይ ድርጅቶች የዚህ የወያኔ መሰሪ ተግባር ሰለባ እንዳይሆኑ እንዲያውም ትግሉን ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን እንዲያቀጣጥሉ ጥሪ ማቅረቡ።

በትክክሉ፡ በጥልቀትና በረጅሙ በማሰብም የኢትዮጵያ ሀገራችን የወደፊት ሰላም ፣ ሀገራዊ አንድነት፡ የህዝቦች አብሮ መኖር መጻኢ እድል ለሚያስስበው ማናቸውም ቅን (ቅንን የሚለው ይሰመርልኝ) ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህ መልክት ወቅታዊም አንገብጋቢም መሆኑን ሊያጡት አይችሉም ።

4. የወያኔ ፋሽስቶች የትግራይን ህዝብ ምሽግ አድርጎ የአምባገናዊ የዘረፋና የዘረኘነት ስረአቱን ለማሰቀጠል የሚያደርገውን የአልሞት ባይ ተጋዳይ እንቅሳቃሴ ለማምከን የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን ሁለ ገብ ትግሎችና ከወያኔ ፋሽስቶች ጋር የሚያድርገውን ትንንቅና ፍልሚያም በሚያፋፋምበት በአሁኑ ሰአት በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦችና ታጋዮች ሁሉ (በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የኣርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮችን ጨምሮ) የህወአትን ሰላዮችና ገዳዮች ከስርአቱ ጋር ምንም ቁርኘት ከሌላቸው የትግራይ ተወላጆች ነጥሎ መመታት አስፈላጊና ፡ ህዝቡም በትግሉ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ነው በመግለጫው የተገለጸው።

5. ሌላው የመገለጫው ጫካ ዋና መንፈስ የአግ7 ንቅናቄ በወያኔ ፋሽቶች የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተንኮልና መሰሪነት ሊመጣ የሚችለውን የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ ስጋት እንዳለው ነው የተገለጸው። በዚህ ፋሽታዊው ሕወአት በሸረበው ወጥመድ ውስጥ ታጋዩ ማህበረሰብ እንዳይገባ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያሰመረበት፡ እነዚህ ዋና ዋና መልክቶች መግለጽ ሃላፊነት ከሚሠማው የፖሊቲካ ድርጅት የሚጠበቁ ተግባራት ናቹው፡፡

6. በእርግጥ በዚሁ ብዙ አነጋጋሪ በሆነው መግለጫ ላይ የተጻፈው አንድ አንቀጽ (አንድ ዣፍ) የሚሰጠው ትርጉም ከላይ በስተመጨረሻ #5 ከተጻፈው የተለየና ብዙዎች በሌላ መልኩ እንዲረዱት ማድረጉ ለተነሳው ውዝግብ መንሴኤ ሆናል።

7. በብዙሃን ቅን ኢትዮጵያውያን (አባላት፡ ደጋፊና፡ ለትግሉ ቀናዊ ከሆኑ) ኢትዮጵያውያን ወንድሞችና እህቶች አወዛጋቢዎችን አንቀጽ በሚመለከት የተነሱ ጥያቄዎች፣ ገንቢ አስተያየቶችና ፡ እርምት እንዲደረግና ንቅናቄው መልስ እንዲሰጥበት ከሚያስስቡ መልክቶች ሁሉ እንደተጠበቁ ሆነው ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከወያኔ ይልቅ ትግላቸውን ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ለማድረገ የወስኑ ክፍሎችን በተመለከተ በአጭሩ ለማለት የምፈልገው በእርግጥ የሕዝቡ ሥቃይ ይሰማችኃልን ? በእርግጥ ከተሰማችሁ ሕዝብን ከሚያሠቃየውና ከሚጨፈጭፈው ሕወሐት ይልቅ ሕወሐትን የሚታገለው አርበኞች ግንቦት 7 እንዴት ዋነኛ ጠላታችሁ ሊሆን ቻለ? .መልሡን በቅንነት ለሚዳግፏቸው ወገኖቻችን እንደሚሰጡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

8. የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ምንም ሳይደርስባቸው ገና ከጅምሩ በጠላትነት ፈርጀውት ከወያኔ ይልቅ ዱላቸውን በሙሉ ጊዜና ህይል ሳይቆጥቡ ለዚህ የጎንዮሽ ልፊያና ጠለፋ የሰጡ፣ ነገር ግን ለዚህ ውስብስብና ብዙ አቀበትና ቁልቁለት ለበዛበት ትግል ምንም ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የማያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ማህበራዊ ሚዲያውን አጨናንቀውት እያየን ነው፡

9. በአንጻሩ ይህን ትግል ዳር ለማድረስ ምን ያህል መስዋእትነት እየተከፈለና በተግባርም ብዙ ብዙ ተግባራዊ ስራዎች በሀገር ውስጥም በውጭም እየተሰሩ እንደሆነ የሚያውቁ፣ የሚረዱ፣ ለትግሉም ቀናኢ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የዚህ መሰሪ አካሄድ ሰለባ ላለመሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና ፡ በስሜት ሳይሆን በአምክንዮና ለትግሉ የሚጠቅመውን፡ የወያኔን ፋሽታዊ አገዛዝን የሚያስጨንቀውና የሚያዳክመውን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ለድል የሚያደርሱ፣ የሚያበቁ ፣ ለሀገራችን ኢትጵዮጵያ ትንሳኤን የሚያፋጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል። በሰከነ አእምሮ ማሰብ የሚያስፍልግበት ስሱ ወቅት ስለሆነ፡ ቆም ብለን ፡ ትንፋሽ ወስደን በረጅሙና ከፊታችን በተደቀነው ተግባሪዊ ትግል ላይ አይናችንን እንዳናነሳ ማድረግ ያስፈልጋል። ጥንቃቄ እንዳርግ በሚል በትህትና ለማሳሰብ እወዳለሁ።

ነአምን ዘለቀ

የህወሀት ጸሀይ እየጠለቀች ነው ( ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የህወሀት ጸሀይ እየጠለቀች ነው

ብዙ ምልክቶች በመታየት ላይ ናቸው። ተመልሶ የሚያንሰራራበት እድል ያለ አይመስልም። እየተንፏቀቀ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። እግሮቹ ተሰብሮ በደረቱ እየተሳበ ከቤተመንግስት የተወሰነ ጊዜ ሊቆይ ይችላል። ስጋው አልቆ በአጥንቱ ቆሞ ጥቂት ጊዜያት መቆየቱ የማይቀር ነው። በዘላቂነት ግን አልቆለታል ማለት ይቻላል። የህዝቡ ተቃውሞ ሳይቋረጥ ከቀጠለ፡ ከያቅጣጫው የበረታው ግፊት ጉልበቱን ጨምሮ ይበልጥ ከገፋ የሚንፏቀቀውን፡ እግሮቹ የተሰበረውን፡ በአጥንቱ የቀረውን ህወሀት ከታሰበው ጊዜ በታች ዘላለማዊ ሞቱን የሚጨልጥ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። እስቲ ምልክቶቹን አንድ በአንድ እንመልከታቸው፥-

የትግራይ ህዝብ

ህወሀት ከ2010 ዓም ዋዜማ ጀምሮ መቀሌ ከቷል። ላለፉት አምስት ወራት በስብሰባ፡ በኮንፈረንስ፡ በግምገማ፡ በህንፍሽፍሽ፡ በጉባዔ ተጠምዶ ከርሟል። አሁንም እንደሚኖር ይጠበቃል። ትግራይ የህወሀት የመጨረሻ ምሽግ ናት። ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ልብ ማግኘት ያቃተው ህወሀት አክ እንትፍ፡ ተብሎ መተፋቱን አረጋግጧል። የኢትዮጵያን ህዝብ በፍቅርም፡ በጉልበትም መምራት እንደማይችል ተረድቶታል። ከእንግዲህ ወርቅ እንኳን ቢያነጥፍ የሚቀበለው እንደሌለ አውቆታል። ስለዚህ ወደ መጨረሻ ምሽጉ ፊቱን አዙሯል። ይህ ምሽግ የተወሰነ ዕድሜ እንደሚያዘልቀው ተማምኗል። በኋላ ኪሱ የሸጎጣትን ”የትግራይ ሪፑብሊክ” ምስረታ ከተሳካለትም ይሞክራል። በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት በበላይነት መቆየት ካልቻልኩ ያሉኝ አማራጮች ብሎ ከያዛቸው እርምጃዎቹ አንዱ ወደ ትግራይ ጠቅልሎ ገብቶ ምሽጉን ማጠናከር ነው።ለዚህም የትግራይን ህዝብ ልብ ሙሉ ለሙሉ ለማግኘት ቃል በመግባት ተግቶ እየሰራ ነው።

ህወሀት ምሽጉን ለማጠናከር እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። ከእነዚህም አንዱ የትግራይን ህዝብ ታች ወርዶ ይቅርታ መጠየቅ ነው። በልማት ማንበሽበሽ ነው። ቀድሞውኑ ያዘነበለውን ተጠቃሚነት ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ነው። ሰሞኑን እንደተሰማውም የትግራይ ህዝብ ለከፈለው መስዋዕትነት የሚመጥን ልማት ሊዘረጋለት ተወስኗል ተብሏል።። ከወዲሁ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል እስከአሁን ተገንብቶ የማያውቅ በፌደራል መንግስቱ በጀት በ2ቢሊየን ብር የኮንክሪት አስፋልት ግንባታ ስምምነት ተደርጓል። ኢፈርት የዘመናዊና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ ስምምነቶችን እያጣደፈ ነው። ከአማራና ከኦሮሞ አርሶአደሮች ከመደበኛው የገበያ ዋጋ ከፍ ባለ መጠን የተለያዩ የእህል አይነቶች እየተገዙ ወደ ትግራይ እየተጫኑ ነው። በትግራይ በተለያዩ አከባቢዎች ግዙፍ ጎተራዎች ተተክለው እህሎች እየተከመረባቸው ነው። ምናልባት ነገሮች ከረው ወደትግራይ የሚወስዱ መስመሮች ቢቋረጡ በሚል ብዙ ምርቶች በገፍ ተገዝተው እየተጠራቀሙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ህወሀት የትግራይን ህዝብ እየተለማመጠ፡ እየተማጸነ መሆኑ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ዞሮ መግቢዬን፡ መቃብሬን አጣለሁ ከሚል ስጋት ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። የመቀሌው ኮንፍረንስ የህወሀት የነፍስ አድን ጥሪ እንደሆነ ይነገራል። የመጨረሻ ምሽጉን አስተማማኝ ለማድረግ ነው። የህወሀት አመራሮች ”ልባችሁን ክፈቱልን። በጠላት እጅ ላይ ከምንወድቅ በእናንተ ክንድ ላይ የመጨረሻዋ እስትንፋሳችን ታልፍ ዘንድ ፍቃዳችሁ ይሁን” ዓይነት ልመና ባደረጉበት የቅርብ ጊዜው ኮንፍረንስ ያሰቡትን ያህል ስለማግኘታቸው የሚታወቅ ነገር የለም። አይናቸውን በጨው አጥበው ግን ”ከማንም በላይ መስዋዕትነት ስለከፈላችሁ ትካሳላችሁ። ጊዜው ደግሞ አሁን ነው ” የሚል በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራ ለትግራይ ባላት ላይ ሊከምሩባት፡ ወስነዋል። የሚያስጨንቃቸው ስልጣናቸው ነው። አዲስ አበባ ላይ ተነቃንቋል። ቢያንስ መቀሌ ላይ ምሽጋቸውን አጠናክረው ትንሽ ጊዜ የሚያቆያቸውን ሃይል ማጠራቀም አለባቸው። ማምሻም እድሜ ነውና።

የትግራይ ህዝብ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም። የህወሀት ካድሬዎችን፡ ደጋፊዎችንና አባላትን ጩሀት ለሰማ ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። ጨፍነው ግፋ እያሉት ነው። አበጀህ የእኛ ልጅ ከሚል ሞራል ጋር የህወሀትን የጥፋት ዕቅድ እየደገፉት ነው። ይህ ስሜት የትግራይ ህዝብ በሙሉ ነው ለማለት ይከብዳል። ድምጹ ስለማይሰማ፡ የሚጮሁት ጥቂቶች የሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ስሜት ቀይረው በጅምላ የትግራይን ህዝብ ከወገኑ እንዳይነጥሉት ስጋቱ አለ። የትግራይ ህዝብ ለህወሀት የመጨረሻ ምሽግ መሆን የለበትም። ህወሀት ያልፋል። በቅርቡ። ከማያልፈው ህዝብ ጋር ሰልፉን እንዲያስተካክል ይጠበቃል። ህወሀት እየገነባ ያለውን የመጨረሻ ምሽግ ቀድሞ ማፍረስ ያለበት የትግራይ ህዝብ ነው።

የኢኮኖሚው ቀውስ

አይ ኤም ኤፍ ሰሞኑን እንዳስታወቀው የህወሀት መንግስት ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከአንድ ወር ከ8ቀናት በላይ የሚያዘልቀው አይደለም። መረጃዎች የሚያሳዩት ግን ከዚህም በላይ አስደንጋጭ ነው። ከአንድ ቢለየን ዶላር በታች የደረሰው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ህወሀትን እጅና እግሩን አሳስሮ አስቀምጦታል። አይ ኤም ኤፍ ለህወሀት የሚጨክን አንጀት ስለሌለው እውነተኛውን ቁጥር ስለመግለጹ ጥርጣሬ አለ። የሆኖ ሆኖ የአይ ኤም ኤፍ መረጃ በራሱ ብዙ ነገሮችን ይነግረናል። አንድ መንግስት በዚህ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ አቅም ላይ ከደረሰ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም። ኢኮኖሚው በከፍተኛ ፍጥነት ወደ እየወደቀ ነው። የአገዛዙ ጠበቃ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣ ”ለመንግስት ከባድ አደጋ መጥቶበታል” ሲል በተቆርቋሪነት ስጋቱን ገልጿል።

የውጭ ንግድ ተዳክሟል። ኢንቨስትመንት የኋሊት እየገሰገሰ ነው። የንግድ ስርዓቱ ተፋልሷል። ግብይቱ ተረባብሿል። የቱሪዝሙ ዘርፍ እያቃሰተ ነው። በእንቅርት ላይ እንዲሉ የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉ ቀውሱን አባብሶታል። የዋጋ ግሽበት ከአንድ አሀዝ ወደ ሁለት አድጓል።በሀገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄዱ ባሉ ተቃውሞችና ህዝባዊ አመጾች ምክንያት የንግድ ቦታዎች ስራ ፈተዋል። በየጊዜው የሚመታው አድማ መደብሮችንና ሱቆችን ጾማቸውን እንዲከርሙ እያደረገ ነው። በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ተቃውሷል። መፍትሄው ከህወሀት አቅም በላይ ሆኗል። ከውስጥ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የህወሀት አገዛዝ በድጋሚ የብርን የመግዛት አቅም ለመቀነስ እየተዘጋጀ ነው። ይህ ከሆነ በኑሮ ውድነት ጀርባው የጎበጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የመኖር ህልውናው ያከትማል ሲሉ መጪውን ጊዜ በስጋት የሚገልጹ ወገኖች አሉ። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ተጠያቂነት ባለባቸው ሀገራት እንዲህ ዓይነት ቀውስ በሩብ ያህል ቢከሰት እንኳን መንግስትን የሚመራው አካል በራሱ ጊዜ ከስልጣን ይወርዳል።

ህወሀት የኢኮኖሚው ነገር ከአቅም በላይ ሆኖበታል። መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ተስኖታል። ውሃ መብራትና ሌሎች አገልግሎቶች የሚቆራረጥባቸው፡ ጭራሽኑ የማያገኙ ከተሞች እየጨመሩ መጥተዋል። የነዳጅ እጥረቱ ተባብሷል። ለነዳጅ መግዣ የሚሆነው የውጭ ምንዛሪ እየተሟጠጠ በመሆኑ በቀጣይ ቀውሱ ሊከፋ እንደሚችል ይጠበቃል። ለመድሃኒት መግዥ የምትሆነዋ የቀረችው የውጭ ምንዛሪም ተመናምናለች። ህገወጥ የመድሃኒት ዝውውር ይህን ተከትሎ የሚዛመት በመሆኑ ከፍተኛ የጤና ቀውስ ይከሰታል ተብሎ ይሰጋል። በአንዳንድ አከባቢዎች የመንግስት ሰራተኞች ደመውዝ ሳይከፈላቸው ወራት እንደሚቆጠሩ ተሰምቷል።

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የከፈቱት የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦም ለህወሀት መንግስት ራስምታት መፍጠሩ እየተነገረ ነው። የውጭ እርዳታ በነጠፈበት፡ ብድር ሰጪዎች እጃቸው ባጥረበት በዚህን ወቅት የህወሀትን ኢኮኖሚ ደጋግፎ የያዘው ሪሚተንስ(ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የሚላክ ገንዘብ) እንዲቀንስ የተጀመረው ዘመቻ ውጤት እያሳየ ነው። ህወሀት ብርክ ይዞታል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የህወሀትን አገዛዝ ነፍስ ቀጥ አድርጎ የያዘው የሪሚተንስ ገንዘብ ነው። እሱ በአንዳች ሁኔታ ከቀነሰ ለማፈኛ ተቋማቱ የሚከፍለው ገንዘብ አይኖረውም። ይህም የማፈን አቅሙን ያዳክማል።ያ አቅሙ ከተዳከመ ደግሞ ይገነደሳል። አዲዮስ ህወሀት!

የፖለቲካ ምሁራን እንደሚስማሙት በኢትዮጵያ እስከአሁን ከተደረጉት ህዝባዊ ተቃውሞዎች በላይ ሀገር አቀፍ የሆኑ አመጾችና እምቢተኝነቶች መቀጣጠላቸው አይቀርም። የኢኮኖሚው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ከተሞች፡ መንደሮች፡ አውራጎዳናዎች በተቃውሞ ይጠለቀለቁ ዘንድ የሚጠበቅ ነው። የአገዛዙ ደጋፊ የሆኑ ሚዲያዎችም ይህን ሀቅ እየጎመዘዛቸውም ቢሆን እየተናገሩት ነው። ሪፖርተር እንዳለው መንግስት በአስቸኳይ መፍትሄ ካልሰጠ የኢኮኖሚው ቀውስ የበለጠ የህዝብ ተቃውሞዎችን ያመጣል። በየቀኑ የአመጽ ሰልፎችን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

ውስጣዊ ቀውስ

ህወሀት በራሱ ውስጥና እንደኢህአዴግ ከአባል ድርጅቶች ጋር የገባበት ቀውስ የሚሰክን አልሆነለትም። ከመቀሌው የነፍስ አድን ኮንፍረንስ ጎን ለጎን እየተለቀቁ ያሉት ሚስጢሮች ህወሀት ይበልጥ በውስጣዊ ቀውስ እየተሰቃየ ለመሆኑ ምልክት የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል። በተሸነፈው ቡድን የሚዘከዘኩት ጉዶችና ቅሌቶች በህወሀት መንደር ያለው አንድነት መናጋቱን የሚያመላክት ነው። በተለይ የህወሀት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልልን በም/ፕሬዝዳንትነት እንዲመራ የተሰየመው የወሲቡ ሻምፒዮን ደብረጺዮን ገብረሚካዔል ላይ የተከፈተው የማጋለጥ ዘመቻ ለህወሀት ትልቅ አደጋ እንደሚሆን ይገመታል። የተመታው ቡድን እጁን አጣጥፎ እንዳልተቀመጠ እያስመሰከረ ነው። ያለድርጅታዊ መተዳደሪያ ደንብ ወደ መቀሌ ዳግም እንዲከትና በኮንፍረንስ እንዲጠመድ ያደረገው የውስጣዊ ሽኩቻው እየበረታ በመምጣቱ እንደሆነም ይነገራል። በትግራይ ሽማግሌዎች እግዚዮታና ልመና ለጊዜው ጋብ ቢልም ህወሀት እንደ ድርጅት ለመቀጠል የሚያስችል ውስጣዊ አንድነቱ እንደሰባበረ የሚደብቁት አልሆነም።

ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ17 ቀናቱ ዝግ ስብሰባ በኋላ ”ልዩነታችንን ፈተናል። አንድ ሆነናል” የሚለው መግለጫ በወረቀት ላይ እንጂ መሬት ላይ እንደሌለ ከዚያን ወዲህ የተፈጠሩ ነገሮችን በመጥቀስ መግለጽ ይቻላል። ለጊዜው ውጥረትን ማስተንፈስ የቻሉ ቢመስልም አንድነታቸው ላይመልስ መናጋቱ ከማይደበቅበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። የኦህዴድና የብአዴን አመራሮች አሁንም በአቋማቸው እንደጸኑ ናቸው። የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን ከዝጉ ስብሰባ በኋላም የሚያደርጋቸው፡ የሚናገራቸው ለህወሀት ምቾት የሚሰጡ አልሆኑም። በ17ቱ ቀናት ዝግ ስብሰባ ያደረግነውን ተጋድሎ ህዝቡ ቢያውቀው ጥሩ ነበር ያሉት አቶ ለማ ስምምነት እንደሌለ በጎን እየነገሩን እንደነበረ አልተረዳናቸውም። በእስረኞች መፈታት ላይ በተለይ የኦህዴድ አመራር የያዘው አቋም አሁንም ኢህአዴግ ቤት ቀውስ እንዳለ ግልጽ መልዕክት ነው። የፌደራል መንግስቱን የፍቺ መስፍርት አልቀበልም ያለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ህወሀቶች የሚተናነቃቸውን ”የፖለቲካ እስረኞች” ን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚፈታ አስታውቋል።

አቶ ለማ የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ የገዙበትን የፍቅርና የአንድነት መልዕክታቸውን ከዝጉ ስብሰባ በኋላም ቀጥለውበታል። ህወሀት ያወገዘውን ”የመርህ አልባ ግንኙነት” የቀጠሉት አቶ ለማ መገርሳ ”ነፍስ ዘር የላትም” በሚል አዲስ ቀልብ ሳቢ መልዕክታቸው ብቅ ብለዋል። ከዚያም ተሻግረው በለገጣፎ የኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን የገጠማትን የጥገኛ ባልስልጣናት አደጋ አስወግደው ቤተክርስቲያኒቱ ይዞታውን አግኝታ አገልግሎቷን ያለምንም ችግር እንድትቀጥል ማድረጋቸው በእርግጥም ሰውዬው የህወሀትን የልዩነት ግንብ ሳይደረምሱ እንቅልፍ እንደማይወስዳቸው ያረጋገጡበት ውሳኔያቸው ነው። የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የባህርዳሩ ኮንሰርትም ከህወሀት ፍላጎት ውጪ ስለመፈቀዱ ምንም ጥርጥር የለውም። ኮንሰርቱ በመካሄዱ ህወሀት የሚያተርፈው አንዳችም ነገር ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም። ይልቅስ የገዱ ቡድን በብአዴን ውስጥ ያለውን የህወሀት ተላላኪ አመራርና የመቀሌውንም ገዢ ቡድን ተጋፍጦ የፈቀደው ኮንሰርት መሆኑን መግለጽ ይቻላል።

እናም ኢህአዴግ ውስጥ የገባው ንፋስ ህወሀትን እያናጋው ቀጥሏል። ወደ መቀሌ አማትሮ የመጨረሻ ምሽጉን እንዲያጠናክር ያደረገውም በኢህ አዴግ ውስጥ የነገሰው ክፍፍል በቀላሉ የሚጠገን ባለመሆኑ እንደውም ህልውናን የሚያጠፋው እንደሆነ በመረዳቱ ነው።

የአፍሪካው ቀንድና የምዕራባውያን አቋም

የምዕራባውያን ፍላጎት የህወሀት አገዛዝ እንደምንም ብሎ በስልጣን ላይ ቢቆይላቸው ነው። አሁን ግን ያ የሚሆን አልመሰላቸውም። ህወሀት የተለከፈበት በሽታ ለእነሱም መዘዝ እንደሚያመጣ የተረዱት ይመስላል። ከወዲሁ አንዳንዶቹ እጃቸውን መሰብሰብ ጀምረዋል። ለህወሀት ፊት መነሳታቸውን የሚያረጋግጡ ምልክቶችን በአደባባይ እያሳዩ ነው። በጀርባ አዝለው ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ያስገቡት የአሜሪካው ዲፕሎማት የሰሞኑ የቲውተር መልዕክት አንድ ፍንጭ የሚሰጥ ነው። ከ27ዓመት በኋላ የህወሀት ጭራቅነት የተገለጠላቸው ዲፕሎማቱ ሀርማን ኮን የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበት አቋም አስደንግጦአቸዋል። ”ከህወሀት ደርግ የተሻለ ነበር”

በእርግጥም አሜሪካ እየተንሸራተተች ነው። ከህወሀት አገዛዝ ጋር ለዘመናት የተጣበቀችበትን የውጭ ፖሊሲዋን ልትቀይረው መውሰኗን ታውቋል። የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሰሞኑን እንደተናገሩት ”አሜሪካ የጸረ ሽብር አጋርነት ላይ የተመሰረተው የውጭ ፖሊሲዋ አብቅቷል” ይህ ውሳኔ ለህወሀት አገዛዝ ታላቁ መርዶ ሊባል የሚችል ነው። ድሮውኑም ከፖለቲካ ድጋፍ በቀር ከህወሀት ጋር የኢኮኖሚ ወዳጅነት ያልፈጠረችው አሜሪካ ብቸኛውን የግንኙነት መስመር ለመበጠስ መወሰኗ ለነጻነትና ዲሞክራሲ ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የምስራች ሲሆን ለህውሀትና ደጋፊዎቹ አስደንጋጭ ዜና ነው። ይህ ውሳኔ ህወሀትን የሚያሳጡት በርካታ ነገሮች አሉ። በዓለም ዓቀፍ ዲፕሎማሲ ላይ የአሜሪካንን ጭራ እየተከተለ ድጋፍ ሲያሰባስብ የከረመው ህወሀት በተላላኪነት ያገኘውን ተሰሚነት የሚያጣበት ይሆናል። በጸረ ሽብር አጋርነት የሚያገኛቸውንና ኢትዮጵያውያንን የሚገድልባቸውን አሜሪካ ሰራሽ የጦር መሳሪያዎችን ከእንግዲህ ይነጥፍበታል። በዚሁ የጸረ ሽብር አጋርነት የሚሰጠውም ዶላር ይቆማል። ይህ በፖለቲካ ድጋፍ የሚያገኘው ዶላር ለህወሀት የመኖር ዋስትናው ሆኖ ቆይቷል። የእንጀራ ገመዱ ነበር።

የአፍሪካው ቀንድ ፖለቲካዊ ትኩሳት ላይ ነው። የግብጽና የሱዳን ፍጥጫ በርትቷል፡፡ የአረብ ሀገራት በረጅም እጃቸው የሚያምሱት ቀጠና ሆኗል። ወደለየለት አጠቃላይ ቀውስ ባይገባም ከወዲሁ የሚታዩት ፍንጮች ለህወሀት አገዛዝ ህልውና ወሳኝ መሆኑ አይቀርም። የህዝብ አመጽ ገፍቶ ከቀጠለ ከአፍሪካው ቀንድ ቀውስ በፊት ህወሀት ሊሰናበት ይችላል። ካልሆነም ቀውሱ የህወሀትን ዘላለማዊ ሞት እንደሚያስከትል የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ። ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን ቢደረድሩም የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሀትን የመሰለ ጨካኝ አገዛዝ ቤተመንግስት አስቀምጦ የትኛውንም የውጭ ወራሪ ሃይል ለመዋጋት የሚሰለፍ አለመሆኑ ዋናው ምክንያት እንደሆነ ይስማማሉ። ሻዕቢያ መጣብህ እያለ ህዝባዊ ድጋፍ ማሰባሰብ ከእንግዲህ የሚቻል አይደለም። እንኳን ሻዕቢያ ግብጽም ከመጣች ጦርነቱ የህወሀትና የግብጽ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አይሆንም የሚለው አቋም ከወዲሁ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተመላለሰ ይሰማል። ህወሀትን ይዞ ጦርነት አያዋጣም። እንደውም ህወሀትን ለመሰናበት ጥሩ አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል።

ማጠቃለያ

አስቸኳይ አዋጅ ያላስቆመው፡ የደህንነት ምክርቤት ማጠንቀቂያ ያላበረደው፡ የኢህአዴግ መግለጫ ያልገታው፡ የእስረኞች ፍቺ ያላዘናጋው ህዝባዊ ተቃውሞ ቀጥሏል። የጥምቀት ዋዜማ የከተራ በዓል በጸረ ህወሀት መልዕክቶች ደምቆ ነው የተከበረው። በአምቦ፡ ጎንደር፡ ነቀምት ፡ ወልዲያ አንድ መልዕክት ይሰማል ”ቻው ቻው ወያኔ፡” ዛሬ በወልዲያ አራት ሰዎች የተገደሉበት ተቃውሞም የሚያመላክተው የኢትዮጵያ ህዝብ የትኛውንም መስዋኢትነት ከፍሎ ህወሀት የሚባል ኋላቀር፡ አውሬ አገዛዝን ለመገላገል መቁረጡን ነው። አዎን! የህወሀት ጸሀይ እየጠለቀች ነው።

ታዳሚን እንባ ያራጨው የችሎት ውሎ (በጌታቸው ሺፈራው)

ታዳሚን እንባ ያራጨው የችሎት ውሎ

(በጌታቸው ሺፈራው)

ዛሬ በጠዋት ሰብሰብ ብለን የገባነው ወደ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነበር። ከ4ኛ ወንጀልችሎት ስወጣ 19ኛ ወንጀል ችሎት ታዳሚውን ያስለቀሰ፣ ዳኞቹን ሳይቀር ያሳዘነ ትዕይን እንደነበር ሰማሁ። 19ኛ ወንጀል ችሎት የነበረ አንድ ጓደኛዬን ማስታወሻውን እንዳየው ጠየኩት። የተጀመሩ ዐረፍተ ነገሮች፣ ያልተቋጩ ሀረጎችን አነበብኩ። በእርግጥ እንባ በሚያራጭ ትዕይንት ውስጥ መፃፍ ከባድ ነው። እኔንም ብዙ ቀን አጋጥሞኛል።የጓደኛዬ ማስታወሻ ላይ የሰፈሩ የተቆራረጡትን ዐረፍተ ነገሮች መዝግቤ፣ ጓደኛዬ በችሎት ያየውን እንዲያብራራልኝ ጠየኩት። በአማራ ክልል በነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ ሰበብ የታሰሩትና በእነ ታደሰ መሸሻ አሰጌ ክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል 3ኛ ተከሳሽ የሆነው ዮናስ ጋሻው ደመቀ በሌሎች የአማራ ወጣቶች የሚፈፀመው ጭካኔ ተፈፅሞበታል። አስቻለው ደሴና ሌሎች አማራ ወጣቶች እንዳደረጉት ሱሪውን በችሎት አውልቆ “ህዝብ ይፍረደኝ” ብሏል። ሃይላንድ ያንጠለጠሉበትን ብልቱን አሳይቷል።በዚህ ወቅት ታዳሚው አልቅሷል። ጓደኛዬ ይህን ሰቆቃ እያየ በደንብ መፃፍ አልቻለም። ዳኞች እንኳ አንገት ደፍተዋል። በጠዋቱ ችሎት በተከሳሹ ሰቆቃ ያለቀሱትን ታዳሚዎችም አነጋግሬያቸው ነበር። ከሰዓትም ሀዘኑ ሳይለቃቸው ስለ ሰቆቃው ነግረውኛል።

ዮናስ ማዕከላዊ በነበረበት ወቅት ሀይላንድ አንጠልጥለውበታል። በፒብሳ ከታትፈውታል። እግሩ ተጎድቷል። ማዕከላዊ በተፈፀመበት ሰቆቃ የነርቭ በሽተኛ ሆኗል። ይህን ሲናገር ሰቆቃውን ያደረሱበት ሁለት የማዕከላዊ ገራፊዎች ችሎት ውስጥ ተቀምጠው ነበር።

የጓደኛዬ ማስታወሻ አገላበጥኩ። ዮናስ የተበደለው ማዕከላዊ ብቻ አይደለም። ከመታሰሩ በፊትም በቤተሰቡ ላይ በደል ደርሶበታል። ” ወንድሜን ሆን ብለው በኦራል(መኪና) ገጭተው ገደሉት፣ እናቴንም በተመሳሳይ መልኩ ገድለውብኛል። በማዕከላዊ አማራና ኦሮሞ ዘር እንዳይተካ ለምን ይደረጋል? የተማርነው ጥላቻ ነው። የእኛ ትውልድ ከእኛ ምን ይማራል? ሀይላንድ ተንጠልጥሎብኛል። በፒንሳ…… ሁላችንም ጉዳት ደርሶብናል” ብሎ በችሎት ምሬቱን ተናግሯል።

የዮናስ ስቃይ ከማዕከላዊ በኋላም አላበቃም። በማዕከላዊ የደረሰበትን ጉዳት ለመታከም ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ተወስዶ፣ ከአቅማችን በላይ ነው ብለውታል። ጳውሎስ ሄዶ የአጥንት ስብራት እንዳለበት ማረጋገጫ ቢሰጠውም ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውጤቱን አጥፍቶበታል። በድብደባው ምክንያት የቀኝ እግሩ ሽባ ወደመሆን ደርሷል። ለዚህም ሽፍን ጫማ ያስፈልጋል። ሆኖም ሽፍን ጫማውን ገብረእግዚ የተባለ የገዥዎች ወገን ቀዶ ጥሎበታል። “ሽፍን ጫማ ለማድረግ እንኳ ብሔር መቀየር አለብን” ሲልም ገዥዎቹ እያደረሱበት ያለው በደልና ጭካኔ ቅጥ ጠይቋል።

ጠዋት ቀጠሮ የነበራቸው ተከሳሾች ጉዳይ ከሰዓትም ይቀጥላል ስለተባልን ከማህሌት ፋንታሁን ጋር ከሰዓት ወደ 19ኛ ወንጀል ችሎት አቀናን።ተከሳሾቹ ወደ ቂሊንጦ ሄደው ስለነበር ችሎት ስራ ይጀምራል ከተባለው ሰዓት ዘግይተው ደረሱ። ከሌሎች ተከሳሾች ቀደም ብሎ አንድ ተከሳሽ እያዘገመ ነው። በቀኝ ጎኑ በኩል ሌላ ተከሳሽ ደግፎታል። ወዲያውኑ ከኋላው የነበሩት ተከሳሾች አለፉትና ተደግፎ ከኋላ ማዝገም ጀመረ። በጠዋቱ የችሎት ጊዜ ሱሪውን አውልቆ የተፈፀመበትን በደል የተናገረው ተከሳሽ እንደሆነ መገመት ችያለሁ። ተከሳሾች ወደ ችሎት ከገቡ በኋላ እኛም ለመታደም ገባን። ተደግፎ ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ወዳለው ጊዜያዊ ማቆያ ያቀናው ተከሳሽ ፊት ወንበር ላይ ተቀምጧል። የቀኝ እግሩ ለሚያየውና የደረሰበትን በደል ለሚገምት በሚሰቀጥጥ መልኩ ይንቀጠቀጣል። ተቀምጦ እንኳን በቀኝ እግሩ አይረግጥበትም። የቀኝ የሰውነት ክፍሉ እስከ ትክሻው ድረስ ይንዘፈዘፋል።ችሎቱ ስራ ላይ በነበረበት ሰዓት ለሽንት ተደግፎ ሲወጣ የቀኝ እግሩን በደንብ አይረግጥበትም። ይጎትተዋል ማለት ይቀላል።

የማዕከላዊ ምስክሮች

ከሰዓት በነበረው የፍርድ ቤቱ ሰዓት ሁለት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ተሰምተዋል። በቀዳሚነት የተመሰከረበት ደግሞ ሰቆቃ የተፈፀመበት ዮናስ ነው። ምስክሩ ባህርዳር ከተማ ይኖር የነበር ደላላ እና የሆቴል ባለቤት ነኝ አለ። አሁን ተፈትቼ ባህርዳር እገኛለሁ ብሎ ቃሉን ሰጠ። እውነታው ግን ሌላ ነው። ዮናስ ጋሻው ወደ ግንቦት 7 እንድልከው ጠይቆኝ ነበር ብሎ መሰከረ። ቆይቶ ደግሞ የአማራ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (አሕነን) የተባለ፣ የግንቦት 7 ቅርንጫፍ ነው ያሉት ቡድን እንዲቀላቀል በአንድ ስብሰባ እንደተነገረው፣ ከምሽቱ 12 ሰዓት ተሰብስው ማታው መንግስትን ለመገልበጥ ጦርነት ሊያደርጉ፣ ምስክሩም አባል እንዲሆን በተነገረው በነጋታው በተነገረው ጦር አደራጅቶ አባይን ሊያስዘጋ ተልዕኮ እንደተሰጠው መሰከረ። ምስክሩ መረጋጋት አይስተዋልበትም። የሚሰጠው መልስ ይበቃል እየተባለ እንኳን ማብራሪያውን ይቀጥላል። ዐቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቱም፣ የተከሳሾች ጠበቃም “በቃ” እያሉት አይበቃውም።

ፍርድ ቤቱ በመሃል እየገባ “ወደ ግንቦት 7 ለመሄድ የሚጠየቁት ምን ሰለሆኑ ነው? ወደ ግንቦት 7 እንዲልኩት ሲጠይቅ የነበረ ሰው እንዴት የግንቦት 7 ቅርንጫፍ ነው የተባለ ቡድን መስርቶ እንዲቀላቀሉ ይጠይቅዎታል? በአንድ ቀን ዝግጅት እንዴት ጦርነት ይደረጋል? አንድ ቀን ተነግሮዎት ያለ ዝግጅት እንዴት አባይን ያስዘጋሉ? ማን ጋር ሆነው አገኙት?……” ብዙ ብዙ ጥያቄ አነሳ። 19ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች አንድ ቀን በማጣሪያ ጥያቄ ምስክርን አጥብቀው ሲጠይቁ አይቻለሁ። ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲመሰከርባቸው። እንደዛሬው ምስክርነት ግን ግራ ሲጋቡ፣ ግራ የተጋቡበትን የምስክርነት ቃል ለተከሳሽ የሚጠቅም በሚመስል መልኩ ሲጠይቁ አይቼ አላውቅም። ምን አልባት፣ ጠዋቱ የፍርድ ቤቱ ሰዓት የተነገረው ተፅዕኖ ፈጥሮ ይሆናል።

ተከሳሾች በጠበቃ አለልኝ ምህረቱ በኩል ምስክሮቹ ማዕከላዊ ታስረው እንደነበር፣ ተገደው እንደመሰከሩ፣ በድብደባ ብዛት “ልንመሰክርባችሁ ነው” ብለው ለተከሳሾች እንደነገሯቸው ጠየቁ፣ ዳኞችም አጣሩ። አንደኛው ምስክር “ሁላችንም ከምንታሰር የተወሰንነው ለቤተሰብ እንድረስ ብያቸዋለሁ” ብሎ አመነ። በጠበቃና በዳኞች ጥያቄ ብዛት ሌላኛው ምስክርም “መንግስት ምህረት ያደረገልኝ በእነሱ ላይ እመሰክራለሁ ስላልኩ ነው” ብሎ የማዕከላዊ ምስክር መሆኑን ተናገረ። ስልክ ስለመደዋወል ሲመሰክር የነበረው አንድ ምስክር “አሁን ስልክ የት አለ?” ሲባል “አልጋ የያዝኩበት ሆቴል አስቀምጨቃለሁ” ብሎ ተናገረ። ስልክ ቁጥሩን ሲጠየቅም “092 352 9019” ብሎ ተናገረ። ከችሎት እንደወጣሁ በዚህ ቁጥር ላይ ደወልኩ። ከቴሌ የድምፅ መልዕክት “ይህ ቁጥር አይታወቅም……” የሚል መልስ አገኘሁ። እኔ ስታሰር የተወሰደብኝ ስልክ ቁጥር አልተመለሰልኝም። ሁ በእኔ ቁጥር ላይም ስደውል የሚሰጠኝ መልስ ተመሳሳይ ስለሆነ ይህ ምስክር አሁን እጠቀምበታለሁ ያለው ስልክ ሲታሰር ተወስዶበት ቴሌ ቁጥሩን እንዳልለመለሰለት ግልፅ ሆነልኝ። እሱ ግን እጠቀምበታለሁ ብሎ መስክሯል። የማዕከላዊ ምስክር ከዚህ ውጭ ይላል ተብሎ አይጠበቅም።

ምስክሮቹ በዳኞችና በጠበቃ አለልኝ ምህረቱ ሲጠየቁ ” በምህረት ተፈትተናል” ብለዋል። የተፈቱበትን ቀን፣ ወርም ሲጠየቁ መልሳቸው “አናስታውስም” ነው። አልተፈቱምና የተፈቱበትን ቀን ሊያስታውሱ አይችሉም!

ተከሳሾቹም ምስክሮቹ ማዕከላዊ ታስረው እንደሚገኙ፣በእነሱ ላይ በሀሰት መስክረው እንደሚለቀቁ ቃል ተገብቶላቸው በሀሰት እንደሚመሰክሩባቸው ተናግረዋል። ሰቆቃ ደርሶበት ሱሪውን በችሎት አውልቆ ሀይላንድ የተንጠለጠለበትን ብልቱን ያሳየው ዮናስም በጠዋቱ ችሎት ምስክሮቹ ማዕከላዊ ታስረው፣ በግድ መስክሩ እየተባሉ እንደሆነ ተናግሮ ነበር። እውነታውም ይሄው ነው!

ሁለቱ ምስክሮች መስክረው ችሎት ተጠናቅቆ ስንወጣ የገቡት ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ መኪና ነበር። እስረኞች ወደሚመላለሱበት፣ እኔም በአንድ ወቅት የማዕከላዊ እስረኛ ሆኜ ወደተመላለስኩበት መኩና እንጅ አልጋ ወደያዙበት ሆቴል የሚያደርሳቸው መኪና ውስጥ አልገቡም። ጉዟቸው ጓደኞቻቸው ወደተሰቃዩበት፣ እነሱም ተሰቃይተው በሀሰት እንዲመሰክሩ ወደተገደዱበት ወደ ማዕከላዊ ነው። ዮናስ አካሉን ወዳጣበት፣ ብልቱ ላይ ውሃ ወደተንጠለጠለበት፣ ኢህአዴግ ደርግ ሲጠቀምበት ነበር ብሎ 26 አመት ሙሉ አማራ እና ኦሮሞ ወጣቶችን ወደሚያሰቃይበት ማዕከላዊ! ምስክሮች የሄዱት ተፈትተን እንኖርበታለን ወዳሉት አማራ ክልል ሳይሆን ትህነግ/ህወሓት የአማራ ወጣቶችን ብልት ወደሚሰልብበት፣ የትህነግ የጥላቻ ጥግ ወደሚታይበት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ!

የመቀሌው ስብሰባና የ’ፖለቲካ እስረኞች’ ፍቺ ( ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የመቀሌው ስብሰባና የ’ፖለቲካ እስረኞች’ ፍቺ

ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ሰዓት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ መግለጫ እየሰጡ ነው። የእስረኞችን መፈታት በተመለከተ ትላንት መግለጫ እንደሚሰጡ ስንሰማ መቀሌ ወሰነች ብለን ነበር። ምክንያቱም የእስረኞች መፈታት ወሬ ከሃይለማርያም አፍ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በህወሀት መንደር የፈጠረው መንጫጫት የተባለው እንደማይሆን ከምልክትም በላይ ነበርና ነው። ከጠቅላይ አቃቤ ህጉ የዛሬ መግለጫ ለመረዳት እንደተቻለው ግን የሚፈታ የፖለቲካ እስረኛ የለም።

ክሳቸው ተቋርጦ፡ የሁለት ቀናት ተሀድሶ ተሰጥቷቸው የሚለቀቁት 528 እስረኞች ህገመንግሥቱን ወይም ህገመንግሥታዊ ስርዓቱን የመናድ እንቅስቃሴ ላይ ያልተሳተፉ ወይም ያልመሩ፡ በከፍተኛ የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ ጉዳት ለማድረስ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ያልተሳተፉ ወይም ያልመሩ፡ የሰው ህይወት ያላጠፉ ወይም በአካል ላይ ከባድ ጉዳት ያላደረሱ የሚል መስፈርት ተቀምጦ የተመረጡ ናቸው። በአጭሩ የምንፈታው የፖለቲካ እስረኛ የለም ማለት ነው። ያለወንጀላቸው፡ ወንጀል የተለጠፈባቸው፡ ያለሃጢያታቸው ሃጢያት የተከመረባቸው፡ የፖለቲካ እስረኞች ከላይ ከተቀመጡት መስፈርቶች በአንዱ ወይም በሶስቱም የተከሰሱ በመሆናቸው የመቀሌው የምህረት ውሳኔ የሚመለከታቸው አይደለም።

በቀውስ የሚናጠው ህወሀት መፍታትም አለመፍታትም ችግር ሆኖበታል። ምናልባት መቀሌ ላይ የተሰበሰቡት ህወሀቶች ከደህንነት መስሪያ ቤቱ የተሰጣቸው ስም ዝርዝር ላይ ከውሳኔ ደርሰው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ሰጥተን ነበር። ከጠቅላይ አቃቤ ህጉ የዛሬው መግለጫ መረዳት የሚቻለው የፖለቲካ እስረኞች እንዳይፈቱ የተቀጣጠለው የህወሀት ደጋፊዎች ጫጫታ አሸናፊ መሆኑን ነው። ህወሀት የመጣበትን ውጪያዊ አደጋ ለመመከት ቅድሚያ ከውስጡ እንደቋያ እሳት የሚንቀለቀለውን የደጋፊዎቹንና አባላቱን ቁጣና ተቃውሞ ለማብረድ ጓዙን ጠቅልሎ መቀሌ ገብቷል። በእርግጥ ደጋፊዎቹና አባላቱ የሚያማቸው የሌላው ኢትዮጵያዊ ህመም አይደለም። የሚያስቆጣቸው፡ የሚያንጨረጭራቸው የነጻነትና የፍትህ ረሃብ አይደለም። ሌላው ቢቀር በሚፈቱት እስረኞች ላይ ከህወሀት ደጋፊዎች መንደር የሚሰማው ትርክት ለቅሶአችን ለየቅል መሆኑን የሚሳይ ነው።

ከመቀሌ የተለየ ነገር አይጠበቅም። የስብሰባ ጋጋታ የህወሀትን ሞት የሚያስቀረው እንዳልሆነ ይታመናል። በውስጣቸው የገባውን ትርምስ በውይይት መፍታት ስላልቻሉ ለጊዜው የተወሰኑ እስረኞችን በመልቀቅ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ የወሰኑ ይመስላል። ከፌስ ቡክ ሰራዊት እስከ ዲያስፖራ የህወሀት ክንፍ፡ ታች ወረዳ እስካለው አመራር የከተተበት የመቀሌው ግርግር የህወሀትን ዕድሜ ለማራዘም የሚቻለውን እያደረገ ቢሆንም ብዙም ውጤታማ እንዳልሆነ ሾልከው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። በሚፈቱት ሰዎች ላይ በህወህቶች መሃል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የትግራይ ሽማግሌዎች ልመና ውስጥ ገብተው እንደነበርም ይነገራል። በልመና የሚፈቱት እነማን እንደሆኑ ፍንጩን አውቀናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉ እንጂ ደጅ በመጥናት መብቱን እንደማይጠይቅ ታሪክ ምስክር መሆኑን ህወሀቶች ዘንግተውታል።

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እየጠበቀ ነው። የህወሀት ቀለብ ሰፋሪዎች ህወሀት ቃሉን እንዲያከብር በጓሮ በኩል ውትወታ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል። የዛሬውን የጠቅላይ አቃቤ ህጉ መግለጫ ከሰሙ በኋላ ምን ሊሉ እንደሚችሉ አናውቅም። ህወሀትን እያባበሉ እዚህ ያደረሱ በመሆናቸው አንድም እስረኛ ቢለቀቅ ”ጥሩ ጅምር ነው” በሚል ሊያሞካሹት እንደሚችሉ ይጠበቃል። ”እሱን ይዛችሁ ደግሞ ሌላውን ጠይቁ። ለውይይት በር የሚከፍት መልካም ውሳኔ ነው” ከሚል ጫና ጋር ምዕራባውያን መንግስታት ምላሽ መስጠታቸው የማይቀር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን መንገሽገሽ የሚመጥን እንደማይሆን ቢነገራቸው ላይገባቸው ይችላል። የእነሱ ጭንቀት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጋተው መከራና ስቃይ አይደለም። ህወሀት ተጠጋግኖ፡ አፈር ልሶ፡ እንደምንም ቆሞ በስልጣን ቢቆይላቸው ደስታቸው ወደር የለውም። ችግሩ ህወሀት ፈውስ በሌለው፡በማይድን በሽታ የሚሰቃይ ሆኖባቸው እንጂ።

#የካንጋሮው #ፍርድቤት #ወንጀለኞች #ሲጋለጹ ( ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ)

#የካንጋሮው #ፍርድቤት #ወንጀለኞች #ሲጋለጹ

«አንደኛው ዳኛ የህወሃት አባል ነበሩ»

ክፍል እንድ

የህዝብን ዉክልና ተቀብለው ህዝብና መንግስትን ለማስታረቅ የጣሩት የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ለመልካም ተግባራቸው ወሮታ እንዲሆን ህወሃት መራሹ ቡድን አስሮ አሰቃያቸው። የደረሰባቸው አካላዊ ስቃይ ተነግሮ አያልቅም። መንፈሳቸውን ሰብሮ ሽንፈትን ፈልቅቆ ለማዉጣት ህወሃት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የጨቋኙን፣የአፋኙንና የገዳዩን ህወሃት መራሽ ቡድን ሴራ የተቋቋሙት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የህወሃት ደህንነቶች በሚሾፍሩት የካንጋሮ ፍርድ ቤት ላይ በዳኞች፣በዓቃቤ ህጎች፣በሐሰት መስካሪዎች ብዙ ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። የሐሰት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል።ንጹህነታቸው በታሪክ መዛግብት ላይ ሰፍሮ ሲታወስ የሚኖር መሆኑ ሰቆቃዉን የሚያስረሳ ሐቅ ነው። የካንጋሮው ፖለቲካዊ ፍርድ ቤት ወንጀለኞች እነማን ናቸው? ዛሬ የህወሃትን ፖለቲካዊ ጉዳይ አስፈጻሚ ከሆኑት ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ሚና ምን ነበር? የማጋለጽ ስራችንን ይቀጥላል።

ፍርድ ቤቱን የሚሾፍሩት ወንጀለኛው ዳኛ አቶ ሙሉጌታ ኪዳኔ ይባላሉ።በብቃት ሳይሆን ለህወሃት ባላቸው ፖለቲካዊ ጠቀሜታ በተከበረው የዳኝነት ወንበር ላይ የተሰየሙ ናቸው። ህወሃትና የሚቆጣጠረው የደህንነት መስሪያ ቤት በተለያዩ ክልሎች እያዟዟረ ፖለቲካዊ ብያኔን እንዲያሳልፉ የሚጠቀምባቸው ናቸው። ጠበቆችን «የኔን ችሎት ካልፈለጋቹ ተዉት» በማለት እስረኞች እስር ቤት ዉስጥ ተወርዉረው እንዲቀሩ የሚያደርጉ ሰብዓዊነት የጎደላቸው ናቸው። በዘራቸው ከህወሃት ጋር የቆራኙ በመሆናቸውና የህወሃት ታማኝ ፖለቲካዊ አገልጋይነታቸው በግልጽ በችሎት ላይ የሚንጸባረቅ በመሆኑ «ህግ» ለሚለው ለተከበረው ቃል ደንታ የላቸውም።ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ሰብዓዊነትን የሚጠየፉ በመሆናቸው በብዙ ንጹሗን ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበትን ፍርድ ፈርደዋል፣ብዙ ቤተሰብን አለያይተዋል፣ እስረኞች በእስርቤት ዉስጥ እንዲሞቱ መንስኤ ሆነዋል። ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ወንጀለኛ መሆናቸውን ይፋ ማድረጉ ተገቢ ነው።

በካንጋሮው ፍርድ ቤት የወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ የዓቃቤ ህጎች፣ወንጀል መርማሪዎች፣የሐሰት መስካሪዎች፣ስልጠና የሚሰጡ የደህንነት አባልት፣ ድራማዉን ከበስተጀርባ ሆኖ በማቀነባበር ለህወሃት ሎሌ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት የፍትሕ ሚኒስቴር ድኤታው ዶ/ር ሃሺም በደም ያደፈ እጅና መርዛማ ተግባር የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ብቻ ሳይሆን መላዉ የፍትህ ስርዓትና የኢትዮጵያ ህዝብ የተጎዳበት በመሆኑ ወንጀለኞች እርቃን የማስቀረቱ ተግባር የዜጎች ሁሉ ሐላፊነት ነው።

የሙስሊም የመፍትሔ እፈላላጊ ኮሚቴዎችና አብረዋቸው የታሰሩት ሌሎች ባልደረቦቻቸው በማእከላዊ ዉስጥ አያሌ ስቃይና መከራን አሳልፈው በጥቅምት 19 ቀን 2005 በልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀረቡ፡፡ በዕለቱም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል የመናድ ሙከራ እና የሽብርተኝነት ወንጀል መፈጸም የሚል ሁለት ክሶች ተመሰረቱባቸው። በሁለቱም ክሶች ላይ ተከሳሾች «ኢስላማዊ መንግሥትን ለመመሥረት እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ በማሰብ ከ2001 ጀምሮ ሲዘጋጁ ቆይተው በ2004 ግምቱ 160 ሺህ ብር ገደማ የሆነ ንብረት እንዲወድምና ኮማንደር ግርማይ ወ/ሚካኤል የተባሉ ፖሊስ ላይ መጠነኛ ጉዳት እንዲደርስ አነሳሱ» የሚል የሐስት ዉንጀላ ታክሎበት ነበር፡፡

የሐስት ክሱን ተዓማኒነት ለማጉላት በህወሃት የሚመራው ቡድን በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሗን ብዙ የፕሮፓጋንዳ ስራ ሰርቷል።ይህንኑ ፕሮፓጋንዳ ለማመን የበቁ ሰዎች ቢኖሩም የኮሚቴዎቹ ንጹህነት ከሐስት ዉንጀላዉ የላቀና የገዘፈ ሆኖ በታሪክ ድርሳናት ላይ ሰፍሯል።ሌላው ቀርቶ ‹‹የአካል ጉዳት ደረሰባቸው›› የተባሉት ኮማንደር ግርማይ በፍ/ቤቱ ለምስክርነት ቀርበው ተከሳሾቹን እንደማያውቁ ጠቅሰዋል። በዓይናቸውም ላይ መጠነኛ ጉዳት ያደረሱባቸው ሰዎች ታስረው፣ በጳውሎስ ፍ/ቤት መስክረውባቸው በቀላል እሥራት መቀጣታቸው ይታወቃል። በፈጠራ ግጭቱን ‹‹አነሳሳችሁ›› የተባሉት የኮሚቴ አባላት ክስ ግን «ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማፍረስ እና ሽብርተኝነት» የዘለገ መሆኑ የማይታበልና ህወሃት የፈጸመው ፖለቲካዊ ወንጀል ነው፡፡

የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ለመወንጀል ብቻ ሲባል ከጅምሩ አንስቶ ጉዳዩን የማያውቁና ለዓላማ ሲባል የመጡ ዳኞች ተሰይመው ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ሀብቴ ፍቻላ (የመሃል ዳኛ)፣ አቶ ሙሉጌታ ኪዳኔ (የቀኝ) እና አቶ አዱኛ ረጋሣ (የግራ) ነበሩ፡፡ ከነዚሁ ዳኞች መካከል የመሃሉና የቀኙ ዳኛ ለሥርዓቱና ለገዢው ፓርቲ ተቆርቋሪነታቸውን በችሎት ያሳዩበት መንገድ የመንግሥት ፍላጎት ባለባቸው ተመሳሳይ መዝገቦች ላይ የዳበረ ልምድ እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነበር፡፡

ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ፖለቲካዊ ተልእኮን ለማስፈጸም የተሰየሙበት ችሎት ጭካኔና ኢሰብዓዊነት የሞላበት ስለነበር በብዙ እናቶች የእምባ ጠፈጥፍ ርሷል። ብዙ እህቶች ተንሰቅስቀው አልቅሰዋል።ሚስት የትዳር ጓደኛዋን፣ፍቅረኛዋን አብጠርጥራ የምታዉቅ ቢሆንም አሸባሪ የሚል ሸክም ተጭኖበት በካቴና ታስሮ ስታይ ቅስሟ ተስብሮ ፈጣሪ ይሰማት ዘንድ አልቅሳለች።አላለቅስም ያሉ አባቶችም የፍርድ ቤቱን ጣራ በመልከት አንድዬ ይሰማቸው ዘንድ ሲማጸኑ እምባቸው ኮለል ብሎ ወርዷል። ይህንን ሰቆቃ በችሎቱ ላይ ተሰይመው የሚመለከቱት ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ህግን ከመተግበርና እንደሰው ከመራራት ይልቅ ፖለቲካዊ አቋምን ይዘዋል።ህወሃት የሚባለውን ቡድን በስልጣን ለማቆየትና የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦ ለመግዛት ለፍትህ ስርዓቱ ተገዢ ከመሆን ይልቅ በእብሪት የተወጠሩት ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ ሰላማዊ የቤተሰብ ህይወትን በማኮላሸት ረገድ የነበራቸው ሚና የላቀ ነበር። ይህንን ከግምት ዉስጥ በማስገባት በካንጋሮው ፍርድ ቤት የተፈጸሙ አምስት አበይት ክስተቶችን ቀጥለን እናሰፍራለን።

#የሙስሊም #የመፍትሔ #አፈላላጊ #ኮሚቴዎች #የፍርድቤት #ሂደት

1. በጥቅምት 19/2005 ክስ ተመሰረተ። ከጥር 14 እስከ ነሓሴ 2005 ድረስ ለ9 ወራት ያህልበዝግ ችሎት የሐሰት ምስክር አዳመጡ።

2. ጥር 28 ቀን 2005 ”ጀሓዳዊ ሐረካት“ በሚል ዘጋቢ ፊልም መንግስት በቴሌቪዥን አቀረበ። በእለቱም በጠበቆች በቀረበ አቤቱታ ፍ/ቤቱ እንዳይተላለፍ ቢያግድም መተላለፉ ይታወሳል።

3. በታህሳስ 03 ቀን 2006 በሰጡት ብይን 10 ሰዎች ነጻ በማለት ሌሎች 18 ሰዎችን ተከላከሉ አሉ። ከመጋቢት 15/2006 ጀምሮ የመከላከያ ሰነድና ዝርዝር ገባና መከላከል ተጀመረ። እስከ መጋቢት 2007 ድረስ 152 የሰው 72 ቪድዮና በርካታ ሰነዶችን ቀርበው መከላከሉ ቀጠለ።

4. በመጋቢት 2007 የሰማያዊ ፓርቲ እና የሙስሊሙ እንቅስቃሴ በምርጫው ላይ አብዮት ሊያነሱ ተስማምተዋል የሚል መረጃ የደህንነት ቢሮ አገኘሁ በማለቱ ስጋት ላይ ወድቀናል ተባለ። በዚህን ጊዜ ከምርጫ በፊት ቶሎ የፍርድ ሒደቱ እንዲጠናቀቅ ብለው ለቀድሞ የፍትህ ሚኒስቴር ደኤታ ዶ/ር ሓሺም ቶውፊቅን፣አቶ ሐብቴ ፍቻላ እና አቶ ሽመልስ ከማል ተነገራቸው። ከተወያዩ በሗላ ወዲያውኑ በከፍተኛ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዜዳንት አቶ ሃብቴ ፍቻላ አማካኝነት ለአቶ ሙሉጌታ ኪዳኔ ተነገረ፣ የመሃል ዳኛ የነበረው አቶ ሙሉጌታ በችሎት በመገኘት ገና የመከላከያ ምስክር ተሰጥቶ ሳያልቅ ለጠበቆች በአንድ ሳምንት ውስጥ የክርክር ማስቆሚያ አስገቡ፣ በ15 ቀን ውስጥ ውሳኔ እንሰጣለን አሉ። ጠበቆች የኮምፒውተር የባለሞያ ምስክርነት አልተሰማም በፍ/ቤት ትዕዛዝ የሚመጡ ሰነዶች አልመጡም፣ የክርክር ማቆሚያ ለማስገባት ቢያንስ ከአንድ ወር እስከ 45 ቀናት ያስፈልግናል አሉ። ዳኞቹ እስከ መጋቢት 30/2007 ድረስ የክርክር ማቆሚያ ይግባ ሲሉ ጠየቁ።ግዜ ያንሰናል ብላችሁ ነበር እስከ ሚያዚያ 30 ድረስ ጨምረንላችኋልም አሉ ዳኞቹ። ከዚያም ለሰኔ 27 ተራዘመ።

5. የፍርዱን ጹሁፍ የጻፉት አቶ ሽመልስ ከማልና አብራዋቸው የተመደቡት ሁለት ሰዎች መሆናቸው ታውቋል። የአቶ ሽመልስ የእጅ ጹሁፍ በመቀበል በራሳቸው የእጅ ጹሁፍ የጻፈፉት የቀኝ ዳኛ ሆኖ በመጨረሻ የተሰየሙት ህወሃቱ አቶ ሙሉጌታ ኪዳኔ ነበሩ።

የህዝበ ሙስሊሙን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴን አስሮ፣ማእከላዊ አስገብቶ፣መርምሮ ካንጋሮ ፍርድ ቤት አቅርቦ በሐሰት ፖለቲካዊ ፍርድ እንዲሰጥ በርካታ የህወሃት ባለስልጣናት፣የህወሃት ተባባሪዎች፣የህወሃት ሎሌዎች፣የመጅሊስ ተመራጮችና ሌሎችም ተሳትፈዋል። እጃቸው በወንጀል ያደፈ ወንጀለኞች ብዙ ናቸው። ነጻነት የተጠማው የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህን የሰው ቆዳ ለብሰው ሰው መሆን የተሳናቸውን ጨካኝ ወንጀለኞች አብጠርጥሮ ሊያዉቅ ይገባል።

ልክ አምባገነናዊው መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ አቶ በረከት ስሞን ብሔራዊ የሐዘን ስነስርዓት ማዘጋጀታቸው አይዘነጋም። ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በህወሃት የሚመራው የሽብር ቡድን በመላኒየም አዳራሽ እስረኞችን የመቀበል ብሔራዊ በዓል ለማዘጋጀት ያደረገው ሙከራ ተጋልጿል።ህወሃት እራሱ ለፖለቲካ ፍጆታዉ ያስረቸውን ሰዎች ሲፈታ ብሔራዊ እስረኛን የመቀበል ስነስርዓት በማለት የሚያዘጋጀው ድግስን አስቀድሞ ማስተዋሉና ሊያገኝበት የሚሻዉን ፖለቲካዊ ትሩፋት ማወቁም ግድ ነው።

የካንጋሮውን ፍርድ ቤት ወንጀለኞች የማጋለጹ ስራ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ሊቀጥል ይገባል የሚል አቋም አለን። ልብ ያለው ልብ ይበል።ይቀጥላል..

ለቅሶዬን መልሱ! (የ5ደቂቃ ንባብ)( በጦማሪ በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

ለቅሶዬን መልሱ!
(የ5ደቂቃ ንባብ)

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአደባባይ ሁለት ግዜ አልቅሻለሁ። ወይም ለቅሶ ሞክሮኛል ብል ይሻላል። ሁለቱም በአንድ ምክንያት ነው። የመጀመሪያው፣ ሕዳር 2008 ነው። ገና ዓመት ከስድስት ወር ታስሬ የተፈታሁ ሰሞን ነበር። ሰመጉ የሰብኣዊ መብቶች ቀንን እያከበረ ነበር። ድንገት እስኪ ገጠመኝህን ተናገር ተብዬ እንደጀግና መድረክ ላይ ተንደርድሬ ወጣሁ። በፈገግታ አንድ ዓረፍተ ነገር ከተናገርኩ በኋላ በሳግ ሁለተኛው ተቋረጠ። ልቀጥል ስል ሌላ ሳግ። ልቀጥል ስል ሌላ ሳግ። መድረክ መሪው “ከዚህ በላይ አስረጂ ንግግር የለም” ብሎ ብሎ ወደ ወንበሬ መለሰኝ።

ከ3 ዓመት በኋላ ሰሞኑን መንግሥት “ማዕከላዊ ሊዘጋ ነው። ሙዚዬም ሊሆን ነው” ብሎ አወራ። የቻይና ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትዎርክ (አፍሪካ) ጋዜጠኛ የማዕከላዊ ትዝታዬን ጠየቀችኝ። የት እንደደበቅኩት የማላቀው እምባ ባይኔ ካልወጣሁ አለ። ምላሴ ተሳሰረ። እንግሊዝኛው ጠፋ። አማርኛ አስናፈቀኝ። የማዕከላዊን ገብስ ገብሱን እየሳቅኩ ሳወራ የኖርኩ ሰው፣ በሐሳብ ተመልሼ ገባሁ። በቀላል ቋንቋ በሳግ መልስ ሰጠሁ።

ባለሥልጣኖቻችን ኮሜድያን ናቸው። ማዕከላዊ የሚዘጋው ‘ደርግ የማሰቃየት ተግባር ይፈፅምበት ስለነበር ከዚያ ትዝታ እንዲላቀቅ ለማድረግ ነው’ አሉ። ይህም አልበቃቸውም። ኮማንደር መብራህቱ የተባሉ ሰው በጋዜጠኛ ሲጠየቁ ‘ቦታው ለቢሮ ሥራ ስለጠበበ ወደተቀያሪ ቦታ ዝውውር አድርገናል’ አሉ። የፖለቲካ ክንፉ በፕሮፓጋንዳ ሊያተርፍበት የፈለገውን ጉዳይ የፀጥታ ኃይሉ ሳያውቅ አጋልጦታል።

ኮሜድያኑ በብዛት ትራጄዲያን ናቸው። እየዋሹ በሐዘንም በደስታም ያስለቅሱናል። እኛም እንታለላን። አንዳንዴ አውቀን ነው የምንታለለው። አለበለዚያ ሕይወታችን ደረቅ እዬዬ ይሆናል። ባለፈው ሳምንት ከማዕከላዊ መዘጋት በላይ አስደሳች የሚመስለው ዜና የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ዜና ነው። እምባ የሚያመጣ ዜና ነበር። የደስታ። ከዚያ በላይ እምባ የሚያመጣው ግን ማንን ፈተው ማንን እንደሚያስቀሩ፣ መቼ ወደተግባር እንደሚፈፅሙት ባለማወቅ በተስፋ ጭንቀት የሚብሰለሰለው የእስረኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በቃል ያሉት እንዲህ ነበር፦ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ በዐቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው እና ጉዳያቸው በመታየት ላይ በሚገኙ የፖለቲካ አመራሮችም ሆነ ግለሰቦች […] ክሳቸው ተቋርጦ እንደዚሁም ደግሞ ምኅረት ተደርጎላቸው” ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መሠረት ይፈታሉ። ይህ በመሠረቱ ሁሉም እስረኞች (የፖለቲካዎቹን ብቻ ሳይሆን ደረቅ እስረኞችን ጨምሮ) ይፈታሉ ከማለት አይለይም። ሁሉም እንዳልሆኑ እንዳናስብ “አንዳንድ” የሚል ቃል ተጠቅመዋል። አንዳንዶቹ እነማን ናቸው የሚለውን ግልጽ ለማድረግ ደግሞ የሚፈቱበትን ምክንያት ማየት ያስፈልጋል፦ “አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ይበልጥ ለማስፋት”። የደረቅ ወንጀለኞች መፈታት ለአገራዊ መግባባትም ይሁን ለፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት ፋይዳ ስለሌለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለፖለቲካ እስረኞች ማውራታቸው እንደሆነ ያለጥርጣሬ ማመን ይቻላል። “የፖለቲካ እስረኞች” የሚለውን ቃል ሲክዱት የኖሩትን ነገር ከማጋለጡም ባሻገር፣ ራሳቸውን ወደመወንጀል ስለሚያመራባቸው ቃሉን የጠሉበትን ምክንያት እንረዳለን። መረዳት የማንችለው የገቡትን ቃል ወደተግባር ለመቀየር ምን እንደቸገራቸው ነው።

በፌዴራል ደረጃ የፖለቲካ ክሶች መደብሮቹ – የልደታ ምድብ 4ኛ እና 19ኛ ችሎቶች ናቸው። እነዚህ ችሎቶች ይህ ብዙዎቻችንን በደስታ እምባ ያስተናነቀ ዜና ከተሰማ በኋላ ብቻ ከ30 በላይ ሰዎች ላይ ፍርድ አስተላልፈዋል። ጭራሽ በችሎት መድፈር ትልልቆቹን ፖለቲከኞች ሳይቀር የእስር ብይን አሳልፈውባቸዋል። የደስታ እምባን በሐዘን እምባ ማበስ ማለት ይሄ ነው። ቃል የተገባው ፍቺ ያለጥርጥር የሚመለከታቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ኦቦ በቀለ ገርባ ከነዚህ “የችሎት መድፈር ፍርደኞች” አንዱ ሆነዋል። በአሸባሪነት ተከሰው ከቀረበባቸው ማስረጃ አንዱ በኦሮሞ ስተዲስ አሶሲየሽን መድረክ ላይ ስለሠላማዊ ትግል አስፈላጊነት ያደረጉት ንግግር ነው። ዳኞች “ማስረጃው ለሽብር ክስ አይበቃም፤ በንግግር አመፅ የማነሳሳት ሙከራ ነው” በሚል ክሳቸው ከሽብር ወጥቷል። በወንጀል ሕጉ 257/ሀ መሠረት ክሳቸው ሲቀጥል ደግሞ በዋስ መውጣት ነበረባቸው። ተከልክለው፣ ይግባኝ ብለው፣ 30ሺሕ ብር ተፈቅዶላቸው፣ ከፍለው፣ ታግዶባቸው… በግዞት የተያዙ የፖለቲካ እስረኛ ናቸው። እኚህ ሠላማዊ ፖለቲከኛ ታዲያ አሁን የመንግሥት ቃል ሲፈፀም የትላንቱ ፍርድ ይነሳላቸዋል ወይስ እንደደረቅ ወንጀል ሊቆጠር ነው?

ወይ ሁሉንም ፍቱ፣ አልያም ለቅሷችንን መልሱ!

የህወሓት የበላይነት አለ! የትግራይ የበላይነት ከወዴት አለ? (በጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ)

የህወሓት የበላይነት አለ! የትግራይ የበላይነት ከወዴት አለ?

በጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ

“አለ፣ የለም” ከሰሞኑ ያየሁት ክርክር ነው። የማያከራክር ጉዳይ ቢሆንም ሰዎች የህወሓትን የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የመንግሥት ተቋማት ስልጣንና የኢኮኖሚ የበላይነትን እየዘረዘሩ የትግራይ የበላይነት መኖሩን ለማስረዳት ሞክረዋል።

#Ethiopia : እስኪ ቀላል ጥያቄዎችን በመጠየቅ ልጀምር:: ህወሓቶች እንደ ፓርቲ፣ እንደ ቡድን እና እንደ ግለሰብ ከሚፈጽሙት ተግባር ተጠቃሚውና ተጎጂው ማን ነው?
በጠመንጃቸውና በስልጣናቸው ከሚያስሩት፣ ከሚያሰዱድትና ከሚገደሉት አበዛኛው ቁጥር ወይም የጥቃቱ ሰለባ ማን ነው?

እነርሱ ከሚገነቡት ኢኮኖሚ ተጠቃሚው ማን ነው? ለምሳሌ በትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት ከሚሰሩ ልማቶች ማን ይጠቀማል?
ህወሓትም ሆነ ድርጅቱ የተቋቋመው ለትግራይ አለያም ትግራይን መልሶ ለማቋቋም እንጂ ኢትዮጲያን እንደሀገር ለማቋቋም እንዳይደለ በግልጽ ተቀምጧል።

ከ6 ወር በፊት የትራክተር ፋብሪካ መቀሌ ላይ ስራውን ሲጀምር የትግራይ መልሶ ማቋቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወይዘሮ አዜብ መስፍን “በትግራይ መልሶ ማቋቋም ስር የሚገኙ ተቋማት ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት እየደገፉ ናቸው” ብለዋል። ድርጅታቸው ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ እንድትሸጋገር አስቦ ከሆነ ፋብሪካዎቹን ለምን ትግራይ ላይ ብቻ መገንባትን መረጠ?
“ሀገሪቱ” የሚሉት ፋብሪካዎቹ ጥሬ እቃዎችን ከሌሎች ክልሎች ስለሚጭኑ ይሆን? አሰታውሳለሁ አቶ መለስ ዜናዊ በሞቱ ማግስት ወይዘሮ አዜብ ጥቁር ለብሰው “መለስ ትግራይን የኢንዱስትሪ ማእከል አደርጋለሁ ብሎ የጀመረውን እቅድ ከግብ ሳያደርስ መሞቱ ይቆጨኛል” በማለት የመለስን ራዕይ እውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር። ቃላቸውንም እያከበሩ እንደሆነ በተግባር እያየን ነው።
ባለፉት እንድ ዓመት ከግማሽ ብቻ የትምህርት፣ ወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ፣ ኬሚካል ፋብሪካ በኢትዮጲያ የመጀመርያው ሲሚንቶ፣ መኪና መገጣጠሚያ፣ ትራክተር መገጣጠሚያ፣ ሌዘር ፋብሪካ፣ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካና ሌሎች ልማቶች በትግራይ ተከናውነዋል። ጥቂቶቹ ደገሞ በቅርብ ይጠናቀቃሉ ተብሏል። መረጃዎቹን ከነ ቀናቸው አስቀምቻለሁ፣ ምስላቸውም ከታች ተያይዟል።

ከነዚህ ፋብሪካዎች የሚጠቀመው ማን ነው? ሠራተኞች የሚቀጠሩት ከየት ነው ገቢውን የሚያገኘው ማን ነው ?
በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ግዙፍ ኩባንያዎችና እርሻዎች በአጠቃላይ ስልጣናን ኢኮኖሚው የነጮች ነበር። በዚምባብዌም እንደዛው። በዚያ የግፍ አገዛዝ ሁሉም ነጮች ተጠ ቃሚ ባይሆኑም የነጭ የበላይነት መኖሩ እሙን ነበር። በአሜሪካ የጥቁሮች የነፃነት ትግል ወቅት ከነ ማርቲን ሉተር ኪንግና ማልከም ኤክስ ጎን የተሰለፉ ጭቆናን የተጠየፉ ነጮች ነበሩ። ዛሬም ከጥቁሮችና ስደተኞች ጎን የሆኑ ነጮች ሚሊየን ናቸው። ያ ማለት ግን የነጭ የበላይነት የለም ብሎ ለመከራከር የሚያስደፍር አይደለም። ነጮች ሁሉ ተጠቅመዋል ማለትም አይደለም።

ስለዚህ ህወሓት ስንል የምናወራው ስለ ትግራይ ነፃ አውጪ ነው። ህወሓት ደግሞ ትግሬ ነው። ለፖለቲካ ትክክለኝነት ሲባል “NO የህወሓት የበላይነት እንጂ የትግራይ የበላይነት የለም” ተብሎ ቢነገር እንኳ በሌላ ቋንቋ የትግሬ የበላይነት አለ ማለት ነው። የበላይነቱ በስልጣንና ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በሥነልቡናም ጭምር ነው። ባለፉት 27 ዓመታት “ቧይ” የሚለው ቃል ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ወይም ትግርኛ አነጋገር ዘዬ እንዲኖረው ያልተመኘ፣ ግንባሩ ላይ ምልክት እንዲኖረው ያልተመኘ ማን አለ? ያለስጋት ለመኖር ሲባል። እውነቱን ለመናገር ባዶ የስልጣን ስም ከተሰጣቸው በርካታ የሌላ ብሔር ተወላጆች ይልቅ ይህ ቃል (ቧይ) ኃይል ነበረው::

ትግሬዎች “ለምን ‘የትግራይ የበላይነት አለ’ ተባለ” ብሎ በንዴት ከመጦፍ ይልቅ በርግጥ ህወሓት የማይወከላቸው ከሆነ “በትግራይሕዝብ ስም የሚነግደው” ድርጅት ላለፉት 27 ዓመታት ሌላውን ኢትዮጲያዊ በጠላትነት ፈርጆ በዘሩ፣ በኀይማኖቱ እና በፖለቲካ አመለካከቱ ሲያሳድድ፣ሲያስርና ሲገድል ስለምን ዝምታን መረጡ? 27 ዓመታት በሙሉ!
ህወሓት ለ17 ዓመት” ደርግ…” እያለ አነሳስቶ ለስልጣን በቃ:: ታዲያ ለምን ለ27 ዓመታት እስካሁን “ደርጊ” እያለ ጭራቅ ይስልብኛል ብሎ የጠየቀ ስንት ነው? ካድሬዎች የትግራይ ሕዝብ ከሌላው እንዲነጠል ድልድዩን ለዓመታት ሲያፈርሱ “ጀጋኑ” ከማለት በስተቀር “በቃችሁ” ያላቸው አለ ወይ? ከዚያ ይልቅ ሠላም ባስ ሲቃጠልና “ከመተማና መቱ ትግሬዎች ተፈናቀሉ” ብለው ዘመቻ ማድረግና እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቅን መርጠዋል።
አሁንም የኢትዮጲያ ሕዝብ “እያንዳንዱ ትግሬ ተጠቃሚ ነው” ብሎ አያምንም። ሁሉንም ላበልጽግ ቢባል ኢኮኖሚውም አይፈቅድም:: ምስኪን የትግራይ አረሶ አደሮች፣ ምስኪን ትግሬ ወገኖች በየቦታው እንዳሉ ያውቃል። ነገር ግን ከሌላው የተሻለ ነገን ያለመ ሥራ በህወሓት ወይም ትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት እየተሰራ እንደሆነ ጠንቅቆ ይረዳል:: ምን እየተከናወን እንደሆነ ያገናዝባል:: በፍርሀት ዝም ቢልም ቂል ነው ተብሎ እንዳይታሰብ::
ረጅም የኢንዱስትሪ እቅድ አስቀድሞ የታቀደው ለዘለቄታዊና አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሠረት ተብሎ ነው::ይህ የአደባባይ ምስጢር እንጂ ድብቅ እውነት አይደለም። በዚህ ዓመት (2010ዓም) ብቻ የተሰሩት 5 ፕሮጀክቶችን ከታች ማየት በቂ ነው። የ27 ዓመታቱን ለማቅረብ ጊዜ እንጂ የተለየ ምርምር አይሻም።
የህወሓት የበላይነት አለ:: ህወሓት ደግሞ የትግራይ ክልል ተወካይ ድርጅት ነው። የክልሉ ሕዝብ ደግሞ ትግሬ ነው። ስለዚህ የትግሬ የበላይነት አለ!
“አይ ድርጅቱ የትግራይን ሕዝብ አይወክልም” ብሎ የሚያምን ካለ ከቄሮና ፋኖ ጋር ሆኖ ይህን ከፋፋይ አረመኔ ስርዓት “በቃህ!” ለማለት የፍትሕና ዴሞክራሲ ትግሉን መቀላቀል እንጂ የአንድ ሰውን የእድሜ ዘመን እኩሌታ ያህል አግጥጦ የሰነበተን ሀቅ መካድ አያዋጣም። ከዚያ ሁላችንም እኩል ኢትዮጲያዊ እንሆናለን!

መቀሌ
——–
1.የእንግሊዙ ኢንትሬድ ኩባንያ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ሊሰማራ ነው (ታህሳስ 30፣2010 ፋና)

2.መሰቦ ሲሚንቶ የ70 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራረመ (ታኅሳስ 29-2010 ሪፖርተር)

3. በ75 ሚሊየን ብር በአዲስ መልክ የተገነባው የአፄ ዮሃንስ አራተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተመረቀ (ታህሳስ 20፣ 2009 ፋና)

አስገደ ፅምብላ ወረዳ
———————-
4.የመሊ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ ወደ መደበኛ ምርት ገባ (ታህሳስ 24፣ 2010)

ውቅሮ ከተማ
————-
5.ሼባ ሌዘር በ10 ሚሊየን ብር ያስገነባውን የእጅ ቦርሳ ማምረቻ ፋብሪካ አስመረቀ መስከረም 23፣ 2010 ፋና

6.መስፍን ኢንዱስትሪያል በውቅሮ ያቋቋመውን የትራክተር መገጣጠሚያ አስመረቀ (ሃምሌ 16፣ 2009 ፋና)

ዓራቶ (ከመቀሌ በስተምስራቅ 25 ኪሎሜትር)
——————————————
7.በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ በ5 ቢሊየን ብር ሊገነባ ነው (መጋቢት 16፣ 2008 ፋና)

8. የትግራይ መልሶ መቋቋም አስር ዘመናዊ አንቡላንሶችን ለወረዳዎች አስረከበ (ጥር 20/2009 ኢዜአ)

የትግራይ የበላይነት ጉዳይ (ቀለል ባሉ ምሳሌዎች!) (ጌታቸው ሺፈራው)

የትግራይ የበላይነት ጉዳይ (ቀለል ባሉ ምሳሌዎች!)

(ጌታቸው ሺፈራው)

ለሀገር ሲባል ተሸፋፍኖ ሲታለፍ የኖረ ሀቅ ሞልቷል። እንዳላየህ ስታልፈው ሀፍረት የሚሰማው ሲጠፋ ግን አፍርጦ መነጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው። ለወደፊት ግንኙነት የሚጠቅመው ይሄ ነው። የትግራይ የበላይነት የለም የሚሉ ሰዎች አብዛኛዎቹን በደሎች፣ ለዚህ የበላይነት ምክንያት የሆኑ ሀቆች መስማት የማይፈልጉ ከበላይነትም በላይ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ናቸው። በእየ አካባቢያችን ያሉትን ሀቆች በግልፅ ብናወራ ትህነግ/ህወሓት የቀደዳቸውን ቦዮች ያለ ገደብ የሚጠቀመውን፣ የሚዘርፈውን፣ የሚዘልፈውን መጥቀስ እንችላለን። እኔ የተወሰኑትን ቀላል ምሳሌዎቹን ብቻ ልጥቀስ።

~ እኔ ለመጀመርያ ጊዜ ስራ የጀመርኩበት፣ በኋላም መለስ ላይ ፃፍክ ተብዬ በትህነግ/ህወሓት ካድሬዎች የተባረርኩበት ኢመድኤ /INSA ከነበሩት 8 ዳይሬክቶሬቶች 6 በትግራይ ልጆች የተያዙ ነበሩ። ዋና ኃላፊው ደግሞ ሜ/ጀ ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ ነው። ተክለብርሃን ወ/አረጋይ በቅርቡ የትግራይን የበላይነት ለማስቀጠል ምን መደረግ እንዳለበት በይፋ የተናገረው ጀኔራል ነው። ኢመድኤ/INSA ቢያንስ ከ80 በመቶ በላይ የሆኑ የትግራይ ልጆችን ይዞ ስራ የጀመረ ተቋም ነው። የአሁኑ ኦህዴድ ሰው አብይ አህመድ እና መሰል ሰዎች ግፊት ከየ ዩኒቨርሲቲው መቀበል ሳይጀመር አብዛኛዎቹ ሰራተኞች ከመቀሌው የቴክኖሎጅ ተቋም የመጡ ነበሩ።

~ ኢመድኤ እያለሁ ከጓደኛዬ ሚሊዮን ጋር ለህክምና ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሄድን። ኢመድኤ/INSA ሰራተኞቹን ጦር ኃይሎች ስለሚያሳክም ነው። ከበር ጀምሮ፣ እስከ ዶክተሩ አብዛኛዎቹ ሰራተኞች የሚያወሩት ትግርኛ ነው። ይህን ሄዶ ማረጋገጥ ብቻ ነው።

~ አንድ የቀድሞ የፖሊስ አባል ጋር ካፌ ቁጭ ብለን እያወራን ነው። ከመልቀቁ በፊት ይሰራ የነበረው ሜክሲኮ ከሚገኘው ዋና መስርያ ቤት ነው። ለምን ለቀቅክ ስል ለጠየኩት ጥያቄ “ትግርኛ ስለማልችል” ብሎ ነበር የመለሰልኝ። ቢያጋንነውም ምን ለማለት እንደፈለገ ግን ግልፅ ነው።

~ እኔ እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት የቂሊንጦው ኃላፊ ተክላይ፣ የሸዋሮቢት እስር ቤት ኃላፊ የማነ፣ የዝዋይ አሰፋ ኪዳነ፣ የቃሊቲው ገብረየሱስ ነበሩ። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋናም የትህነግ/ህወሓት ታጋይ ነው። የየዞኑ ኃላፊዎች የትህነግ ታጋዮች ናቸው። ለምሳሌ የቂሊንጦ ዞን ኃላፊዎች ልዕላይ፣ ካህሱ፣ ኃይላይ… … ናቸው። የጥበቃና ደህንነቱ ገ/ማርያም ወልዳይ ነው። ሌላው ቀርቶ እስር ቤት ውስጥ ለእነዚህ ኃላፊዎች መረጃ የሚያቀብሉት፣ አሁን በቃጠሎው በተከሰሱት ላይ የሚመሰክሩት አብዛኛዎቹ የትግራይ ልጆች ናቸው። ማዕከላዊ በነበርኩበት ወቅት የአማራና የኦሮሞ ልጆችን አምነው የሌሊት ተረኛ አያደርጓቸውም። ደግነቱ የማዕከላዊ ጠባቂ ፖሊሶች እንደሚታሰበው ክፉዎች አይደሉም።

~ በአንድ ወቅት ሰብሰብ ብለን ወደ ቂሊንጦ አቀናን። ሳሙኤል አበበ አይኑ ጥግ ምልክቶች አሉበት። የትግራይ ሰው ነው ያለው የቂሊንጦ ፈታሽ በትግርኛ አዋራው። ሳሙኤል ትግርኛ እንደማይችል ሲገልፅለት “በቋንቋህ ለመናገር ታፍራለህና አላስገባህም” አለው። ሳሙኤል መግባት ነበረበትና አንዱ ጓደኛችን ዘቡን በትግርኛ አዋራው። ሳሙኤል አዲስ አበባ ስላደገ ትግርኛ እንደማይችል ገለፀለት። ደስ እያለው አስገባን። በዚሁ እስር ቤት የኦሮሞ ልጆች ጠዋት ወደ ፍርድ ቤት ሲጠሩ “ጅራ” ሲሉ ታጋዩ ሁላ ደሙ ይፈላል። ኦሮምኛ የማንችለውም የእነዚህን ሰዎች ደም ለማሞቅ “ጅራ” እንል ነበር። ታጋዮቹ “አንተ ደግሞ ምን አውቀህ ነው?” ይሉናል።

~ ብርሃነ ፀጋዬ የትህዴን ታጋይ ነበር። ሞላ አስግዶም ከተመለሰ በኋላ እሱም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ከሰሱት። አንድ ቀን ያመውና ትርሃስ ጋር ይሄዳል። ትርሃስ የቂሊንጦ እስር ቤት ነርስ ነች። ትርሃስ ብርሃነን እየመዘገበች ነው። የተወለደው አድዋ ነው። ፆታው ፣ እድሜው፣ “ብሔሩ”………ተመዘገበ። በመጨረሻ የተከሰሰበት “የወንጀል አይነት” ይጠየቃል። ብርሃነ “ሽብር” ብሎ መለሰ። የትግል ልምዷ ተቆጥሮላት ቂሊንጦ የተመደበችው ትህራስ ደሟ ፈላ፣ እስክርቢቶዋን ጠረጴዛ ላይ ጣለች፣ ብርሃነ ላይ አፈጠጠች። “ትግሬ ሆነህ እንዴት ታሸብራለህ?” ብላ አንባረቀችበት። ፖሊስ ሆስፒታል ሄዶም ተመሳሳይ ደፍ አፈላ። ህክምና ተከለከለ። እነዚህ “የህክምና ባለሙያዎች” ትግሬ ምን አንሶት” ያሸብራል? ” ምን ብሎ ያምፃል? ሀገሩ፣ ስርዓቱ ሁለመናው የእሱ አይደለምን? ማለታቸው ነውኮ! ማረጋገጥ የሚፈልግ ቂሊንጦ ዞን 3 ብሎ ይግባ፣ ብርሃነ ፀጋዬ ብሎ ያስጠራ፣ ጠይቆም ያረጋግጥ።

~ አንድ ቀን እኔም ትህራስ ጋር ሄድኩ። የተከሰስኩበትን ጠየቀችኝ። ነገርኳት። “ሽብር” ብዬ። ወዲያውኑ የጠየቀችኝ “አማራ ነህ ኦሮሞ” ብላ ነው።

~ከትህራስ የተለየች አንዲት ታጋይ ነርስ አለች። ከመታሰሬ በፊት የሸዋስ አሰፋ ነግሮኝ ነበር። ማዕከላዊ ነው የምትሰራው። የአማራና የኦሮሞ ልጆች እንደሚቀጠቀጡ ታውቃለች። ቀጥቅጠው እሷ ጋ ነው የሚልኳቸው። ደረጀ አለሙን የማዕከላዊ ሰዎች ግንባሩን ፈለጡት። ልክ እንደደረጀ የአማራና የኦሮሞ ልጆች ሲፈለጡ፣ ሲቀጠቀጡ የምታውቀው የትህነግ ታጋይ የገባትን ሌሎች ቢገባቸው መልካም ነበር። “እዚህ ሀገር ግን እንደ ደቡብ አፍሪካ ዘር እየተለየ ማጥቃት ተለመደ?” አለችው ደረጀን። ደረጀ ተጠቂ ነው አይመልስላትም። ሀቁ ግን ዘር ይለያል። ግልፅና ቁልጭ ያለ ሀቅ ነው! እንደዚች ሀኪም ብልጭ የሚልለት ጥቂት በመሆኑ የተፈጠረውን የአስተሳሰብ ችግር መቅረፍ አልተቻለም።

~ ይህ ደግሞ ቴሌ ውስጥ የሚሰራ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ነው። አብራቸው የምትሰራ የትግራይ ሰው ነበረች። ሰው የትግራይ ሰውነች ብሎ በቀላሉ የሚለያት ሰው ነች። በሄደችበት አገልግሎት መስጫ ሁሉ መንገድ ይለቀቅላታል። እሷ ይህን አልፈለገችው። “አዲስ አበባ ዘረኛ ከተማ ነው” ብላ ወደመቀሌ ተመለሰች። ይህን ዘረኝነት፣ ፍርሃት፣ ስጋት፣ የትግራይ ሰዎችን አለማመን ማን ፈጠረው የሚለው ግልፅ ነው። ማረጋገጥ ከፈለክ ካፌ ውስጥ፣ ታክሲ ውስጥ ትግርኛ ጮህ ብለህ አውራ! ብዙ ሰው ዞሮ ያይሃል፣ ይጠራጠርሃል፣ ይፈራሃል። የዛሬው መፈራት፣ መጠላት ከየት መጣ ብሎ የሚጠይቅ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ ነኝ ባይ የለም። መሸፋፈን ነው! ተጨማሪ ጥቅም፣ ተጨማሪ ስልጣን ፍለጋ ነው!

~ አንድ በወልቃይት ጉዳይ የታሰረ ሰው ቤተሰብ ሰነድ ይፈልግና ወደ አንድ ትልቅ መስርያ ቤት ይገባል። መጨረሻ ግን ሰነዱ ታየ። የአማራ ማንነት አስመላሽ ግለሰብ ሰነድ ነው። በትግርኛ ተጠቅሞ ገባ፣ ሰነዱ የማን እንደሆነ ሲታወቅ ግን “ውጣ” ተባለ። “አሁንም ወደ ቂሊንጦ የምገባው ይችን ቋንቋ ተጠቅሜ ነው” ብሎኛል! “ጠቃሚ” ቋንቋ አለ!

~ ተስፋዬ ዋቴ ነው። የወጣለት አጭበርባሪ ነው። ቂሊንጦ ዞን 2 እያለሁ እኔ የነበርኩበት 5ኛ ቤት አስተዳደር ነበር። ሀኪሞቹን በትግርኛ አዋርቶ ከሌላው ቀድሞ መድሃኒት ተቀብሎ ይመለሳል። ዝዋይ ስቃይ ቤት ሆነን ሳሙና የነበረው ብቸኛ ሰው እሱ ነበር። ያመጡለት ታጋዮቹ ናቸው። ትግርኛ ይናገራልና! እሱም በትግርኛው የባለስልጣን ዘመድ ነኝ ብሎ ያጭበረብራል፣ በትግርኛው ታጋዮችን የፈለገውን ይቀበላቸዋል።

~ስለ ደህንነቱ፣ ስለ መከላከያው፣ ስለ መሰረተ ልማት፣ ስለ ጦር ኃይሉ ስብጥር፣ ስለ መርማሪዎች፣ ስለ ኢፈርት ሀብት፣…… የሚታወቅ ነው። እንዲያው ቀላል ምሳሌዎች ይሻላሉ ብየ ነው። ግልፅ ያደርጉታል ሁኔታውን። ሀቁን እናውራ ከተባለ የትህነግ ሰዎች ከላይ እስታች የራሳቸውን ሰዎች ነው የሚቀጥሩት።በአካባቢ ይመርጣሉ፣ በቋንቋ ይመርጣሉ። በሌሎች አካባቢዎች ካሉ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በላይ የ”ቐ” ትስተካከል ጥያቄ መፍትሄ ያገኛል። ኃላፊ ከተባለ አማራ እና ኦሮሞ በላይ የትግራይ ሰው በምክትልነት ይሰማል! ቋንቋው ያግዛል!

~ትህነግ/ህወሓት ሲተች “የልጆቻችን ደም ላይ” የሚል ትግርኛ ተናጋሪ ብዙ ነው። ትህነግ/ህወሓት በሌላ ህዝብ ላይ በደል ሲፈፅም ተው የሚለው በጣም በጣም ጥቂት ነው። አትንኩት እያለ፣ ሲረግጥ ዝም እያለ “ህዝብና ፓርቲን ለይ” ለማለት ከባድ ሆኗል።

~ትህነግ/ህወሓት የአማራና ኦሮሞ ወጣቶችን ሲያኮላሽ፣ ህዝብ ሲሰድብ፣ ሲዘርፍ ያልወቀሰ፣ ሲተች “ህወሓት የልጆቻችን ደም ውጤት ነው” እያለ ሲከላከል የቆየ፣ የህወሓትን የበላይነት፣ የህወሓት አድሎ፣… አብሮ መጋራት የግድ ሊለው ነው። የአማራ ህዝብ ግንቦት 7፣ የኦሮሞ ህዝብ ኦነግ ነው እያለ ሲከስ ከርሞ፣ “ወያነን አትንኩብኝ” ሲል ከርሞ አሁን የትህነግ የበላይነት፣ የትግራይ የበላይነት ነው ሲባል ማመን ይከብደዋል። ጆሮ ዳባ ልበስ ነው ነገሩ። አሁንም የሚፈልገው ሌላ ጥቅም፣ ሌላ ስልጣን……ሌላ!

እንግዲህ ትህነግ የትግራይን ህዝብ በሙሉ ወርቅ ሊያነጥፍለት የሀገር ሀብትም አይችልም። ቢችል እንኳ እወክለዋለሁ በሚለውም ህዝብ መካከል ልዩነት ያደርጋል። አድዋ እና ተንቤን እንኳ እኩል አይታይም። በትግራይና በሌሎች ክልሎች መካከል ግን ግልፅ የሆነ ልዩነት ተፈጥሯል። ትግርኛ መናገር ጥቅም ሲያስጠብቅ አልኖረም ማለት አይቻልም።

~ሀቅ የሚፈልግ የትም መሄድ አይጠበቅበትም። ደፋር ካለ ሰብሰብ ብለን ጥናት እንስራ። አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ትግርኛ እያወራን ጥናት እንስራ! ወደ ትልልቅ ተቋማት እንግባ እና አገልግሎት እንጠይቅ! ተክላይም፣ ተክለብርሃንም፣ አበበም፣ ገመዳም ላይ ገብተን እንጠይቅ፣ ታክሲ ሰልፍ ላይ፣ ካፌ ውስጥ በእነዚህ ቋንቋዎች ጥናት እንስራ። ማን ነህ ደፋር! ና እውነቱን እንጋፈጥ እስኪ!

መፍትሄ:_ እነ ደብረፅዮን ድሮ ድሮ “በትግራይ ህዝብ ስም የሚጠቀም” ብለው አላመኑም ነበር። አሁን ዳር ዳር እያሉ ነው። ሌላ ችግር ፈልጎ ማመን በሽታ ነው። እውነታውን አሁኑኑ አምኖ፣ ጥላቻም፣ ፍርሃቱንም ከማስወገድ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም። እውነታውን መጋት ነው። ግን አያምኑም! ይከብዳቸዋል!

ከኤርሚያስ ለገሰ ይድረስ ለዶ/ር አቢይ አህመድ (ለኦህዴድ ፅህፈት ቤት ሀላፊ) 

ከኤርሚያስ ለገሰ
ይድረስ ለዶ/ር አቢይ አህመድ
(ለኦህዴድ ፅህፈት ቤት ሀላፊ)

ሰላም ላንተ ይሁን።

ይህን ማስታወሻ የምፅፍልህ የምከትበው ነገር ላታስበው ትችላለህ ከሚል እምነት ተነስቼ አይደለም። በዙሪያህ ያሉ የድርጅቱ ሃላፊዎች እና አማካሪዎችም ያጡታል ከሚል ጥራዝ ነጠቅነት የመነጨ አይደለም። ነገር ግን በፓርቲው የፕሮፐጋንዳ እና ድርጅት እቅድ የማውጣት እና አፈፃፀሙን የመከታተል ስራዎች ላይ ቆይታ አድርጐ እንደነበረ ሰው ቀለል ያሉ ምክረ ሐሳቦችን ለመሰንዘር ነው። እነዚህ አስተያየቶች ቀላልና ህውሃት ቀርጾ ለሩብ ክፍለ ዘመን እየተገበረ ካለው ” ህጋዊ ማእቀፍ” ሳትወጡ ልትፈፅሙት የምትችሉት ናቸው።

ካልተቀየረ በስተቀር የድርጅትና ፕሮፐጋንዳ እቅድ ስታወጡ የሁኔታዎች ትንተና ( SWOT analysis) እንደምታደርጉ አውቃለሁ። ከእነዚህ የሁኔታዎች ትንተና ተነስታችሁ በአመቱ የምትፈፅሟቸው ቁልፍ እና አበይት ተግባራት እንደምትዘረዝሩም እገምታለው። በሌላ በኩል ይህ ከባድ ሃላፊነት በአንተ ጫንቃ ላይ እንደወደቀ ደግሞ ከያዝከው ስልጣን በመነሳት መገመት ይቻላል። መቼም እንደ ሰገሌው ዘመን ህውሓት በትግርኛ እቅድ አውጥቶ በአማርኛ እና ኦሮምኛ ተርጉማችሁ ወደ ስራ አውሉት የሚለው ዘመን ታሪክ የሆነ ይመስለኛል። እርግጥ እነ አባይ ፀሀዬና በረከት ስምኦን ይሄን ሊያደርጉት አይችሉም ብሎ መገመት ግን የዋህነት ነው። ይሁን እንጂ የበላይ አለቃህ የሆነው ለማ መገርሳ ” ቀዳድጄ ቅርጫት ውስጥ ከተትኩት!” እንዳለው አንተም የአለቃህን አርአያነት እንደምትከተል አልጠራጠርም። የፈጠነ አስተያየት ቢሆንም በአጭር ጊዜ ያሳየኸው የአመራር ጥበብ ለዚህ አገላለጤ መነሻ ነው።

በቅርብ እርቀት እንደተመለከትኩት አንተም ሆነ አለቃህ ለማ መገርሳ ” የጥሩ መሪ ባህሪያት” እንደተላበሳችሁ ብዙ ኢትዬጲያውያን ምስክርነት እየተሰጡ ነው። አንዳንድ የቅርብ ወዳጆቼ ከዚህ በኃላ ብትሳሳቱ እንኳን ኢትዬጲያዊነትን የሰቀላችሁበት ማማ ታሪክ የሚያስታውሰው ነው በማለት በግላጭ እየመሰከሩ ነው። በእኔ አመለካከት የሰው ልብ የሚሰርቅ ተወዳጅነት በእርግጥም የአመራር ጥበብና ቅመም በውስጣቸው የሌላቸው ሰዎች ሊኖራቸው አይችልም። በፍፁም። በተለይ ደግሞ ተቀባይነቱ ወደ ኔጌቲቭ ወርዶ የአመራር ትርምስ ውስጥ የገባው ህውሓት ጣዖት መሆኑ ባልተለወጠበት ሁኔታ የእናንተ ጐልቶ መውጣት የጥሩ መሪ ባህሪ ለመላበሳችሁ ምስክር ሊሆን ይችላል።

ጓድ አቢይ! እንደምታውቀው ጥሩ መሪ መሆን በተከታዬች እና በውጤት የሚሰጥ እውቅና ነው። አዴይር ጆን የሚባል የአመራር ሳይንስ ፀሀፊ ” ውጤታማ መሪ” በሚለው መፅሐፋ ጥሩ መሪነት የሚለካባቸው ሁለት ቁልፍ ጉዳዬችን ያነሳል።

የመጀመሪያው ተከታዬቹ ” እከሌ/ እከሊት መሪዬ ነው!” በማለት እውቅና ሲሰጡት የሚመጣ ነው። ይህም በተከታዬች ዘንድ ጥልቅ ስሜት፣ ሁለንተናዊ እይታ፣ የማሳመን እና የመወሰን ችሎታ እንዳላቸው ማረጋገጫ ሲሰጥበት እንደሆነ ይመሰክራሉ። ጥሩ መሪ አንደበተ ርቱዕ መሆን ይጠበቅበታል። የመሪነት ጨው ያላቸው መሪዎች አብሮ መቆምን፣ ከራስ ስልጣን በላይ ለሚመሩት ህዝብ ከፍተኛ ፍቅር እና አክብሮት አላቸው። ህይወታቸውን ይሰጣሉ። ከአገር እና ህዝብ በላይ የሚበልጥባቸው ነገር የለም።

አዴይር ጆን በሁለተኛ ደረጃ የሚያስቀምጠው መመዘኛ በመሪው የአመራር ጥበብ ድርጅቱ አላማውን በማሳካት መጠን የሚለካ ይሆናል ይላል። የድርጅቱን አላማ የማያውቅ መሪ ጥሩ መሪ ሊሆን አይችልም። የፓለቲካ ፓርቲ ደግሞ የሰዎች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን ቀዳሚ አላማው ሰብአዊነት ነው። ሰብአዊነት የሚሰማው አመራር ያሻል። የፓለቲካ አመራር አላማ ከሰብአዊነት እና ከህዝብ እምነት ጋር መግጠም ይኖርበታል። በበቀልና በጥላቻ የተበከለ ልብ ይዞ የሚጓዝ መሪ የዜጐች መብት እና ክብር፣ አልፎም ሄዶ የአገር ፍቅር ሊኖረው አይችልም። (የአቶ መለስ ዜናዊ የሞቱ መንስኤ በበቀልና በጥላቻ የተበከለ ልብ ይዞ መጓዙ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።)

ጓድ አቢይ!ቀደም ሲል ወዳነሳሁት ልመልስህና በያዝነው አመት እተገብረዋለው ብለህ የምታወጣው የድርጅትና ፕሮፐጋንዳ እቅድ ላይ ሊካተት ይገባል ወደምላቸው ቁምነገሮች ልመለስ። መላልሼ እንደገለጥኩት መክረ ሃሳቤ የእኔን ፍፁማዊ ፍላጐት የሚያሟላ አይደለም። እኔ ህውሓት ከኢትዬጲያ ፓለቲካ ምህዳር ተጠራርጐ እንዲወጣ የምፈልግ ሰው ነኝ። በሌላ በኩል አንተ በህውሓት የበላይነት ውስጥ እየኖርክ የእኔን ምኞት መቶ በመቶ ክተብልኝ የምል ማሞ ቂሎ አይደለሁም። በመሆኑም አንተ (የድርጅቱን የበላይ ሀላፊ!) የምጠይቀው በህውሓት የህግ ማእቀፍ ውስጥ ሆነህ እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጉባኤ ልትፈፅመው ይገባል የምለውን “ህጋዊ” ተግባራት ይሆናል። የማቀርባቸው አስተያየቶች በድርጅት እና ፕሮፐጋንዳ ዙሪያ የታጠሩትን ብቻ ይሆናል።

ተግባር አንድ:- በኦህዴድ ውስጥ ያሉ ምንደኛ አመራሮች መመንጠር

ህውሓት በውስጠ ድርጅት ትግል ውስጥ ቢሸነፍ ሕልውናቸው አጠያያቂ ከሚሆነው ክፍል ውስጥ በኦህዴድ ውስጥ ያሉ ተላላኪዎች ይሆናሉ። እነዚህ ዘወትር ” ከጳጳሱ ቄሱ” ለመሆን ሲፍገመገሙ የነበሩ የኦህዴድ አመራሮች በቀጣዩ ግምገማና ድርጅታዊ ጉባኤ መመታት ከቻሉ ማረፊያ ያጣች ወፍ መሆናቸው አይቀርም። ለማ መገርሳ( የኦህዴድ ሊቀመንበር) እና አንተ ( የፅህፈት ቤት ሀላፊ) በያዛችሁት ቁመና መቀጠል ከቻላችሁ የምንደኞቹ እጣ ፋንታ ከፓለቲካው መድረክ መወርወር ይሆናል። ህውሓትም ቁመናው ስለተዳከመ እና ስለሚፈራ ከአሸናፊዎቹ ጋር በማበር አብሮ ወርዋሪ ይሆናል። በመሆኑም የድርጅት እና ፕሮፐጋንዳ እቅድ የመጀመሪያ ተግባሩ እነዚህን ተላላኪዎች ከድርጅት ስልጣን ማባረር ሊሆን ይገባል። ወርቅነህ ገበየሁን፣ ድሪባ ኩማን፣ አብድላዚዝን፣ ፍቃዱን ፣ እሸቱ ደሴን…ወዘተ ከድርጅት ስልጣን ማእከሉ ማባረር የእናንተ ስልጣን በመሆኑ የህጋዊነት ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም። ኩማ ደመቅሳን፣ ግርማ ብሩን፣…ወዘተ ከጡት አባትነት ገሸሽ ማድረግ በተመሳሳይ ቀላል ነው። ይህም ሆኖ የአልሞት ባይነት ተጋድሎ ሊያደርጉ ቢችሉም የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም።

ተግባር ሁለት:- የኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እና የፅህፈት ቤት ሀላፊነቱን መረከብ

ጓድ አቢይ! ለኢህአዴግ ቁመናም ሆነ የአባላት ብዛት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁ። የህውሓት እና ደኢህዴን አባላት ተደምረው የእናንተ በእጥፍ ይበልጣል። የኦሮሞን ህዝብ ወክላችኃል የሚል እምነት ባይኖረኝም እናንተ ” ወክለናል” ያላችሁትን ተቀብዬ በህዝብ ብዛትም ማንም አይደርስባችሁም። ከዚህ በተጨማሪም ኢህአዴግ በአብዛኛው የሚያገኘው ገቢ አባል ድርጅቶቹ ድጐማ የሚሰጡት እንደሆነ ይታወቃል። ከፍተኛ ድጐማ የሚመጣው ከኦህዴድ በመሆኑ ሊቀመንበሩነቱንም ሆነ የፅህፈት ቤት ሀላፊነቱን መረከቡ ፍትሐዊ ነው። ተገቢም ነው። ከሁሉም በላይ በብቃትና ኢትዬጲያዊነት በኢህአዴግ ውስጥ የሚስተካከላችሁ ባለመኖሩ ወንበሩን በውድም ይሁን በግድ መንጠቅ ይኖርባችኃል።

ተግባር ሶስት:- የ18 ቀኑን የኢህአዴግ ሰአኮ ግምገማ እና በቀጣይ የኦህዴድ ሰአኮ እና ማእከላዊ ኮሚቴ የሚያደርገውን ግምገማ እንደ ወረደ ይፋ ማድረግ።

ጓድ አቢይ! በቤተመንግስት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ(ሰአኮ) ግምገማ ያደረጋችሁት ትግል ህዝቡ ሳይቆራረጥ እንዲያዳምጠው እና የህሊና ፍርዱን እንዲሰጥ በይፋ መጠየቃችሁን ሰምቻለሁ። ይሄ ውሳኔያችሁ ለድርድር የሚቀርብ መሆን የለበትም። እስከማውቀው ድረስ የቀረፃውን ስራ የሚሰራው የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ዶክመንቴሽን ክፍል ነው። ዶክመንቴሽን ክፍሉ ደግሞ የብሔር ድርጅቶቹ ኮፒ አድርገው ለመውሰድ ጥያቄ ካቀረቡ የመስጠት ግዴታ አለበት። አይደለም ድርጅቶቹ የሁሉም ፓርቲ አመራሮች ለጥናት አሊያም ዶክመንት ለማዘጋጀት ከጠየቁ ዶክመንቴሽን ክፍል ሄደው መጠቀም ይችላሉ። ዛሬም ቢሆን የተለወጠ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም።

በሌላ በኩል የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚውን ግምገማ ህውሓት ከድርጅቱ ህግ በላይ ሆኖ መስጠት ካልቻለ ሌላ አማራጭ መከተል ይቻላል። የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ፣ ማእላዊ ኮሚቴ እና የጉባኤ ስብሰባውን በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ። በእነዚህ ስብሰባዎች በቤተመንግስት ያነሳችሁትን መከራከሪያዎች በግልፅ ማቅረብ ያስፈልጋል። ይሄን አለማድረግ የፈጠራችሁትን አመኔታ ከመሸርሸሩም በላይ አሁንም ተላላኪዎች ናቸው የሚለውን ስማችሁን ትንሳኤ የሚያረጋግጥ ይሆናል። ይሄን አለማድረግ በሸፍጥ ላይ ለተመሰረተው የህውሓት ፓለቲካ ተጠልፎ በመጣል ታሪካዊ ስህተት መፈፀም ነው። ኢትዬጲያዊነት የሚባለው ስሜት በሚተናነቃቸው እግር ስር በመውደቅ ማንሰራራት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

ተግባር አራት: – ሶህዴፓ ወደ ኢህአዴግ የሚቀላቀል ከሆነ ግንባሩን ጥሎ መውጣት

በአብዲ ኢሌ የሚመራው ሶህዴፓ ወደ ኢህአዴግ ለመቀላቀል ከህውሓት አረንጓዴ መብራት እንደበራለት የህውሓት የደም አባላት ነግረውናል። ጓድ አቢይ! አንተም ሳታዳምጠው የቀረህ አይመስለኝም።እነዚህ በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ ከአብዲ ኢሌ የሚከፈላቸውና የሰውየውን የፕሮፐጋንዳ ማሽን በኮንትራት የወሰዱ የአድዋ ልጆች ከጀርባ ግፊት እንዳደረጉ የሚያጠያይቅ አይደለም። አላማውም ለህውሓት ተጨማሪ አቅም መፍጠር እና ኦህዴድን ከጥቅም ውጭ ማድረግ ነው። ይሄ ሸፍጥ አይገባችሁም ከሚል አይደለም። ነገር ግን ግንባሩን ለቃችሁ እንደምትወጡ በአደባባይ መናገሩ ገንዘብ እየተከፈላቸው ህዝብ ከህዝብ የሚያጨፋጭፋትን የአድዋ አወናባጆች ኩምሽሽ ያደርጋል። በሂደትም በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ የራሳችሁን ጥቅም በተሻለ ደረጃ ለማስጠበቅ ኢህአዴግን ለቆ ለመውጣት የምታደርጉትን ሩጫ መደላድል ያመቻቻል። መቼም የኦህዴድ በኢህአዴግ ዣንጥላ ውስጥ መገኘት በኢትዬጲያውያን ዘንድ ከመሰደብና ከመናቅ ውጭ ያተረፈላችሁ ነገር እንደሌለ ጠንቅቃችሁ ታውቁታላችሁ።

ተግባር አምስት:- ኦፌኮን ይቅርታ መጠየቅና በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ የፓለቲካ ምህዳሩን ማመቻቸት

ጥሩ መሪ የለውጥ ሐዋርያ ነው። ለመሰረታዊ ለውጥ ያልተነሳሳ ሰው መሪ መሆን አይችልም። መሰረታዊ ለውጥን መምራት ደግሞ የእሳት ወላፈኑንም ሆነ የጥይት አረርን ቀድሞ ለመቀበል ዝግጁነት ይጠይቃል። በሌላ በኩል ጥሩ መሪ ራሱን በተሻሉ መሪዎች ለመተካት ማመቻቸት ይኖርበታል።
ለሁሉም ግልፅ ሆኖ እንደሚታየው ፕሮፌሰር መረራን ጨምሮ የኦፌኮ አመራሮች እና አባላት ብሔራዊ ውርደትን ላለመቀበል፣ ንቅዘት እና የሞራል ድቀትን ለመታገል፣ ዘረኝነት እና ኢ-እኩልነትን ለማስቀረት መስዋእትነት ከፍለዋል። መረጃና ማስረጃ ላይ ተደግፈው የህውሓት አገዛዝን ገበና እርቃኑን የሚያስቀረውን፣ ቅጥፈቱንና ውስልትናውን የሚያጋልጥ ስራ ሰርተዋል።
የለማ እና አቢይ አመራር ለዚህ የኦፌኮ የነፃነት ትግል ለተከፈለ መስዋእትነት እውቅና መስጠት ይኖርበታል። እግራቸው ስር ወድቆ ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ይሄን ማድረግ ጀግንነት ነው። ሰዋዊም ነው።መሪዎች ጥፋት ተሰርቶ ሲመለከቱ ” ስህተት ሰርቻለሁ፣ አጥፍቻለሁ፣ ይቅርታ ይደረግልኝ!” የሚሉ ከሆነ በአርአያነት እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። በኢትዬጲያ ህዝብ ዘንድ አክብሮት እና ግርማ ሞገስ ይላበሳሉ። እውነቴን ነው የምልህ ይቅርታ መጠየቅ የትልቅነት ምልክት ነው። የኢትዬጲያ ህዝብ ለማ መገርሳ እና ፕሮፌሰር መረራ ከአንድ መሶብ እንጀራ እየቆረሱ ሲበሉ ማየት ይፈልጋል። እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ ከሌሎች የዲሞክራሲ ሀይሎች ጋር መሪውን ጨብጣችሁ ” ኢትዬጲያዊነት ሱስ ነው!” እንድትሉ ይፈልጋል።

መውረድ ይሆንብኛል እንጂ ለኦህዴድ ከህውሓት ይልቅ ኦፌኮ ቅርቡ ነው። ለዚህ ምስክር ጥራ ብባል እሩቅ መሄድ ሳያስፈልገኝ አንተ እና አለቃህን እማኝ ማቅረብ እችላለሁ። እስከገባኝ ድረስ ኦፌኮ ከጅምሩ ጀምሮ በኢትዬጲያዊነት ላይ ጥያቄ ያለው ድርጅት አይደለም።የድርጅቱ ፕሮግራም ላይም ” አንድ ሰው አንድ ድምፅ” መሆኑን አውቃለሁ። ይህ ከሆነ ዘንዳ በሂደት ኦህዴድ ኢህአዴግን ህጋዊ በሆነ መንገድ ፍቺውን ፈፅሞ ከኦፌኮ ጋር ግንባር መፍጠር ይችላል። በሂደትም ወደ ውህደት በመሄድ ከሌሎች ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ጋር ጥምረት መፍጠር ይችላል። አልፋ እና ኦሜጋው የኢትዬጲያ አንድነት እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሚካሄድ ምርጫ ስልጣን ለመያዝ እስከሆነ ድረስ። አበቃው!!

የቂሊንጦ ቃጠሎ ሚስጥሮችን በጨረፋታ ( ጛዜጠኛ ጜታቸው ሽፈራው)

የቂሊንጦ ቃጠሎ ሚስጥሮችን በጨረፋታ

~”የሰው እጅ ጣት ተቆርጦ ቆሻሻ ጋር ተጠርጎ ተጥሏል። ይህን ከቃጠሎው በኋላ ቤት ያፀዱ እስረኞች ነግረውናል። የሰው ልጅ እጅ እና እግር ከቆሻሻ ጋር ተቀብሯል። የምንጠይቀው ወይ እኛ ገድለናል በሉ ወይም ለቤተሰብ ይሰጥ ነው። ቴዎድሮስ የሚባል ልጅ ተገድሎ የት እንደተጣለ አይታወቅም። መታወቅ ስላለበት ነው።” 31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ

(በጌታቸው ሺፈራው)


የቂሊንጦ እስር ቤት ደህንነት እና ጥበቃ ኃላፊ ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም ወልዳይ በቃጠሎው ሰበብ በተከሰሱት እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ (38 ተከሳሾች) በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ቀርበዋል። ተከሳሾች ዋና ኦፊሰሩ በቃጠሎው ወቅት ሰው እንደገደሉ፣ ሸዋሮቢት ወስደው እንዳሰቃዩዋቸው፣ ለቃጠሎው ኃላፊዎቹ ተጠያቂ እንደሆኑ፣ እነ ገ/ማርያም በቃጠሎው ወቅት የትግራይ ተወላጆች እየነጠሉ ከግቢ እንዳስወጡ፣ ተገድለው አስከሬናቸው ለቤተሰብ ሳይደርስ የቀሩ እስረኞች እንዳሉ በመስቀለኛ ጥያቄዎቻቸው አመልክተዋል። ተከሳሾቹ ካቀረቡት መካከል፣ የ31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ መስቀለኛ ጥያቄና የዋና ኦፊሰሩ መልስ ከሞላ ጎደል የሚከተለውን ይመስላል!

ጌታቸር እሸቴ:_ የምንመሰክረው በአሰሩብን ሰዎች ላይ ነው። ትናንት ምስክሩ ሲመሰክሩ እስረኛ ሊያመልጥ ሲል መጀመርያ እግሩን፣ ደረጃ በደረጃ፣ ከዛም ራስ መትተው እንደሚገድሉ ተናግረዋል። በአሰሩን ሰዎች ስለሆነ እየመሰከርን ያለነው ለደህንነታችን ያሰጋናል። ጥበቃ ያሰፈልገናል።

ጌታቸር:_ ታራሚ በበዓል ወቅት ገንዘብ ይሰበስባል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አይሰበስብም

ጌታቸር:_ይሰበስባል አይሰበስብም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላውቅም

ጌታቸር:_ ከእናንተ ጋር አብረው የሚሰሩ የእስረኛ ኮሚቴዎች አሉ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ እንደ አንተ ያሉ!

ጌታቸር:_ እኔ የክልል አስተዳደር እንደነበርኩ ያውቃሉ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አውቃለሁ

ጌታቸር:_ በሽብር የተከሰሱ እስረኞች ላይ እኛ የቤት አስተዳደሮች በምንሰጠው መረጃ መሰረት ልዩ ፍተሻና ቁጥጥር ይደረግባቸዋል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ይፈተሻል፣ ክትትል ይደረጋል።

ጌታቸር :_ በሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ግቢ ውስጥ ሱቅ፣ ካፌ……ጥቅማጥቅም የሚያስገኙ ነገሮች ላይ እንዲሳተፉ አይፈቀድላቸውም አይደል?

ዐቃቤ ሕግ:_ የክሱ አካል አይደለም። በዋና ጥያቄም አልተጠየቀም። ተከሳሽ ከራሱ አግባብ ነው መጠየቅ ያለበት ስለ ሌሎች ተከሳሾች ሊጠይቅ አይገባም።

ጌታቸር እሸቴ:_ የጠየኩት ስለ ሌሎች ተከሳሾች አይደለም። ከአሁን ቀደም የተመሰከረበት ጉዳይ ነው። ጥያቄዬን እንድቀጥል ይፈቀደልኝ!

ፍርድቤቱ:_ ጥያቄው አግባብ ነው ይቀጥል!

ፍርድ ቤቱ:_ ተከሳሹ የሚሉት በሽብር የተከሰሱት በልዩ ልዪ የስራ መደብ አትመድቡም፣ አድሎ ታደርጉባቸዋላችሁ ነው!

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አይገባም የሚባል የለም!

ጌታቸር እሼቴ:_ እኔ በሽብር ተከስሼ ነው የገባሁት?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_በምን እንደገቡ አላስታውስም።

ጌታቸር እሼቴ:_ ነሃሴ 28/2008 ዓም የየቤቱ አስተዳደሮች አስተዳደር ቢሮ መመሪያ ተሰጥቶን ለታራሚ ትዕዛዝ እንድንሰጥ ልከውናል!

ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም:_ አላኩም

………
ጌታቸር እሸቴ:_ ረብሻው የተነሳው በምግብ ጥያቄ ነው አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሼቴ:_ ዞን 2 ወልደሚካኤል ኃለፎምን ያውቁታል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አውቀዋለሁ

ጌታቸር እሸቴ:_ ሰጠኝ ሙሉ፣ ወጋየሁ ረጋሳ፣ መድሃኒት፣ አብዲሳ ቦካ፣…… ያውቋቸዋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አላውቃቸውም

ጌታቸር እሼቴ:_ አባይ ነህ የ2ኛ ቤት አስተዳደር፣ ያኬት የ4ኛ ቤት አስተዳደር፣ ወጋየሁ ኦሮሞነው፣ መድሃኒት አማራ ነው። ኮሚቴ ናቸው። የእናንተ ረዳት ናቸው። ወልደሚካኤል ግን ምንም ስራ ሳይኖረው፣ ሳያግዛችሁ ያስታውሱታል?

ዐቃቤ ሕግ:_ ጥያቄው መጠየቅ የለበትም ብሎ መቃወሚያ አንስቷል።

ጌታቸር እሸቴ:_ ጥያቄውን አልፌዋለሁ!

ጌታቸር እሸቴ:_ እርስዎ የቃጠሎው ሰዓት ዞን 2 በመስጊዱ በኩል ቆርቆሩ አጥሩን ገንጥለዋል አይደል?

ዋና ኦፊሰር: _ አልገነጠልኩም

ጌታቸር እሼቴ:_ ሜዳ ላይ አንድ ረዥም ቀላ ያለ ፖሊስ ወደላይ ጥይት ሲተኩስ በጥፊ መትተው መሳርያውን አልቀሙትም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም: _ አልቀማሁትም

ጌታቸር እሸቴ:_ አብዲሳ ቦንካ የወለጋ ልጅ ነው፣ ሰጠኝ ሙሉ የጎንደር ልጅ ነው በጥይት አልመቷቸውም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አልመታሁም

ጌታቸር እሸቴ: _በወቅቱ ሽጉጥ ይዘው ነበር?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አልተኮስኩም

ጌታቸር እሼቴ:_ እኛ አድኑን እያልን በቀኝ እጅዎት ሽጉጥ፣ በግራ እጅዎት ወልደ ሚካኤል ኃለፎም እና ከፊት ደግሞ ታደለ ብርሃኑን ይዘው ከግቢ አላስወጡም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አላስወጣሁም

ጌታቸር እሼቴ:_ ገመቹ የሚባል ፖሊስ ያውቃሉ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ ከሚጠየቁት አንዱ ነው

ጌታቸር እሼቴ:_ እርስዎ ወልደሚካኤል ኃለፎምን እና ታደለ ብርሃኑን ይዘው ሲወጡ “ለምን በዘር እየመረጥክ ታስወጣለህ? እኔም ኦሮሞ እየመረጥኩ ላስወጣ ወይ?” ብሎ አልጠየቅዎትም?

ዋና ኦፊሰር:_ አላለም

………

ጌታቸር እሼቴ:_ ሸዋ ሮቢት አብረውን ሄደዋል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ዐቃቤ ሕግ:_ መቃወሚያ አለን። እኛ እያስመሰከርን ያለነው ስለ ነሃሴ 28/2008 ዓም እንጅ ከዛ በኋላ ስላለው አይደለም። በጭብጡም አልተያዘም። ጥያቄው ውድቅ ይደረግልን።

ጌታቸር እሸቴ:_ እኔም እየጠየኩ ያለሁት ስለ ነሃሴ 28 ነው። ጥያቄዬን እንድቀጥል ይፈቀድልኝ!

ፍርድ ቤቱ:_ ጥያቄው መልስ ተሰጥቶበታል። ይቀጥሉ!

ጌታቸር እሼቴ:_ ነሃሴ 28 ማታ 4 ሰዓት አንገትዎት ላይ ሽርጥ አድርገው ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ወስደውናል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ስንወጣ ሁሉም ታራሚ ዕቃ ይዞ ነበር?

ዋና ኦፊሰር:_ አላስታውስም

ጌታቸር እሸቴ:_ ትናንት እቃ ሰብስበናል ብለው ስለመሰከሩ ነው!

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ የአንገት ሀብል፣ የጣት ቀለበት፣ መነፀር፣ ጫማ፣ ልብስ… … እያስወለቃችሁ ከግቢ እንድንወጣ ነው ያደረጋችሁ አይደል?

ዋና ኦፊሰር:_አልወሰድንም

ጌታቸር እሸቴ:_ በባዶ እግር ነው የወሰዳችሁን?

ዋና ኦፊሰር:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ የሰበሰባችሁት ንብረት ምን ተደረገ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ ተሰብስቧል። ከዛ በኋላ አላውቅም።

ጌታቸር እሸቴ:_ ከሸዋ ሮቢት ስንመለስ፣ ልብሳችንና የዘረፋችሁትን ንብረት ስጡን ስልዎት፣ “የማረሚያ ቤቱን ንብረት እንዳወደማችሁት፣ የእናንተንም ንብረት አውድመነዋል” አላሉኝም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አላልኩም

ጌታቸር እሸቴ:_ የታራሚ መነፀር፣ ገንዘብ፣ የጣት ቀለበት…… ንብረት ተወስዷል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላየሁም

ጌታቸር እሸቴ:_ አላዩም

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አላየሁም

ፍርድ ቤቱ: _የተወሰደ ገንዘብ አለ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ የተወሰደ የለም። አላውቅም።

ፍርድቤቱ:_ እርግጠኛ ከሆኑ የለም ይበሉ!

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልተወሰደም

ጌታቸር እሸቴ:_ የተሰበሰበ ንብረት አልነበረም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ ሻንጣና ፔስታል ተሰብስቧል።

ጌታቸር እሸቴ:_ ታዲያ የት ሄደ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ ዝናብ መትቶት፣ ገምቶ ተወግዷል።

ጌታቸር እሸቴ:_ ትናንት ጠሃ እና ቴዎድሮስ የሚባሉ መረጃ ይሰጡን ነበር ብለዋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ የት ናቸው ተብለው ሲጠየቁም፣ ሞተዋል ብለዋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ ቴዎድሮስ ማለት ጠያቂ የሌለው ገድላችሁ የቀበራችሁት ልጅ ነው አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አይደለም

ፍርድ ቤቱ:_ ተከሳሽ አግባብነት ባለው መንገድ ይጠይቁ!

ጌታቸር እሸቴ:_ አሻሽላለሁ። ግን እርስዎ (ግራ ዳኛው) ከአሁን ቀደም በነበረው ሂደቶች ስላልነበሩ ይሆናል። ስንናገር ቆይተናል። የሰው እጅ ጣት ተቆርጦ ቆሻሻ ጋር ተጠርጎ ተጥሏል። ይህን ከቃጠሎው በኋላ ቤት ያፀዱ እስረኞች ነግረውናል። የሰው ልጅ እጅ እና እግር ከቆሻሻ ጋር ተቀብሯል። የምንጠይቀው ወይ እኛ ገድለናል በሉ ወይም ለቤተሰብ ይሰጥ ነው። ቴዎድሮስ የሚባል ልጅ ተገድሎ የት እንደተጣለ አይታወቅም። መታወቅ ስላለበት ነው። በፍርድ ቤቱ ጫና እየተደረገብኝ ነው። ካልሆነ አቁም በሉኝ ጥያቄዬን ላቁም!

ፍርድ ቤቱ:_ ጥያቄው ታልፏል! ሌላ ጥያቄ ካለዎት ይጠይቁ!
………
……

አግባው ሰጠኝ:_ እኛ ክስ ላይ ሞቷል ተብሎ ከተጠቀሰው ሰው በላይ ሰው እንደሞተ ለማሳየት ነው። ምስክሩ ራሳቸው የገደሉትን፣ ነገር ግን ክስ ላይ ያልተጠቀሰ ሰው እንደሞተ ስላመኑ ጥያቄያችን እንቀጥል።

(ሌሎች ተከሳሾችም በቂሊንጦ ቃጠሎ ተገድለው ለቤተሰብ አስከሬናቸው ያልተሰጠ፣ ክስ ላይ ስማቸው ያልተጠቀሱ አሉ። ምስክሩ ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም ይህን እያመኑ በመሆኑ ለማጣራት እንዲቻል ጥያቄው ይቀጥል በሚል ጥያቄው እንዲቀጥል ፍላጎታቸውን ገልፀዋል። ፍርድ ቤቱ አልፈቀደም!)

የትኛውም የህወሀት ዲስኩር፡ በሃይለማርያም አንደበት ሲመጣ ቶምና ጄሪን እንደማየት በፈገግታ አልፈዋለሁ።( በጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ብዙ ጊዜ ሃይለማርያም ሲናገር ያዝናናኛል። በሱ ንግግር ከመዝናናት ባለፈ የተናደድኩበት ጊዜ ስለመኖሩ አላስታውስም። ባለፈው ረቡ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ሃይለማሪያም አናደደኝ። ”በደርግ ጊዜ የሰው ልጅ ማሰቃያ የነበረው ማዕከላዊ……” ብሎ ሲጀምር ትኩር ብዬ አየሁት። አይኑ እንኳን አይርገበገብም። እኔ ግን በንዴት ቦግ አልኩኝ። እንዳልኩትም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የትኛውም የህወሀት ዲስኩር፡ በሃይለማርያም አንደበት ሲመጣ ቶምና ጄሪን እንደማየት በፈገግታ አልፈዋለሁ። የረቡ ዕለቱ ግን ከውስጥ ጠቅ የሚያደርግ ንዴት ሰውነቴን ነዘረኝ። ደግሜ ደጋግሜ አየሁት። በደጋገምኩት ቁጥር የማይበርድ ንዴት ይንጠኛል። ለምን ይሆን?

ከማዕከላዊ የሰማናቸው የቶርቸር አሰቃቂ ዜናዎች፡ ስቃዮች፡ የጣር ድምጾች ከጆሮአችን ጓዳ ሳይወጡ ሃይለማርያም ስለደርግ ዘመን ሲያወራ መስማት በእርግጥም ያማል? ከደርግም በከፋ መልኩ በዘር ማንነታቸው እየተዘለፉ፡ ብልታቸው የተኮላሸ፡ ጥፍሮቻቸው በጉጠት የተነቀሉ፡ ጡታቸው በኤሌክትሪክ ሽቦ የተተለተሉ፡ በርበሬ ታጥነው፡ የገማ ጨርቅ በአፋቸው ተወትፎ ወፌላላ ተዘቅዝቀው የተገረፉ፡ በእግራቸው ተራምደው ገብተው በቃሬዛ አስክሬናቸው የወጣ፡ የስንቱን ወጣት ስቃይና መከራ እየሰማን ሀዘን ልባችንን ወግቶት ባለበት በዚህ ወቅት ”ማዕከላዊ በህወሀት ዘመን ኩሪፍቱ ሎጅ ነው” ማለት የቀረውን የሃይለማርያምን ደረቅ ውሸት ከመስማት በላይ ምን ቅጣት አለ? ሃይለማርያም ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ሆኖ ”ማዕከላዊ በደርግ ዘመን….” እያለ ሲያላዝን በአንድ ኪሎሜትር ርቀት አራዳ ፒያሳ ከሚገኘው ማዕከላዊ የኢትዮጳያ ልጆች በህወሀት ገራፊዎች ቶርቸር እየተደረጉ ነበሩ።

ደርግና ህወሀት በማዕከላዊ ለንጽጽርም የሚበቁ አይደሉም። በሶስት ምክንያቶች። አንደኛው ከዘመን አንጻር ነው። ሁሌም ዛሬ ከትላንት ይሻላል። ነገ ደግሞ ከዛሬ። የሰብዓዊ መብት፡ ዲሞክራሲ፡ እኩልነት፡ ፍትህና ነጻነት ዓለምን እየዋጁ፡ የበላይነትን ይዘው የሀገራት የዕድገት መለኪያ በሆኑበት ዘመን የተፈጠረው ህወሀት ከትላንቱ ደርግ ጋር በአንድ ሚዛን መቀመጥ አይገባውም። ሁለተኛው ምክንያት ደርግ ማዕከላዊን በማሰቃያነት የተጠቀመው ለጥቂት ዓመታት ብቻ ነው። የቀይ ሽብር ዘመን ካበቃ በኋላ በማዕከላዊ ቶርቸር የሚፈጸም መሆኑን የሚገልጽ መረጃ ላገኝ አልቻልኩም። እናም ከ17 ዓመቱ የደርግ የስልጣን ጊዜ ማዕከላዊ በማሰቃያነቱ የዘለቀው ከአምስት አመታት በላይ አይሆንም። ህወሀት እነሆ ለ27ዓመታት ማዕከላዊን የኢትዮጵያውያን የስቃይ ማዕከል አድርጎ በመጠቀም የእድሜውን ያህል ቆይቷል።

ሶስተኛው ምክንያት በደርግ ዘመን ገራፊዎቹ ወይም ገዳዮቹ ከአንድ ብሄር የተወለዱ አይደሉም። ስቃይ የሚደርስባቸው ኢትዮጵያውያንም በዘር ማንነታቸው ተሰፍረው አልነበረም። በህወሀት ጊዜ ገራፊዎቹና ገዳዮቹ ከአንድ ወገን፡ ስቃይና መከራን የሚቀምሱት ደግሞ በዘር ማንነታቸው በህወሀት መዝገብ ”ጠላት” የተደረጉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ነው። ሀብታሙ አያሌው እንደነገረን ”ትግርኛ ቋንቋ በሰማሁ ቁጥር የማዕከላዊ ስቃይ እየተመላለሰ ያስጨንቀኛል።” ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ እንዳጫወትችንም ”መቀሌ እስር ቤት ያለሁ ነው የመሰለኝ።” ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እንደሚለውም ”ማዕከላዊ የህወሀት የምርኮ ቦታ እስኪመስል ገራፊ ከትግራይ የተሰባሰቡበት ቦታ’

ለማንኛውም ሃይለማርያም ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ አናዶኛል። ከዚህ በላይ ምንም ቢናገር የሚያናድድኝ አይመስለኝም። በተረፈ ህወሀት ማዕከላዊን የመዝጋት ሞራል የለውም። ህንጻ ቢዘጋ ምን ትርጉም አለው? ከማዕከላዊ የከፉ ስንት ስውር የማሰቃያ ቦታዎች እንዳሉ እናውቃለን። በሀሽሽ በጦዙ፡ በአልኮል በናወዙ፡ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በደረቀባቸው ነውረኛ የትግራይ ደህንነቶች በየስውር ማሰቃያ ቤቱ እየተፈጸሙ ያሉትን ግፎች ሂሳብ የምናወራርድበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የማዕከላዊ የስቃይ ዘመን የሚያከትመው በህወሀትን መቃብር ላይ ነው።

‘አንዳንዶች’

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ፌስ ቡክ ገጽ ላይ ስምንት ጊዜ ተቀያይሯል። ፋና ማልዶ ጠዋት የነገረንን ከቀትር በኋላ ለዋውጦታል። ሲጀምር በይቅርታ ኋላ ላይ በምህረት፡ ጠዋት ”ሁሉም”፡ ምሽት ላይ ”አንዳንዶች”፡ ንጋት ላይ ”የፖለቲካ እስረኞች፡ ረፋድ ላይ ”ፖለቲከኞች”፡ አመሻሽ ላይ ”ጥፋት የሰሩ ግለሰቦች”፡ ….መግለጫው ስንቴ ተደለዘ፡ ስንት ግዜ ተሰረዘ። ጭራሽ በነጋታው ያላልኩት ነው የተጠቀሰው ብሎ ሃይለማርያም ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱን ሰማን። ”አንዳንዶች” በሚል ይታረምልኝ ብሏል– ህወሀት በሃይለማርያም በኩል። ”አንዳንዶች” እነማን ይሆኑ?

ድሮም ቅንነት የጎደለው፡ ከአንጀት ያልዘለቀ፡ በውሸት የተለበጠ፡ ከተመረዘ ጭንቅላት የተጨመቀ፡ ክፋት ከሞላው ልብ የፈለቀ፡ ደም ባጨቀየው እጅ የተጻፈ መግለጫ ነው። እየዋሹ እርቅ የለም። እየቀጠፉ መግባባት አይታሰብም። ዕውነት ከእርቅ ይቀድማል። መግባባት ሀቅን ይፈልጋል። ህወሀት ከዕውነት ጋር የተጣላ፡ በውሸትና ቅጥፈት የተሞላ ነው። ደቡብ አፍሪካውያን የአፓርታይድን ጥቁር ዘመን ሲሸኙት በቅድሚያ ዕውነቱን ተነጋግረው ከዚያም ወደ ዕርቅ በማምራት ነው። የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ታሪክ የተቋጨው የዕውነትና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ተቋቁሞ፡ ዕውነቱ ፍርጥርጥ ተደርጎ ወደ ዕርቅ በመሸጋገር እንደሆነ እናስታውሳለን። ህወሀት ተፈጥሮው ለዚህ አይፈቅድም። መሪዎቹ ጫካ በነበሩ ጊዜ ከሰውነታቸው ውስጥ የሆነ ተቆርጦ የወጣ፡ የጎደላቸው ነገር ያለ ይመስላል። ዕውነት ያማቸዋል። ውሸት ያለመልማቸዋል። ቅንነትን ይጠየፋሉ። ክፋትን ይመርጣሉ።

ሃይለማርያም የጎረሰውን እንዳለ ተኩሷል። ያጠናውን ቃል በቃል አነብንቧል። የህወሀትን ተራ ውሸትና ጅላጅል ዲስኩር ሳያላምጥ ውጦ፡ አንድም ሳያስቀር ተፍቶታል። በሃይማኖተኝነቱ የሚያውቁት የቀድሞ ወዳጆቹ መቼም ያፍሩበታል።አዲስ ነገር አይደለም። ወዶ ገብ፡ ምርኮኛ፡ የቤተመንግስት እስረኛ በመሆኑ ሲጠሩት ‘አቤት’፡ ሲልኩት ‘ወዴት’ ከማለት ውጪ ምርጫ አይኖረውም።መቼም ወደ ሰውነት ተራ አይመለስም። ተመችቶታል። የህወሀት መቀለጃ እንደሆነ ዕድሜውን ጨረሰው። ስለሃይለማርያም እዚህ ላይ ይብቃኝ።

የ18 ቀናቱ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዝግ ስብሰባ መጠናቀቁን አስመልክቶ ቅዳሜ የወጣው የተንዛዛና የጠነዛ መግለጫ ለተቀጣጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጥሩ ነዳጅ ነው ማለት ይቻላል። መግለጫውን ተከትሎ ህወሀት ለህዝብ መጥይቅ በትኗል። መግለጫውን እንዴት አገኛችሁት? በእኛ ተስፋ ታደርጋላችሁ ወይ? አይነት መጠይቅ በጥድፊያ ተበትኖ፡ ምላሹ ተሰብስቦ ውጤቱም በራሱ በህውሀት ተገልጿል። በችኮላ ይሁን አልያም በሌላ ምክንያት እውነተኛ ውጤቱ ተበትኗል። በዚህም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው መጠይቁን የሞላው ሰው ”እናንተ አትለወጡም። በእናንተም ተስፋ የሚያደርግ የለም።” የሚል እቅጩን ነግሮአቸዋል። የሻምቡ ተቃውሞ ሲጨመርበት፡ በየቦታው ህዝቡ ትግሉን ሳያቋርጥ መቀጠሉ ህወሀት በመግለጫ ጋጋታ ህዝብን ማንበርከክ እንደማይቻለው ተረዳ። እናም ”እስረኞችን እፈታለሁ” የሚል ሌላ አጀንዳ ከፈተ።

አዎን! ህወሀት ለጊዜው አጀንዳ ወርውሮልናል። እነማን ይፈቱ ይሆን? የሚል አርእስት ተከፍቶልን እየተጨነቅን እየተጠበብን ነው። ይህ መሆኑ ለህውሀት ጊዜያዊ እፎይታን ይሰጠዋል። የውጭ መንግስታት፡ ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች የህወሀትን ተለዋዋጭና ዋስትና የሌለው መግለጫን ይዘው እያራገቡ መሆናቸውን ታዝቤአለሁ። ለኢትዮጵያ ለውጥ የመጣ፡ አንዳች ታሪክ የተፈጠረ ይመስል ሰሞኑን የወሬ ማጥፋጫ እኛኑ አድርገውናል። ጠዋትና ማታ የሚቀያየረውን የህውሀትን አቋም ወደጎን ተትቶ ”ኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ ልትፈታ ነው። ማዕከላዊ ሊዘጋ ነው።” የሚለው ወሬ በውጪው ሚዲያ በርክቷል።

በእኛው መንደርም ያለፉትን ሁለት ቀናት የታየው ስሜት ለትዝብት የሚዳርገን ነው። ያለልክ የፈነጠዙ፡ ደስታቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው በእምባ የተራጩ፡ አንዳንዶች እንደውም ሻንጣቸውን አሰናድተው ጓዛቸውን ጠቅልለው ለመግባት የወሰኑ መኖራቸውን ሰምተናል። ህወሀት የመጀመሪያ ቃሉን አክብሮ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ቢፈታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የሚፈታ አይደለም። በተደጋጋሚ እንደሚባለውም የታስሩለት ዓላማ ሳይፈታ የታሰሩት መፈታታቸው ትርጉም የለውም። ጀግኖቻችን ከተፈቱ መፈታታቸው ሊያስደስተን ይገባል። ከዚያ ባለፈ ደስታ አስክሮ አጥወልውሎ እስኪጥለን ሊደርስ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው።

በእርግጥ ህወህት የፖለቲካ እስረኞችን ይፈታልን? ሪፖርተር ጋዜጣ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ጠብቁ ብሎናል። እነማን እንደሚፈቱ ግን አልገለጸም። በዋዜማ ሬዲዮ በኩል የወጣው መረጃ ደግሞ ደህንነት መስሪያ ቤቱና ፍትህ ሚኒስቴር በሚፈቱት ሰዎች ላይ መግባባት አልቻሉም ይላል። ደህንነት መስሪያ ቤቱ ሰማይ ዝቅ፡ መሬት ከፍ ቢል የማይፈቱ ብሎ በመዝገቡ የያዛቸው አሉ። ሃይለማርያም የመጀመሪያውን መግለጫ በማግስቱ እንዲቀይርና ”አንዳንዶች” በሚል እንዲስተካከል የተደረገው በደህንነት መስሪያ ቤቱ ትዕዛዝ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ህወሀት አስራአንደኛው ሰዓት ላይም ትዕቢትና ድንቁርና አይለቀውም።

በዚህም ተባለ በዚያ ትግሉ ይበልጥ ተጠናክሮ እይተካሄደ ነው። ”አንዳንዶችም” ይፈቱ ”ሁሉም” አሁንም ትግሉ ይቀጥላል። ህወሀት የተሳሳተው እየተካሄደ ያለው ትግል በመግለጫ ጋጋታ፡ በአስቸኳይ አዋጅ፡ እስረኞች በመፍታት የሚቆም አድርጎ ማስላቱ ነው ።በእርግጥ የፖለቲካ ስጋውን እየጨረሰ፡ አጥንቱን እየበላ በቁሙ እየሞተ ያለ ስርዓት ሌላ ምርጫ የለውም።

Mesay Mekonnen

በዚህ ወሳኝ ወቅት ያለው ብቸኛ አማራጭ እስከመጨረሻ መታገልና እውነተኛ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ነው። ( ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም)

በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ መግለጫ ዙሪያ አንድ ነገር ለማለት ሳሰላስል በድንገት የፖለቲከኛ እስረኞች እንደሚፈቱ ተነገረን። የእስረኞች መፈታት ሁላችንንም የሚያስደስት ዜና ቢሆንም፣ ድሮም እነሱ ሳይታሰሩ አፈና እንደነበርና የእነሱ መፈታትም አፈናውን እንደማያቆመው ልብ ማለት ይገባል።

የእስረኞች መፍታት ብቻውን ለህዝቡ ጥያቄ መልስ አይሆንም። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተፈተው በነጻ የሚጽፉበት፣ በነጻ የሚደራጁበትና በነጻ ምርጫ ተወዳድረው አላማቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ይህ አይነቱ ስርዓት የሚዘረጋው ደግሞ ከሁለም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በገለልተኛ አካላት ድርድር ተደርጎ፣ አለም የሚመሰክረው ነጻ ምርጫ ሲደረግና ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር ሲኖር ነው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ስልጣንን በጥገናዊ ለውጥ ለማቆየት ከሚደረግ ሙከራ የተለዬ አይሆንም።

አምባገነን ስርዓቶች ስልጣናቸውን ቢያንስ ከ5ቱ በአንደኛው መንገድ እንደሚያጡ ታሪክ ያስተምረናል።

አንደኛው- መፍንቅለ መንግስት ነው። በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ በርካታ አምባገነን መንግስታት ስልጣናቸው በዚህ መንገድ አጥተዋል። የአፍሪካ ህብረት መፈንቅለ መንግስትን ቢያወግዝም፣ አሁንም በዝምባብዌና ግብጽ ስሙን ቀይሮ እውን ሆኗል።

ሁለተኛው – ህዝባዊ አመጽ ነው። በቱኒዚያ፣ ዩክሬን፣ ሮሜንያ፣ ቼክ ወዘተ በህዝባዊ አመጽ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደርጓል።

ሶስተኛው- ስልጣን የያዘው አካል ከተቃዋሚዎች ጋር ስልጣኑን በመካፈል አብሮ ገዢ ሆኖ መውጣት ነው። በፖላንድ የጄ/ል ጃሩዘልስኪ መንግስት ከሶሊዳሪቲ እንቅስቃሴ ጋር ያደረገው የስልጣን መካፈል ድርድር ይጠቀሳል።

አራተኛው- መሪዎች በእድሜ ሲገፉ እነሱ ለመረጡዋቸው ሰዎች አስረክበው የሚሄዱበት መንገድ ነው። ኬንያ በዳንኤል አራፕ ሞይ፣ አንጎላ በዶሳንቶስ ፣ ኩባ በፌደል ካስትሮ ዘመን የተካሄደውን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል።

አምስተኛው- አምባገነኖች በአገዛዛቸው ላይ መጠነኛ ለውጥ አድርገው፣ ህዝቡን በለውጥ ተስፋ እያዘናጉ ምክንያታቸው ሁሉ ተሟጦ እስኪያልቅ ድረስ የስልጣን ጊዜያቸውን እያራዘሙ ይቀጥላሉ። ለዚህ ሩስያ ጥሩ ምሳሌ ናት። ጎርባቼቭ በኮሚኒስት ፓርቲ ውስጥ ያደገ apparatchik ነበር። ጎርባቼቭ ነባር ኮሚኒስቶች ማርጀታቸውንና ኮሚኒዝም እስካሁን በመጣበት መንገድ እንደማይቀጥል ሲያወቀው ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ትንሽ ከፈት በማድረግ በዚሁ ድርጅት ውስጥ የነበሩ ፖለቲከኞች ስልጣን ይዘው እንዲቆዩ የሚያደርግ አሰራር ተከተለ ። ዛሬ ሩስያን የሚገዛት ፑቲን የጎርባቼቭ የእጅ ስራ ውጤት ነው። እነዚህ ሰዎች መጠነኛ የፖለቲካ ለውጥ በማድረግ የሚያጡት ነገር ቢኖር ግለሰባዊ ክብር ነው። ፈላጭ ቆራጭ በነበሩበት ሰዓት ደፍሮ የሚናገራቸው ስለማይኖር ክብራቸው ምንጊዜም እንደተጠበቀ ነው ። የፖለቲካ ሜዳውን ትንሽ ሰፋ ሲያደርጉት በሚደርስባቸው ትችት ክብራቸው የሚነካ ቢሆንም፣ እየተዘለፉም ቢሆንም በስልጣን ላይ ይቆያሉ። ለእነሱ ስልጣን ከግለሰብ ክብር በላይ ነው።

አሁን ህወሃት/ኢህአዴግ ሊከተለው ያሰበው መንገድ እነ ፑቲን የሚሄዱበትን መንገድ ነው፤ ትንሽ ተስፋ በምታጭር ለውጥ ህዝቡን የተስፋ ዳቦ እየመገበ መግዛት ይፈልጋል። ላለፉት 26 ዓመታት ሲጋገር የነበረው የተስፋ ዳቦ የኢኮኖሚ እድገት የሚል ነበር። ዳቦው ሊበላ ባለመቻሉ ህዝቡ ሆ ብሎ ተነሳ። አሁን ደግሞ “የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት” የሚል አዲስ የተሳፋ ዳቦ ይዘው ብቅ አሉ። ይህን የተለመደውን የማታለያ ዘዴ ህዝቡ አምኖ የሚቀበለው አይመስለኝም።
በዚህ ወሳኝ ወቅት ያለው ብቸኛ አማራጭ እስከመጨረሻ መታገልና እውነተኛ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ነው። የተጀመረውን ትግል እስከመጨረሻው በብልጠትና በጥንካሬ ማስኬድ ከተቻለ የጀግኖቻችንን መፈታት ብቻ ሳይሆን ከእንግዲህ ወዲያ ጀግኖች የማይታሰሩበት ስርዓት መፍጠር እንችላለን።

የሁለት ወታደሮች ወግ (በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው)

የሁለት ወታደሮች ወግ

( ትዝብት )

~የቂሊንጦ እስርቤት የደህንነትና ጥበቃ ኃላፊ የነበሩት ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም ወልዳይ ዛሬ ታህሳስ 24/2010 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ በተከሰሱት ላይ መስክረዋል።1ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ምስክሩ እሱንና አቶ በቀለ ገርባን ለማስገደል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን፣ በቂሊንጦ ቃጠሎ ወቅት የተገደሉ እስረኞች በጅምላ ተቀብረው ቀብሩ ላይ እስር ቤት እንደተሰራ፣ የተገደሉ እስረኞች አስከሬን ለቤተሰብ አለመሰጠታቸውን ለማረጋገጥ በርካታ ጥያቄዎችን ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱ በሁለት ወታደሮች “ሀርድ ቶክ” መሰል ምልልስ ጣልቃ እየገባ በክርክሩ የራሱን አስተዋልኦ አድርጓል። በትህትና እንድታነቡት ተጋብዛችኋል!

(በጌታቸው ሺፈራው)

መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ:_ ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ አብርሃ ነዎት አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ!

መቶ አለቃ:_ ተክላይ ኃይሉ፣ ጉኡሽ፣ …… ሁሉም የቂሊንጦ ኃላፊዎች ናቸው አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ በ2008 የዞን 1 ኃላፊ ዘርኡ ነበር?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_የዞን 2 ደግሞ ኃይላይ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ የዞን 3 ኃላፊም ልዕላይ ነበር?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ በሙሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች ናቸው አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

ዐቃቤ ሕግ:_ በክሱ ላይ ያልተጠቀሰና ከክሱ ጋር ግንኙነት የሌለው ጥያቄ በመሆኑ እንቃወማለን!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ክሳችን ላይ ትግርኛ ተናጋሪዎችን ልንገድል እንደነበር ተጠቅሷል። ምስክሩም መልስ ሰጥተውበታል። ያሳደገን ማህበረሰብና ባህል ይህን አይፈቅድም። ከ1ኛ እስከ 20ኛ የመሰከሩት ምስክሮች በተመሳሳይ ምስክርነት ሰጥተዋል። የፖለቲካ ይዘት ስላለው መስተካከል ስላለበት ነው። ለምሳሌ 31ኛ ተከሳሽ ክስ፣ ሁለተኛ ገፅ ላይ የእነተክላይ፣ ገብረማርያም፣ ጠሃ ስብሃቱ ሊገደሉ ነበር ተብሎ ስማቸው ተዘርዝሯል።

ፍርድ ቤቱ:_ከስም ዝርዝር ባለፈ ይህኛው ዘር ይህኛው ዘር ተብሎ አልተጠቀሰም። ሌላ ጥያቄ ይጠይቁ።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ነሃሴ 28 ጥይት እንዲተኮስ ትዕዛዝ የሰጠው ማን ነው?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ቅድም ተናግሬያለሁ!

ፍርድቤቱ:_ ወደ ሌላ ጥያቄ እለፍ!

መቶ አለቃ:_ ኃላፊ ናቸው። እሳቸው ትዕዛዝ መስጠት አለመስጠታቸውን ለማረጋገጥ ነው።

ፍርደ ቤቱ:_ እርስዎ ትዕዛዝ ሰጥተዋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አልሰጠሁም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ከግቢ ሊወጡ ሲሉ የተመቱ እስረኞች ስንት ናቸው?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_2 ናቸው!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ 2 ብቻ ናቸው?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ መቶ አለቃ ዳንኤል፣ ተመሰገን፣ ወዲ፣ ኩልፊ…… የተባሉ እስረኞች አልተመቱም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልተመቱም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ በህይወት ያሉ በጥይት የተመቱ እስረኞች የሉም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ይኖራሉ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ አሉ ወይም የሉም ብለው እንዲመልሱልኝነው። እርግጠኛ ምስክርነት እንዲሰጡ እፈልጋሉ። እርግጠኛ ሆነው ካልሰጡ እንዲመዘገብ አልፈልግም።

ፍርድቤቱ:_ የተመቱ ሰዎች አሉ ወይስ የሉም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አሉ! ይኖራሉ!

ፍርድቤቱ:_ አሉ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ግቢ ውስጥ ያስተባብር ነበር ብለው መስክረዋል!

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ማስተባበር በምን ይገለፃል? በአካል ነው በወረቀት?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_በአካልም በወረቀትም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ በአካል አይተውኛል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላየሁም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ሰምተው ነው?

ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_………

መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ:_ከዞን 2 መቼ ወጣሁ? ቀንና ወሩ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላስታውሰውም።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ጥር ወር ሊሆን ይችላል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላስታውስም።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ከዞን 2 ወደ ቅጣት ቤት ስንሄድ የተሰጠን ምክንያት ነበር?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ቅጣት ቤት አይደለም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ማግለያ ማለት ነው?

ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_አንድ እስረኛ ግቢ ውስጥ ጥፋት ካጠፋ ይቀጣል። እኔ ቅጣት አልተቀጣሁም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ቅጣት አልቀጣንም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_በዚህ ጉዳይ፣ ጨለማ ቤት ስለገባን፣ ከቤተሰብ ጋር እንዳንገናኝ ተከልክለን፣ እኔ 4ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታ አቅርቤ እራስዎ መልስ አልሰጡበትም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ጨለማቤት የለም ብየ መልስ ሰጥቻለሁ። አሁንም የለም።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ያለንበት ቤት ግድግዳውም ጣራውም ሲምንቶ ነው አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ቤቱ አናት ላይ የጥበቃ ማማ አለ አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_በር ላይም ጥበቃ አለ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_የትም አለ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ታዲያ እኔ ከሌላ እስረኛ ጋር መገናኘት እችላለሁ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አትችልም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ሆስፒታል ሄጄ አውቃለሁ? (ምስክሩ እስረኞች ሆስፒታል ሲሄዱ ይገናኛሉ ብለው ስለመሰከሩ ነው)

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ:_እኔ ሆስፒታል ሄጄ አውቃለሁ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ፍርድቤት ስትሄዱ ነው የምትገናኙት!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_እኔ ሆስፒታልሄጀ አውቃለሁ?

ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:__ማንም ሰው ሲታመም ሆስፒታል ይሄዳል። በእርግጠኝነት ግን ፍርድ ቤት ሲሄዱ ይገናኛሉ።

ፍርድ ቤቱ:_ ተከሳሽ የተለያየ ጥያቄ መጠየቅ መብታቸው ነው። ስለሆስፒታል የተጠየቁትን ይመልሱ!

መቶ አለቃ:_ ፍርድ ቤት ከሰው ጋር እንዳልገናኝ እያደረጉ ራስዎ ሲያቀርቡኝ አልነበረም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አንድ ቀን መጥተሃል።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_አንድ መኪና መድበው፣ ከጎኔ የደህንነት ሰራተኛ መድበው ከአባሪዎቼ ጋር እንዳልገናኝ አድርገው ሲያመላልሱኝ ነበር!

ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_ነበር!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ወደ ፍርድቤት ስመላለስ የነበረው በከፍተኛ ጥበቃነው። እስር ቤቱ ሲቃጠል ማግለያ ክፍል ነበርኩ። ሰው ገድሏል ብለው የመሰከሩብኝ በምን መልኩ ነው?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_መጀመርያ ታደራጅ ነበር።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ነሃሴ 28/2008 ዓም ዞን2 እና ዞን3 ሲቃጠል እኛ ያለንበት ክፍል ተከፍቶ፣መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ እና በቀለ ገርባ… እዛ ቤት ውስጥ የነበሩ እስረኞች በጥይት ይመቱ ብለው ትዕዛዝ አልሰጡም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልሰጠሁም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ቃጠሎው ከበረደ በኋላ ቤቱ ይከፈት ብለዋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ ይከፈትላቸው ብያለሁ።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_በቃጠሎው ወቅት፣ እየተቃጠለ፣ ጭስ ታፍኖ በነበረበት ወቅት ቃጠሎ ይደርስባቸዋል ሳይሉ ቃጠሎው ከበረደ በኋላ ይከፈት ያሉት ለእኛ ደህንነት ብለው ነው?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_:_መጀመርያ ይከፈት ሲባል እምብይ ስላላችሁ ነው።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ መጀመርያ ቃጠሎ ወቅት ሳትከፍቱልን ከበረደ በኋላ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_መጀመርያ እምብይ እንዳላችሁ አባሎች ነግረውኛል።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_እርስዎ እኔና በቀለ ገርባ እንድንገደል ትዕዛዝ ሰጥተው አባሎች (ፖሊሶች) አንከፍትም! አንገድልም አላሉዎትም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላዘዝኩም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_እስረኞች እንዲያመልጡ እቅድ እንደነበረኝ መስክረዋል። የእኔ እቅድ ማምለጥ ከነበር እንኳን ልክፈትልህ ተብዬ፣ ከፍቼ ለምን አልወጣሁም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ እሱን እርስዎ ነው የሚያውቁት!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_እሳት አደጋ ወደ ዞን 2 ገብቶ እሳቱን ለማጥፋት ሲጥር እርስዎ እሳቱን እንዳያጠፋ አስቁመውታል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላስቆምኩም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ዞን 3 የተቃጠለው እስረኞች ከወጡ በኋላነው?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ዞን2 በጥይት የተመቱትን ወንድሞቻችን ዞን 3 ወስዳችሁ አስከሬናቸውን በእሳት አላቃጠላችሁም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላቃጠልኩም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_እሳቱ እስከ ስንት ሰዓት ቆየ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላውቅም።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ክቡር ፍርድ ቤት እንደ አባል፣ እንደ አመራር በወቅቱ ነበርኩ ስላሉ ሰዓቱን እንዲናገሩ ጣልቃ መግባት አለበት!

ፍርድ ቤቱ:_ ስንት ሰዓት ነበር? ይናገሩ!

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ከሰዓት

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ከቃጠሎው ቀን በኋላ ቤቱ ሲፀዳ አስከሬን ተገኝቷል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልተገኘም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_በቃጠሎው ቀን ነሃሴ 28 የሟቾች አስከሬን ስንት ሰዓት ተነሳ?

ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_እኔ ውጭ ነበርኩ። አላየሁም።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_እሳት ቃጠሎው ከቆመ በኋላ ነው የሞተውን ሰው ቁጥር ያወቃችሁት?

ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_አዎ!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ከቀኑ 7 ሰዓት፣ ገና እሳት ቃጠሎው ሳይበርድ መንግስት በሚቆጣጠረው ኢቢሲ 23 ሰው ሞተ ተብሎ ተዘግቧል። የሀሰት መረጃ ሰጥተዋል ማለት ነው?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_የሀሰት ማስረጃ አልተናገርኩም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ታዲያ ከየት አምጥተው ዘገቡ? እሳቱ አልጠፋም። ለኢትዮጵያ ህዝብ የሀሰት ማስረጃ ሰጥተዋል ማለት ነው?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልሰጠሁም!

(መቃወሚያ ቀርቧል)

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ አንድ የዜና ወኪል ወይ ራሱ ተገኝቶ አሊያም ከመስርያ ቤቱ ጠይቆ ነው ዜና ሊሰራ የሚችለው። ምስክሩ ደግሞ በማረሚያ ቤቱ በኃላፊነት 2ኛ ሰው ናቸው።

ፍርድቤቱ:_ እሳቸው መረጃ ላይሰጡ ይችላሉ። በተለያየ መንገድ ልትጠይቅ ትችላለህ።

መቶ አለቃ:_ የሞቱ ወንድሞቻችንን አስከሬን ለቤተሰብ አስረክባችኋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ለፖሊስ ሰጥተን። ፖሊስ ለቤተሰብ ሰጥቷል።

መቶ አለቃ ማስረሻ:_የተገደሉትን እስረኞች ሰብስባችሁ ከቀበራችሁ በኋላ፣ ላዩ ላይ አሁን ዞን 5 የሚባለውን እስር ቤት ሰርታችሁበታል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልሰበሰብንም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ግድግዳው በጥይት ተመትቷል ወይ ተብለው ሲጠየቁ ተቃጥሏል ብለዋል። ግድግዳው ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_በጥይት መመታቱን አላየሁም!

መቶ አለቃ ማስረሻ:_ነሃሴ 28/2008 ዓም በቂሊንጦ ቃጠሎ ለጠፋው የሰው ህይወት እና ለወደመው ንብረት ተጠያቂ አይደለሁም ነው የሚሉት?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ተጠያቂ አይደለሁም!

አቶ አባዱላና አቶ በረከት መልቀቂያቸውን ስበዋል። ወደነበሩበት ተመልሰዋል። ( ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

አቶ አባዱላና አቶ በረከት መልቀቂያቸውን ስበዋል። ወደነበሩበት ተመልሰዋል። የህወሀት ልሳን ሬዲዮ ፋና ትላንት ይሄን ነገረን። የዛሬ ሳምንት ሌላው አፍቃሪ ህወሀት ‘ሪፖርተር’ ጋዜጣ የአቶ አባዱላ መልቀቂያ ተቀባይነት አገኘ ሲል በፊት ገጹ አውጥቶ ነበር። ያኔ ‘ወንድ ልጅ ቆረጠ’ ብለን የአባዱላን ውሳኔ ታዝበን ነበር። ከወራት በፊት አቶ ሃይለማርያም በምክር ቤት ተገኝቶ የአቶ በረከትን መልቀቂያ በተመለከተ ‘በረከት ደክሞታል። እስቲ ይረፍ። ጥያቄውን ተቀብለናል’ ብሎን ነበር።

ሁለቱ ሚዲያዎች ሪፖርተርና ፋና ለህወሀት የስስት ልጆች ናቸው። ቤተኛ ናቸው። አንዱ የስለት ልጅ በሚል ካልተበላለጡ በቀር ከህወሀት አንጻር የሚለያቸው ምንም ነገር የለም። ከፈረሱ አፍ ወሬውን እንደሚያቀብሉ አይጠረጠርም። በአንድ ሳምንት ልዩነት ሁለት ፍጹም ተቃራኒ ወሬዎችን ሲነገሩን ግን የህወሀትን የጤንነት መቃወስ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጥሩ ምልክት እንዲሆነን አድርጓል። በሀወሀት ውስጥ የሃይል መሳሳብ እንዳለ፡ ፍትጊያው እንዳልተቋጨ የሚያረጋግጥም ነው። አንዳንዶች ሆን ብሎ ህዝቡን ለማደናገር፡ የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት ነው ብለው የህወሀትን የሴራ ፖለቲካ ከኋላ ተንደርድረው በመነሳት ይተነትናሉ። ህወሀት አሁን ካለበት ጽኑ ህመም አንጻር እንዲህ ዓይነት ጨዋታ አቅሙ ይፈቅድለት ይሆን?

ሃይለማርያም በእርግጥ እንደነገሩት ነው። ደብረጺዮን ደውሎ እንዲህ በል ካለው ከረባቱን ገጭ አድርጎ ማይክ ይዞ ይለዋል። በረከት ጠርቶት እንደዚያ በል ካለው ደግሞ ሌላ ይላል። የነገሩትን ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ምን እየተደረገ እንደሆነ የሚያውቅ አይመስለኝም። አንዳንድ ጊዜ ከህዝብ እኩል በቴሌቪዥን የሚሰማ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እናም የሃይለማርያምን እንተወው። ከሁለቱ የህወሀት አፈቀላጤዎች ግን የማንን እንመን?

አቶ አባዱላ ”የህዝቤ ክብር ሲነካ ማየት አልቻልኩም” ብሎ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ያለ ዕለት ያልጠበቁት ሲገረሙ፡ ያልጣማቸው ሲያጣጥሉ፡ ህወሀቶች ደግሞ ሲራገሙ ነበር። አባዱላ በተለይ በጨፌ ኦሮሚያ አዳራሽ የብአዴን ልደት ሲከበር የተናገረው ‘ሰውዬው እውነትም ቆርጧል’ የሚል ስሜት በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል። ወደ ‘ሰውነት ተራ’ ለመመለስ የምሩን ወስኗል በለው የተቀበሉ ጥቂቶች አይደሉም። ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ልዩ መብት በአዲስ አበባ የሚለው የፓርላማ የህዝብ ውይይት የተበተነ ጊዜ የያዘው አቋም ደግሞ ‘በሽታው ተመለሰበት እንዴ? ሳያገረሽበት አይቀርም’ የሚል አስተያየት እንዲሰጥበት አድርጓል።

አባዱላ መልቀቂያ ካቀረበበት ቀን ጀምሮ የህወሀት የሚዲያና የፌስ ቡክ ሰራዊት የስድብ ናዳውን ማዝነቡን አላቋረጠም። ከሀገር ቤት እስከባህር ማዶ የተጋሩ ማህበራት በሰልፍ አባዱላ ላይ የእርግማን መዓት፡ የውግዘት ጎርፍ ፡ ሲያወርዱ ከርመዋል። ”ምርኮኛውን ወታደር ሰው ባደረግን” ፡ ”ከአፈር አንስተን ስልጣን በሰጠን” እንዴት ተደፈርን ያለው የህወሀት መንደር ‘አባዱላ ይሰቀል’ ብሎ መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል። ”የህዝቤ ክብር ተነካ” የሚለው የአባዱላ መግለጫ የተጋሩን ሰፈር በንዴት ማጬሱ እርግጥ ነው። ሁሌም ”የበላይነት” ከአምላክ የተሰጣቸው ክብር፡ ከሰማይ የተቸራቸው ጸጋ፡ የትኛውም ምድራዊ ሰው መግፈፍ የማይችለው ሞገስ አድርገው የሚቆጥሩት የተጋሩ ሰፈር ልጆች በአባዱላ መግለጫ መንጨርጨራቸው የሚጠበቅ ነበር። የአባዱላ ”የህዝቤ ክብር ተነካ” መግለጫ በተጋሩዎች መዝገበ ቃላት ‘ለህወሀት ውርደት’ የሚል ፍቺ አለው። ይህ የተጋሩዎች ጩሀት አባዱላ ላይ ጫና መፍጠሩ አልቀረም።

የህወሀት መሪዎች ከተጋሩ መንደር የሚስተጋባውን ‘አባዱላ ይሰቀል’ እሪታ በዝምታ የሚያልፉት አልነበረም። በዚህም በዚያም ብለው፡ እጅ ጠምዝዘው የአባዱላን ውሳኔ ሊያስቀይሩ የመቻላቸው ዕድል ሰፊ ነው። የአባዱላ አቋም ምን እንደሆነ አሁንም አልሰማንም። ውለታቸው ተሰምቶት፡ የውስኪ ብርጭቆ ሲያጋጭ ለዘመናት ከቆያቸው ህወሀቶች ጋር መፋታት ከብዶት፡ ውሳኔውን ሊቀለብስ ይችላል። ”ከኦነግ በላይ ለኦሮሞ ህዝብ የሚቀርበው ህወሀት ነው” ከሚለው ጥግ የደረሰ አቋሙ በብርሃን ፍጥነት ወደ ”የህወሀት የበላይነት አለ። የህዝቤ ክብር ተነካ” ውሳኔ የተለወጠው አባዱላ በዚያው ፍጥነት ”መንገድም ብርሃንም ህወሀት ነው” ቢል ሊደንቀን አይገባም። የህወሀቶች ነርቭ እስኪነካ ያንቀጠቀጣቸውን መግልጫ አባዱላ የሰጠው በህዝብ ማዕበል፡ በቄሮዎች አመጽ ግፊት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ህዝባዊ ንቅናቄው አሁን ካለበት ደረጃ ይበልጥ ከተፋፋመ አባዱላ ብቻ ሳይሆን ህሊናውን ሆዱ ስር የወሸቀ የህወሀት ተላላኪ በሙሉ ተጠራርጎ ሰልፉን ማሳመሩ የማይቀር ነው።

እንግዲህ ማንን እንመን? ሪፖርተርን ወይስ ሬዲዮ ፋናን? ዛሬ የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሶስት ሳምንት ያደረገውን ዝግ ስብሰባ በተመለከተ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። የአባዱላና የበረከት ወደነበሩበት መመለስ በመግለጫው የሚነገረን ከሆነ ከሪፖርተርና ከሬዲዮ ፋና የስለት ልጅ የትኛው እንደሆነ እንለያለን። በእርግጥ ሪፖርተር ህወሀት አደጋ ላይ ሲወድቅ ሰልፉን አስተካክሎ የውሸት መረጃዎች እየለቀቀ ህዝቡን በማደናገር፡ ህወሀትን ለማዳን ምሽግ የሚገባ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስመስክሯል። አቶ መለስ የሞተ ጊዜ አስክሬን ከቤት አስቀምጦ ‘መለስ ለእረፍት አሜሪካን መሄዳቸው ታወቀ’ የሚል ዜና በፊት ገጹ ማውጣቱን እናስታውሳለን። ሬዲዮ ፋና የህወሀት ልሳን በመሆኑ እያደረገ ካለው የተለየ ነገር አይጠበቅበትም።

አሁንም ቢሆን መጨረሻውን ማየቱ የተሻለ ነው። ተስማማን አሉ እንጂ ስለመስማማታቸው የሚያረጋግጥ ነገር የለም። ስርዓቱ የሚገኝበት የቀውስ ቁመና በየሰዓቱ በሚዋዥቅ አቋም ከወዲህ ወዲያ ሲወዛወዝ እያየነው ነው። ህወሀት ክፉኛ ቆስሏል። ከዚህ በኋላ ቆሞ ለመራመድ የሚያስችል ስነልቦናም ሆነ አካላዊ ብቃት የለውም። እንደውም የአባዱላና የበረከት የመመለስ ውሳኔ እውነት ከሆነ የሚነግረን ህወሀት የመቃብር ጉዞው ከጠበቅነው በላይ እየፈጠነ መምጣቱን ነው። ሁለቱም ነባር የኢህአዴግ አመራሮች ህወሀትን እንዲታደጉት ተፈልጓል። ተረባርበው፡ በድርጅት ውስጥ ያላቸውን መዋቅራዊ ተቀባይነት ተጠቅመው ህወሀትን ከመቃብር አፋፍ እንዲመልሱት ነው። ከዚህ ያለፈ ሌላ ሚስጢር የለውም። ሰው ጨው አይደለም። አይቀመስም። አባዱላ ምን እንደሚያስብ አናውቅም። ህወሀትን ማዳን ወይስ የኦሮሞ ህዝብን የነጻነት ጥያቄ መደገፍ? ለአባዱላ የቀረቡ ሁለት ምርጫዎች ናቸው። ስለበረከት ብዙም ማለት አያስፈልግም። በረከት ምርጫ የለውም። ከህወሀት ጋር አብሮ አፈር ከመልበስ ውጪ ምን ዕድል አለው?

በኢትዮጵያ የሚጠበቀው ለውጥ ከኢህአዴግ መንደር የሚመጣ ነው ብሎ የሚያምን ጅል የለም። የዝሆኖች ጥል ሞታቸውን ያፋጥናል ከሚል በቅርበት ተከታተልነው እንጂ የእነሱ መንገድ ወደ ነጻነት ይወስደናል ብሎ የጠበቀ ካለ በቶሎ የአእምሮ ህክምና መውሰድ ያለበት ሰው ነው። እነለማ/ገዱ የጀመሩትን እንቅስቃሴ በአወንታዊ ጎኑ የተቀበልነው የህወሀትን ሞት ስለሚያፋጥነው ነው። ከዚያ ያለፈ ምክንያት የለውም። እነሱም ወደዚህ ተስበው የገቡት በህዝቡ የለውጥ እንቅስቃሴ ነው። ህወሀት በባህሪው ውስጣዊ ሽኩቻ ስጋውን ይጨርሰዋል። ነፍሱ ሲጥ እስክትል ይደርሳል።

በኢትዮጵያ የምናንፍቀው ለውጥ ብዙ መስዋዕትነት እንዳያስከፍል ከተፈለገም አገዛዙ መንደር የፈነዳውን ፍጥጫ ወደለየለት ጦርነት እንዲቀየርና እርስ በእርስ ተበላልተው እንዲያልቁ በማድረግ መሆኑ ይታመናል። እነለማ/ገዱ ያን መንገድ ሲጀምሩት ህወሀትም ወደ መቃብሩ የጀመረው ጉዞ በእጥፍ ፍጥነት ቀጥሎ ነበር። ያን ፍጥነቱን ለመቀነስ እየተረባረበ ነው። እነአባዱላን እንዲመለሱ የሚያደርገውም ወደዘላለማዊ ጉድጓዱ መቃረቡ ብርክ ስላዚያዘው መሆኑን መገመት አይከብድም። ግን ደግሞ አይቀርለትም። የተቀጣጠለው የህዝብ እምቢተኝነት የህወሀትን ሞት በቅርቡ ዕውን ማድረጉን ቅንጣት ታህል መጠራጠር አይገባም።

አባዱላ የማያድነው፡ የበረከት መመለስ የማይፈውሰው፡ የእነለማ/ገዱ መለሳለስ የማይሽረው፡ የተጋሩዎች እሪታና ኋይታ የማያስታግሰው ጽኑ ህመም ህወሀትን እያሰቃየው ነው። ከዳር እስከዳር የተቀጣጠለው የህዝቡ የለውጥ ትግል ህወሀትን ገድሎ አፈር ሳያለብስ አይመለስም። ህዝብ ወስኗል። ቆርጧል። ህወሀትን ከነጉድፉ፡ ከነግሳንግሱና ግብስብሱ፡ ተጠራርጎ ከሚወገድበት ስርነቀል ለውጥ ላይ ያደረሰው ህዝባዊው ትግል ወደኋላ የሚመለስ አይደለም።