የለውጥ ሀይሉ እውነተኛ ከሆኑ ስራቸውን ይስሩ እኛም ስራችን እንስራ:: ማገዝ የሚለውን ቃል አልወደውም ::(በ ርዕዮት አለሙ)

በ ርዕዮት አለሙ

የለውጥ ሀይሉ እውነተኛ ከሆኑ ስራቸውን ይስሩ እኛም ስራችን እንስራ:: ማገዝ የሚለውን ቃል አልወደውም :: ምንድን ነው ማገዝ ማለት ለመሆኑ ? እኔ እኮ ኢትዮጵያ ሀግሬን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ድሮ ያኔ ለትግል ስነሳ ዶር አብይ የሚባል ሰው ከነመፈጠሩም አላውቅም ::

የ ትግሌ አላማ እና ግብ ዶር አብይን ለማገዝ አይደለም አይሆንምም… አላማየ ኢትዮጵያ ሀግሬን ዲሞክራሲት የማድረግ ትልቅ ራዕይ ነው:: እኔ ይህ አላማየ እስኪሳካ ትግሌን እቀጥላለሁ:: በዚህ የ ትግል ጎዳና ላይ እያለሁ ዶር አብይ የሚባል ሰው ከ ኢህአዴግ ወጥቶ አይ እየሄድንበት ያለው መንገድ ልክ አይደለም ብሎ ኢትዮጵያን ለመቀየር ከተነሳ እሽ ጥሩ …ይህ ከሆነ ትክክለኛ ስሜቱ ደግ ነው:: እኔም ትግሌን እቀጥላለሁ መንገድ ላይ እንገናኛለን:: ነገር ግን እየሆነ ያለው ነገር ይህን አያሳይም::

በ ግልፅ በ አደባባይ ሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሀቅ ግን ተስፋ ሰጭ አይደለም …እንደተባለለትም ወደ ዲሞክራሲ እየሄድን አይደለም…አንድ አንዶች ይህን ጥሬ ሀቅ እያዩ ዶር አብይን ከማገዝ ውጭ ምን ምርጫ አለ ለምትሉ መልሴ ምርጫ ካሳጡ በሗላ ምን ምርጫ አለ ይባላል እንዴ ? እየሆነው ያለው እኮ ምርጫ የማሳጣት ነገር ነው::

ለምሳሌ አሁን የተፈጠረውን ችግር ከስሩ እንመልከተው:: የ አዲስ አበባ ወጥቶች ለምን ለመደራጀት ተነሱ ብሎ መጠየቅ ደግ ነው? ሆሮሞሳ ፊንፊኔ በሚል ስም የተደራጁ ወይም እንዲደራጅ ያደረጉ ሰወች እኮ በ አደባባይ የ ጥላቻ ንግግር ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው ይህም ይታወቃል:: እነዚህ ሰወች ተሰብስበው ምን ነበር ሲያወሩት የነበረ ? የ ሚያቃቅር የሚያጣላ የምያጋጭ አይደለም ን? እነዚህ ሰወች ተደራጅተው የፍለጉትን እንዲናገሩ እየተደረገ ነው :: እንዲህም እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል::

በሌላ በኩል ይህን አደጋ የተገነዘቡ የ አዲስ አበባ ወጣቶች የ አዲስ አበባን ወጣት ለማደራጀት ሲሞክሩ አንጠልጥለው እስር ቤት ወረወሯቸው:: እነዚህ ወጥቶች ሄኖክ እና ማይክ ወንጀላቸው ምንድን ነው ? ወንጀላቸው መደራጀት ነው ተባለ …

ይህ ግልፅ መድሎ ነው ! ለ አንዱ መፍቀድ ሌላውን መከልከል ብቻ እንኳ አይደለም ልትደራጅ ነው ብሎ ማሰር ! እዚህ ውስጥ የ ዶር አብይ እጅ የለበትም ብሎ ነገር አይጥመኝም… ጥሩ ጥሩውን ለ ዶር አብይ እንዲህ አይነት ግፍ እና በደሉን ለ ለውጥ ቀልባሾች መስጠት ትክክል አይደለም::

ሲጀመር የለውጥ ሀይሉ የ ለማ ቲም የሚባለው ቁጥራቸው ስንት ነው እነማን ናቸው የሚባለው ነገር ግልፅ አይደለም::

ሌላው የሚገርመው ነገር የ ቤተመንግስቱ የ ወታደሮች ሁኔታ ነው:: በ እለቱ ዶር አብይ ወጥተው ከ ደሞዝ ጋ የተያያዘ ነው አሉን ከዛም ከዚህ በተቃራኒ መረጃ አለን ያሉትን ሰወች ውሸታማሞች አስባሉ::

አሁን ወጥተው አይ ያን ጊዜ የነገርኳችሁ እውነት አይደለም ሌሎች ያሉት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ትክክል ነበረ አሉን :: እንግዲህ ከሁለቱ የቱን እንመን ሲባል ያንም ይህንም እመኑኝ የሚሉት ነገር ነው:: እኔ ያ ነው ይህ ነው የሚል ክርክር ውስጥ አልገባም ነገር ግን ሁለቱንም እመኑኝ የሚሉት ነገር ትክክል አይደለም:: ስለ ሰበታ ለጋጠፎ እና ቡራዮ የተናገሩት ነገር የሚገርም ነው ! እውነት እየመጡ ነበር የሚለው ነገር እንዳለ ሁኖ ለማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል :: እኔ የሚታየኝ ድራማ ነው ለምን እንዲህ አይነት ድራማ ለመስራት ተፈለገ::

ማሳስቢያ::
ይህን ፅሁፍ የ ፃፍኩት ርዕዮት አለሙ በ ኢሳት እለታዊ ያደርገችውን ውይይት ተመርክዤ ቢሆንም ንግግሩን ወደ ፅሁፍ ሲገለብጥ ትንሽ ማጣፈጫ ተጠቅሚያለሁ::
CC Eskedar Alemu Gobebo

“የአዲስ አበባ ፓሊስ” ለሉአላዊ ባለቤቱ ይመለስ! ከኤርሚያስ ለገሰ

“የአዲስ አበባ ፓሊስ” ለሉአላዊ ባለቤቱ ይመለስ!
ከኤርሚያስ ለገሰ
የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጄር ጄኔራል ደግፌ በዲ በወቅታው የመዲናይቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ የሰጡትን መግለጫ ሰማሁት። ኮሚሽነሩን በተሰጣቸው ሃላፊነት እና ስልጣን የማክበር የዜግነት ግዴታ አለብኝ።እንደ አንድ ዜጋ እና ድምፅ አልባ ለሆነው አዲስአበቤ( በአዲስ አበባ በፍላጐቱ የሚኖር) እንደሚቆረቆር ሰው ደግሞ ቅሬታዮን የማቅረብ መብት አለኝ።
በመግለጫው ጄኔራሉ ላለፉት 27 አመታት የሰማነውን የመነቸከ አካሄድ እንደ ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ የህግ የበላይነት ሳይሆን የሕጉ የበላይ መስለው ታይተዋል። ሰውየውን ያለ ዛሬ አይቼአቸው ባላውቅም ከአንደበታቸው የሚወጣው አምባገነናዊ አቋምና እብሪት በተራዘመ ሂደት ስርአቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊወስደው ይችላል። በተለይም ጄኔራሉ እንደ ዛሬው በአክራሪዎቹ ተጠልፈው አይጥ በበላው ዳዋ እየፈለጉ የሚገድልና የሚያስሩ ከሆነ ለለውጥ ሀይሉ ከባድ ሸክምና እዳ መሆናቸው አይቀርም።
እዚህ ላይ የለውጡ መሪ ለሆነው ዶክተር አቢይ አንድ በጥሞና ማየት አለበት ብዮ የማስበውን ቁምነገር ላስገባ። የመጣጥፉም መዳረሻ ይሄ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው ከምርጫ 97 በኃላ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ጋር በተያያዘ አቶ መለስ ሶስት ትላልቅ አምባገነናዊ እርምጃዎች ወስደዋል። በቅርበት ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሠይጣናዊ እርምጃዎች መዲናይቱን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለዋታል። በዚህ ምክንያት የተፈጠረው ችግር ፓለቲካዊ እና መዋቅራዊ በመሆኑ መፍትሔውም ፓለቲካዊ መሆኑ አይቀርም።

#የመጀመሪያው የአዲስ አበባና የአዲስ አበቤን ሉአላዊነት (በራሳቸው ህገ መንግስት አንቀፅ 49 የተጠቀሰውን) በመናድ የመዲናይቱን ፓሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለፌዴራል መንግስት አድርገዋል። በሌላ አነጋገር አዲስ አበባም ሆነ የህዝቡ ሉአላዊነት መገለጫ ተደርጐ የሚወሰደው “የከተማው ምክርቤት” የአዲስ አበባን ፓሊስ የማዘዝ መብት የለውም። በዳቦ ስም “የአዲስ አበባ ፓሊስ” ይባል እንጂ በግብር፣ በተጠሪነት እና ተጠያቂነት አዲስአበቤ አይደለም። እዚህ ላይ ሌላም አስገራሚ ነገር ልጨምር። ለነገሩ አስገራሚ ከምለው አስቂኝ ብለው እመርጣለሁ። ነብሷን ይማረው እና ወላጅ እናቴ ከአቅሟ በላይ የሆነ ነገር ሲያጋጥማት “ ወደው አይስቁ!” ትለን ነበር። ወደው አይስቁ! እናም አስቂኙ ነገር አዲስአበቤ ባለቤት ላልሆነበት፣ ተጠሪው ላልሆነ፣ ለማይጠይቀው “ የአዲስ አበባ ፓሊስ” በጀት ይመድባል። የሉአላዊነቱ አካል ያልሆነውን ፓሊስ ይቀልባል።
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር! መቼም የአለም ሶስተኛ የዲፕሎማሲ ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የኢትዮጵያውያን ዋና መናገሻ የምታዘው ፣ ተጠያቂ የምታደርገው ፓሊስ የላትም ብሎ እንደ መናገር የሚያሳፍር የለም። እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም እርሶም በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የፓለቲካ ቧልትና ጠላታዊ እርምጃ የሚሸማቀቁ ይመስለኛል።
በእርሶ የስልጣን ዘመን ይህን ውንብድና በማስተካከል በቀድሞው ስርአት ፓለቲካ ቁስለኛና ሰለባ የሆነውን አዲስአበቤ ከይቅርታ ጋር እንደሚክሱት ሙሉ እምነት አለኝ። በአዲስ አበባ ፓሊስና አዲስአበቤ መካከል የተጋረደውን መጋረጃ ቀዳደው ለመጪው በነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለሚመጣው የአዲስ አበባ መንግስት እንደሚያስረክቡ ጥርጥር የለኝም።
#ሁለተኛው የአቶ መለስ የውስጥ መመሪያ የፓሊስ ምልመላና ስልጠናን የተመለከተ ነው። ከምርጫ 97 ጀምሮ ለነበሩት ሶስት አመታት የአዲስ አበባ ፓሊስ ለመሆን በሚደረገው ምልመላ ለአዲስአበቤ የሚሰጠው ኮታ 10 በመቶ በታች ነበር። በሂደትም ከሃምሳ በመቶ የሚበልጥ አይደለም። የተቀረው ግማሹ በኮታ ከሌሎች አካባቢዎች ተመልምሎ የሚመጣ ነው።ከኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ…ወዘተ። ከሌላ አካባቢ የሚመጡት ፓሊሶች ደግሞ ከከተሜው ባህሪ ጋር መላመድ ስለሚያቅታቸው ነዋሪው እንደሚንቃቸው ስለሚያስቡ በበታችነት ስሜት ይሰቃያሉ። በተበቃይነት ስሜት መንፈሳቸው ይረበሻል። ፈሪና ድንጉጥ ፍጡር ይሆናሉ። ፈሪ ሰው ደግሞ ሁሉንም ሰው ጠላት ያደርጋል።
በፓሊሱና በከተማው ነዋሪ መካከል ያለው ግንኙነትም የፋራና አራዳ ፣ የተታላይና አታላይ፣ የከተማ ቀመስና ከተሜ፣ የሰገጤና ጩሉሌ መሆኑ አይቀርም። በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ፓሊስ አባላትና አዲስአበቤ መካከል ያለው ግንኙነት ከፍተኛ የመተማመን እጦት ያለበት ሆኗል። ነዋሪው እንኳን በሲነርጂ አብሮ ሊሰራ ቀርቶ በመንደሩ ያስቸገረ ሌባን ለፓሊስ አሳልፎ መስጠት አይፈልግም። ፓሊስ በፓትሮል ለአሰሳ ሲመጣ “ ዛፓው! ሰገጤው! እየመጣላችሁ ነው ወደ ቤት ግቡ!” የምትለው የአራዶች ቃል በእናቶቻችንም ዘንድ የተለመደ ሆኗል።
የምልመላ መስፈርቱም የኢህአዴግ ሊግ አባል (60 ነጥብ)፣ የወጣት ፎረም አባል (20 ነጥብ)፣ የትምህርት ዝግጅት እና ሌሎች የጤና መመዘኛዎች (20 ነጥብ) ነበሩ። በሌላ አነጋገር አዲስአበቤ የኢህአዴግ የወጣት ሊግ ውስጥ መታቀፍ ካልፈለገ ፓሊስ የመሆን የልጅነት ህልም ቢኖረው እንኳን ፓሊስ መሆን አይችልም። በዚህ እኩይ ተግባር ሁላችንም የታሪክ ተወቃሾች ነን። የታሪክ ተወቃሽነት የሚያመጣው ድርጊቱን መፈፀም አሊያም አጋዥ መሆን ብቻ አይደለም። መጥፎው ውሳኔ እንዳይተገበር ለመከላከል ቁርጠኝነት አልፎ ሔዶም ማጋለጥ አለመቻል በዚህ ፈርጅ ይመደባል።
እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከላይ የጠቀስኩት አካሄድ እንዲሁ ቢቀጥል አዲስአበቤ ለእርሶ ያለው ድጋፍ ከተወሰነ በኃላ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይችላሉ። የመዲናይቷን ሰላም የሚያስጠብቀው ክፍል ውስጥ ባለቤቱ ከሌለበት እና ባይተዋር ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ በሂደት እርሶንም በባላንጣነት የሚመለከትበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በመሆኑም በእርሶ የስልጣን ዘመን ይሄን ያልተፃፈ የውስጥ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ያስቁሙ። የኦሮሚያ ክልል ፓሊስ አባላት በኦሮሚያ የሚኖሩ ዜጐች እንተደረገ ሁሉ፣ የአማራ ክልል የፓሊስ አባላት በአማራ ክልል እንደሚመለመሉ ሁሉ…ወዘተ በአዲስ አበባ ክልልም የሚመለመሉ ፓሊሶች አዲስአበቤ( በፍላጐቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ) ብቻ እንዲሆኑ አድርጉ። መመዘኛውም እንደ እርሶ ሙሉ ቁመና ያለው፣ ፓሊስ ሆኖ ማገልገል ፍላጐት ያለው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ በፀባዩ ተቀባይነት ያለው/ ያላት ያድርጉ። የፓርቲ አባልነት እንደ መመዘኛ መወሰዱ ፀያፍ እንደነበር በአደባባይ ይግለጡ።
#ሶስተኛው ከአዲስ አበባ ፓሊስ አመራር ጋር የተያያዘ ነው። አስቀድሜ እንደገለጥኩት ከምርጫ 97 በኃላ የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራር የሚመደበው ከፌዴራል ፓሊስና መከላከያ ሰራዊት ነው። በተለይም ቁልፍ ስራ የሆነውን አዛዥነት፣ ወንጀል መከላከል እና ምርመራ መምሪያ የሚያዘው ለፓርቲው ታዛዥ የሆኑ የፌዴራል ፓሊስና የመከላከያ መኮንኖች ናቸው። ይሄ በራሱ የፈጠረው ችግር አለ።
ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆንብኝ እንጂ የፓሊስ አመራር ሳይንስም ጥበብም ነው። ሳይንስ በመሆኑ ፕሮፌሽናሊዝም እና ምሁራዊ ግንዛቤ ይጠይቃል። ጥበብ በመሆኑ የሰዎችን አእምሮ የሚማርኩ ስልቶችን ማወቅ ይጠይቃል። የፓሊስ አመራር ከሌሎቹ ሙያዎች በተለየ ረቀቅ ያለ ጥበብ ይጠይቃል። በእውቀት፣ በችሎታ፣ በእምነትና ሕዝብ ለሚቀበለው መርሕ መቆምን ይጠይቃል። የሕግ የበላይነትን አምኖ መቀበል ይጠይቃል።
ስለዚህ የፓሊስ አመራር መሆን ያለበት እንደ ድሮው በፓሊስ ኮሌጅ ገብቶ በከፍተኛ መኮንንነት የሰለጠነ ፕሮፌሽናል ሰው ሊሆን ይገባል። የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራል ተመልሶ ፓሊስ ኮሌጅ ገብቶ የአራት አመት ስልጠናውን ካልወሰደ በስተቀር ወደ ፓሊስ አመራርነት መምጣት የለበትም። አሁንም ድፍረት አይሁንብኝ እና አንድ የመከላከያ ሰራዊት መኮንን ስልጠናም ሆነ የአእምሮ ኦረንቴሽኑ ወታደርተኝነት ነው። ጠላትን የማንበርከክ ጀብደኝነት እና የጦረኝነት ዝንባሌ ነው።
ነብሱን ይማረው እና አቶ መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራሮችን ከመከላከያ ሲያመጣ አዲስአበቤን እንደ ጠላት፣ አዲስ አበባን እንደ ጦርነት አውድማ ስለሚቆጥራት ነበር። የአቶ መለስ የጦረኝነት ጽንሰ ሐሳብ የሚመነጨው መዲናይቱን መቆጣጠር የሚቻለው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ በታነፀ ወታደራዊ ኃይል ነው ከሚል እምነት ነው። በጠላትነትና በአደገኛ ቦዘኔነት የፈረጀውም አዲስአበቤ ወጣት ፀጥ ረጭ ማድረግ የሚቻለው በዚህ አይነት የጦር አመራር መሆኑን ያምናል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርሶም በማወቅም ይሁን የቀድሞ አሰራር ትክክል መስሎት የፓሊስ አመራርን የቀየሩበት አሰራር ተመሳሳይ ነው። እርሶም ለአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽርነት የሾሙት የመከላከያ ሜጄር ጄኔራል ሆኗል። ሰውየው የፓሊስ አካዳሚ ገብተው ስልጠና መውሰዳቸውን ባላውቅም ከአነጋገር ለዛቸው ከወታደርተኝነት የተላቀቁ አይመስለኝም። ዶሮ ሶስት ጊዜ ሳትጮህ ጠርብ ጠርብ የሚያካክሉ ኩሸቶችን ሲያወሩ አንደበታቸው አልተደናቀፈም። መስከረም 4፣ መስከረም 5 የሰጡት መግለጫ መስከረም 14 ከሰጡት ጋር እርስ በራሱ ሲደባደብ ከመጤፍ አልቆጠሩትም( የእነዚህ ቀናት አስቂኝ ድራማ በሌላ ጽሁፍ እመጣበታለሁ።) ጆሮአቸውን በጥይት የደፈኑት እኝህ ጄኔራል ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ አይችሉም የሚለውን የህገመንግስት ቃል አንብበውት የሚያውቁም አይመስልም። በአመራር ሳይንስ ውስጥ ቅድሚ ለሚሰጥ ቅድሚያ እንስጥ በሚለው ጥበብ አጠገቡ ያለፉ አይመስልም። የጄኔራሉ አድርባይነት እና የስልጣን ብልግና ከወዲሁ ቁልጭ ብሎ ወጥቷል።
በመሆኑም እንዲህ አይነት ወታደርተኝነት ግርዶሽ የጣለባቸውን የጦር መኮንኖች ያለምንም ስልጠና ሕዝብ ውስጥ መቀላቀል ጦሱ ብዙ ነው።አዲስአበቤ በለውጡ ላይ ያሳደረው አመኔታ ይሸረሽራል። በነዋሪው አንድ “ወዴት እየሔድን ነው?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በጠቅላላው አነጋገር በዚህ ዙሪያ የሚታየው ስህተት በቀላሉ የሚታረም አይደለም። የመጀመሪያው ድንጋይ ከመወርወሩ በፊት መሰረታዊ የሆነ የአመራር ስርአት ለውጥን ይጠይቃል። መሪ መለወጥም ግድ ይላል። ከእንግዲህ በኃላ አዲስአበቤዎች በቀቢጸ ተስፋ የሚኖሩ አይደሉም። እንደ ጥቁሩ አሜሪካዊ የመብት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ህልም አላቸው። አንድ ቀን አዲስአበቤዎች በነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ራሳቸውን ያስተዳድራሉ።

አብዲ ዒሌ እስር ቤት ገብቷል። በረከት ስምዖን የውርደትን እፍታ ቀምሷል። ጌታቸው አሰፋ የሚደበቅበት ጉድጓድ ፍለጋ ላይ ተጠምዷል። (በመሳይ መኮንን)

አብዲ ዒሌ እስር ቤት ገብቷል። በረከት ስምዖን የውርደትን እፍታ ቀምሷል። ጌታቸው አሰፋ የሚደበቅበት ጉድጓድ ፍለጋ ላይ ተጠምዷል። አባይ ጸሀዬ ድምጹን አጥፍቷል። ስብሃት ነጋ በመቀሌ አክሱም ሆቴል ውስኪውን እየላፈ ቆዝሟል። በእብሪትና ትዕቢት ያበጠው የጌታቸው ረዳ ልብም ተንፍሷል። ሳሞራ የኑስ የጡረታ ዘመኑን በስጋት ይገፋል። አስመላሽ ወ/ስላሴ ግን አሁንም ይፎክራል። ሞንጆሪኖም ”የትላንቱ ይበጀናል” ዜማ እያቀነቀነች በትካዜ ተውጣለች። ደብረጺዮን መሀል ላይ ይዋልላል። አዲስ አበባ ሲደርስ ይደመርና ወደ መቀሌ ሲመለስ ይቀነሳል።

ወደ ለውጡ ቅጥር ግቢ ለመግባት አጥር ላይ የተንጠለጠሉ አንዳንድ የህወሀት አመራሮች እንዳሉ ይሰማል። የህዝብ ማዕበል ወደ ለውጡ ይጎትታቸውና የነባሮቹ ህወሀቶች ቁንጥጫ ይመልሳቸዋል። አጥሩ ላይ እንደተንጠለጠሉ አራት ወራት አለፋቸው። ህወሀቶች ዘይቱን ሳያዘጋጁ ሙሽራው መጥቶባቸዋል። ዘይቱ ንሰሀ ነበር። ሙሽራው ደግሞ ለውጥ። እናም ዘይቱን ያላዘጋጀ ሙሽራውን እንዴት ይቀበለው?

ባለፈው ሳምንት አንድ የናዚ የጦር ወንጀለኛ ለ70 ዓመታት ከተደበቀባት አሜሪካ ለጀርመን ተላልፎ ተሰጥቷል። በ95 ዓመቱ በእጆቹ ላይ ሰንሰለት ጠልቆ ከርቸሌ ገብቷል። በእኛም ታሪክ ተመሳሳይ ክስተት ተመዝግቧል። በቀይ ሽብር ዘመን መሪ ተዋናይ የሆኑ ነፍሰ ገዳዮች ለዘመናት ከተደበቁባቸው ሀገራት ማንቁርታቸው እየታነቀ ለፍርድ ቀርበው አይተናል። የቀልቤሳ ነገዎን እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል። ከፍትህ ለጊዜው ማምለጥ ይቻል ይሆናል። ቢዘገይም ግን አይቀርም። ሞት ቢቀድም እንኳን ነፍስ ዘላለሟን እረፍት ታጣለች። መለስ ዜናዊ ለፍርድ ሳይቀርብ ቢሄድም ስሙ በምድር እየተረገመ፡ ነፍሱ በሰማይ እየተሰቃየ ነው። ከመቃብር በላይ ትቷት ያለፈው በዘር ልትበጣጠቅ ጫፍ የደረሰች ሀገር ነበረችና መለስ ከምድራዊ ፍርድ ቢያመልጥም ዘላለማዊ ስሙ የተወገዘ፡ የረከሰ ሆኗል።

ጌታቸው አሰፋ ለጊዜው ከፍትህ ተደብቋል። እንደሰማሁት በኢንተርፖል ራዳር ስር እንዲሆን እንቅስቃሴው ተጀምሯል። ወደ አሜሪካ ያሸሻቸው ቤተሰቦቹ ዘንድ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል። ከፎቶና ከቪዲዮ ተደብቆ ስለኖረ በቀላሉ ላይታወቅ ይችላል። ግን አያመልጥም። እየተሽሎከለከ እድሜውን ሊያቆይ እየሞከረ ነው። ከመደበኛው ፍርድ ለጊዜው ሊሸሸግ ይችላል። ከምንም በላይ ከህሊና ፍርድ አያመልጥም። በሄደበት የሚከተለው ትንሹ እግዚያብሄር የሆነው ህሊናው እረፍት ሲነሳው ይኖራል። የኢትዮጵያ እናቶች እምባስ መች በከንቱ ፈሶ ያውቅና?

ህወሀቶች ጸሀይ እየጠለቀችባቸውም የተሰጣቸውን እድል መጠቀም አልቻሉም። ሰሞኑን ከመቀሌ ተሰብስበው ያወጡት መግለጫ ጥርሱ አልቆበት በድዱ ለመናከስ የሚንገታገት ያረጀ አውሬ አስመስሏቸዋል። በምስራቁ በር አንዱ የጥፋት እጃቸው ተቆርጦባቸውም ለተስፋ መቁረጥ እጅ መስጠት አልፈለጉም። አብዲ ዒሌ የተሰኘ የጥፋት ፈረሳቸው አይናቸው እያየ ከፍትህ እጅ ላይ ወድቋል። አያስመልጡት ነገር አቅም የለም። የእነሱንም እድል እጣ ፈንታ እርግጠኛ አይደሉም። ለጊዜው እድል ሰጥቶ የተዋቸውን ህዝብ ትዕግስት ግን እያስጨረሱት ነው።

ብአዴን

ብአዴን መጨረሻውን እያሳመረ ይመስላል። ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህወሀት ልክ የተሰፋለትን ጥብቆ አድርጎ የኖረው ብአዴን ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ ከህወሀት ጋር የሚደረገው ፍቺ ቅርብ መሆኑን አመላካች ነው። ብአዴን ቆርጧል። የህወሀትን ቀሚስ አውልቋል። አርማና ስያሜ መቀየሩ ትርጉሙ ቀላል አይደለም። ህወሀትን ብአዴንን ጠፍጥፎ ሲሰሰራ የልደት ቀኑን ከህወሀት የአፈጣጠር ታሪክ ጋር እንዲመሳሰል ስለመደረጉ መገመት ይቻላል። 11 ቁጥር ላይ የቆረበው ህወሀት የብአዴንን የልደት ቀን ህዳር 11 ላይ ያደረገው ያለምክንያት አልነበረም። አርማውን ከህወህት አርማ የተቀዳ አድርጎታል። ብአዴን አርማውን ብቻ ሳይሆን በህወሀት የተተከለትን የልደት ቀኑንም መቀየር ይኖርበታል።

የብአዴን መግለጫ የህወህት የበላይነት ፍጻሜ ላይ ትልቅ ሚስማር የቸነከረ ነው። ኦህዴድ ታህሳስ ላይ የብሄር ጭቆና የለም የሚል አዲስ ትርክት ይዞ ሲመጣ ህወሀት የሚይዝ የሚጨብጠው አጥቶ ነበር። የመጽአት ቀኑን ያየበት አስደንጓጩ ምልክት የታህሳሱ የኦህዴድ መግለጫ ነው ማለት ይቻላል። በብሄር ጭቆና ላይ ታሪክ ፈጥሮ ስጋ ደምና አጥንት አልብሶ፡ እስትንፋስ ዘርቶበት ኢህ አዴግ በሚባል ፈረስ ኢትዮጵያን ለብዙ ዘመናት ሊጋልብ የተፈናጠጠው ህወሀት በኦህዴድ መግለጫ ህልሙ በአጭሩ ተቀጨ። ሲጠበቅ የነበረው የብአዴን አቋም ነበር። ሰሞኑን አፈረጠው። የብአዴን መግለጫ በህወሀት አንገት ላይ የጠለቀ ገመድ ማለት ነው። የሚቀረው ገመዱን ሸምቀቅ ማድረግና ህወሀት የረገጠውን መንጠልጠያ ማንሳት ነው። አዲዮስ ህወሀት!

መግለጫው በህወሀት ህልውና ላይ ሪፈረንደም ያደረገ ነው። የአማራ ክልል ወሰን ከእንደገና ይሰመር ዓይነት አቋም ከብ አዴን ሲሰማ መቼም ተአምር ነው። ይህ ማለት የወልቃይት፡ ራያና ሌሎች አከባቢዎችን በተመለከተ ብአዴን ጥያቄ ለማንሳት ወስኗል ማለት ነው። በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የወልቃይትን ጉዳይ ከእንግዲህ ችላ የምንለው አይደለም ሲሉ ጠርጥሬአቸዋለሁ። ይሀው የድርጅታቸው አቋም ሆኖ ይፋ ተደርጓል። የሱዳን ወታደሮች ከያዙት የኢትዮጵያ መሬት እንዲለቁ በብ አዴን መጠየቁ ለህወሀት ትልቅ መርዶ ነው። ህወሀት ለሱዳን የኢትዮጵያን መሬት የሰጠበት ድብቅ ስምምነት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ሱዳን ለህወሀት ምሽግ ናት። የክፉ ጊዜ መደበቂያ ናት። ለውለታዋ የጎንደር መሬት በስጦታ ተብርክቶላታል። ሱዳን ያን መሬት ከተነጠቀች ከህወሀት ጋር ያላትን ድብቅ ፍቅር መቀነሷ አይቀርም። ያ ደግሞ የትግራይ ህዝብ የተፋው ዕለት የሚደበቅበትን ዋሻ ያጣል ማለት ነው።

ብ አዴን በግል መብት ላይ የወሰደው አቋም በራሱ ለህወሀት አስደንጋጭ ነው። በቡድን መብት ስም ዘረኝነትን በማስፋፋት የበላይነቱን አስጠብቆ ለመኖር ፕሮግራም(ህገመንግስት) የቀረጸው ህወሀት ከብአዴን በቃህ ተብሏል። የቡድን መብት እንዳለ ሆኖ የግለሰብ መብት ላይ ማተኮር ለዴሞክራሲ ወሳኝ ነው የሚል አቋም ላይ የደረሰው ብአዴን በብሄራቸው እየተደበቁ ቁማር የሚጫወቱ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችንም ቅስማቸውን የሰበረ አቋም ላይ መድረሱ አስደናቂ ነው። ህወሀት በቁሙ ተዝካሩን በላና አረፈው። በዚህ አልቆመም። የህወሀትን ጥቅም በአማራው ህዝብ ኪሳራ ለማስጠበቅ በብ አዴን ውስጥ የተሰገሰጉ አፍቃሪ ህወሀት የሆኑ ቀንደኛ አመራሮችን ጠራርጎ ማባረር የጀመረው ብአዴን ለህወሀት አንድ መልዕክት እንዲደርሰው የፈለገ ይመስላል። ”በቃ”

በረከተ መርገምት

አቶ በረከት ስምዖን አየሩን ተቆጣጥሮታል። የመንደር የኮሚኒቴ ሬዲዮ ሳይቀር ደጅ እየጠና እንዳለም ሰምቼአለሁ። ብዙ ሰዎች በረከት ሰሞኑን የሰጠው ቃለመጥይቅና አብሮት ከተባረረው ታደሰ ጥንቅሹ ጋር የጻፉት ደብዳቤ ላይ በማተኮር የበረከት ቅጥፈቶች ላይ ጊዜ ሰጥቶ ሲወያዩ ታዝቤአለሁ። ለእኔ በረከት እንዲህ ተዝረክርኮ፡ በስጋት ተንጦ፡ ቅስሙ ተሰብሮ፡ የሚደገፍበት አጥቶ፡ ሲንከራርተት እንደማየት የሚያስደስት ነገር አላየሁም። ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፡ በምዕራብና ምስራቁ እየተወነጨፈ ያሻውን ሲያደርግ፡ ሲያስገድልና ሲያሳስር የከረመ፡ ምድር አልበቃ ብላው በሰማይ መንሳፈፍ እስኪቀረው የደረሰ፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ረጅሙን ርቀት የተጓዘ ሰው ዘመን ተገልብጦ፡ በሰፈረው ቁና የሚሰፈርበት ጊዜ መጥቶ ”እንዳልንቀሳቀስ ገደብ ተጥሎብኛል” ዓይነት እዬዬውን ሲያስነካው እንደመስማት ያለ ምን ድል ይገኝ ይሆን? እንደዚያ በትዕቢት ተወጥሮ የሚታወቀው በረከት ኩምሽሽ ብሎ፡ በፍርሃት ርዶ የምቆም የምቀመጥበት አጣሁ ሲል መስማት ለእኔም ሆነ የፍትህን መረጋገጥ ሲናፍቁ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ነው።

በረከትን ሳስበው ሁል ጌዜ ከአእምሮዬ ጓዳ ብቅ የሚለው አንድ ወቅት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ስለበረከት የተናገሩት ነው። ”መለስ ክፉ ነው። መለስን የበለጠ ክፉ ያደረገው ደግሞ በረከት ስምዖን ነው” እንግዲህ የክፋት አለቃ፡ የጭካኔ ደቀመዝሙር፡ የተንኮል ሀዋሪያ፡ የቅጥፈት አምባሳደር የሆነው በረከት ስምዖን ጊዜ ጥሎት፡ ዘመኑ አብቅቶ ዋጋውን ሊያገኝ ነው። በየሚዲያው ቀርቦ ”ቅዱስ ነበርኩ፡ ክንፍ የሌለው መልዕክ ከእኔ በላይ የት ይገኛል?” ዓይነት የሌባ አይነደረቅ ዲስኩሩን እየለቀቀው ነው። በረከት ብአዴኖች ላይ የጀመረው ውግዘት አፈጣጠሩንና ስነልቦናውን እንድንመራመርበት የቤት ስራ የሚሰጠን ሆኗል። ምድር የተጠየፈችው፡ በእኩይ ምግባሩ ሀገርና ህዝብ በአንድ ሰልፍ ፊት የነሳው ሰው፡ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል መፈክር ይዞ መልሶ ለእኛው ልንገራችሁ ማለት የጤና አይመስለኝም። የሚቀርቡት ወዳጆች ካሉት በጊዜ ዶክተሩን እንዲጎበኝ ቢመክሩት ጥሩ ነው። ጤናም እንዳልሆነ በብዙ ይነገርለታል።

በዘመኑ በሀሳብ የተለዩትን ላይ በጭካኔ አስሯል። የፖለቲካ ተቀናቃኝ ያላቸውን የሀሰት ዶሴ እየከፈተ ከእድሜአቸው ላይ ተቀንሶ በማጎሪያ እስር ቤት እንዲሰነብቱ አድርጓል። መለስ ሲሞት ለቅሶን በሀገር ደረጃ አደራጅቶ፡ ማቅ አስለብሶ፡ ህዝቡን በማህበር እንዲያዝን በማድረግ ታላቅ ግፍ የፈጸመ ወንጀለኛ ነው። በረከት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ስም ያለው ነው። ዛሬ ”በነጻነት፡ በፖሊሲ” እንከራከር ሲል አለማፈሩ ይገርማል። ዛሬ እሱ የሚጠይቀውን መብት ትላንት የጠየቁትን ሲያዋርድ፡ የቴሌቪዥን ድራማ እያሰራ ስም ሲያጨቀይና ገፍቶም ሲያሳስርና ሲያስገድል ዓለም የሚያውቀው ሰው ዛሬ ተነስቶ ”በፖሊሲ እንከራከር” ብሎ አይኑን በጨው አጥቦ መጥቷል። እንግዲህ ‘ፍትህ’ ለዚህ ሰውዬም ያስፈልጋል።

በረከትን ‘ኢትዮጵያዊው’ ጎብልስ በሚል የሚጠቅሱትም አሉ። የናዚው የፕሮፖጋንዳ ማሽን ጆሴፍ ጎብልስ ”ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” የሚለውን አስቀያሚ ትርክት ለዓለም ያስተዋወቀ፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዚሁ ትርክቱ የናዚን ወታደሮችና የጀርመንን ህዝብ ለጦርነት የማገደ እንደነበረ ይነገርለታል። በረከት ስምዖን የዘመኑ ጎብልስ ሆኖ ኢትዮጵያውያን ላይ ተሰይሟል። ሀገሪቱን የውሸት ፋብሪካ አድርጓት አንድ ትውልድ በውሸት ተወልዶ እንዲያድግ ፈርዶበታል። በእርግጥ በናዚው ጎብልስና በህወሀቱ ጎብልስ መሀል ልዩነት አለ። ጎብልስ የቆመለት የናዚ ስርዓት ሲገነደስና እንደአምላክ የሚያየው አዶልፍ ሂትለር ራሱን ሲያጠፋ ጎብልስም ስድስት ልጆቹን መርዝ አብልቶ እሱንና ሚስቱንም በሽጉጥ ገድሎ ይህቺን ምድር ተሰናብቷል። በረከት ስምዖን ግን ፈሪ ነው። አምላኩ መለስ ዜናዊ ሞቶም እሱ እስከአሁን አለ። ወንድሙን ገድሎበት እንኳን በታማኝነት የገበረለትና የተገዛለት የህወሀት ስርዓት በቁሙ ሲገነደስ እያየ በረከት ግን መኖር ይፈልጋል። ፈሪ። መርገምት።

የአንድ ጀግና ወታደር ታሪክ (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)

የአንድ ጀግና ወታደር ታሪክ

የዛሬ 5 አመት ገደማ ነው፤ አንድ መረጃ ያቀብለን የነበረ መኮንን ደጋግሞ ስልክ ይደውልልኛል፤ ስራ እንደጨረስኩ ደወልኩለት። ሰላም ነው አንበሳው። “ምን ሰላም አለ፤ ስልኩን አላነሳ ስትል ሳልሰናበተው ልቀር ነው እያልኩ ቆጭቶኝ ነበር፣ ስልክህ ሲጠራ እንዴት እንደተደስትኩ አትጠይቀኝ” አለኝ። ይቅርታ ስራ በዝቶብኝ ነው፣ ልትዛወር ነው እንዴ አልኩት። “ እረዳሃለሁ ፋሲሎ፣ ለማንኛውም ጠፍቼ እየሄድኩ ነው፣ የት እንደምሄድ ግን አላውቅም፤ ዛሬ ያየሁትን ነገር ህሊናዬ ሊሸከመው አልቻለም” ። ቆይ ምን ተፈጠረ? “ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ፣ እናቶችንና ህጻናትን በጠራራ ጸሃይ ጨረሷቸው፣ እናቶችን ሳይ እናቴ ትዝ አለችኝ”፣ ድምጹ ተቆራረጠ። ወታደር የሚያለቅስ አይመስለኝም ነበር፤ አይዞህ አይዞህ እያልኩ አጽናናሁት። ምንድነው የሆነው እስኪ ተረጋግተህ ንገረኝ አልኩት። “ዛሬ ጠዋት ኦብነግ አንድ መንደር ውስጥ ገብቷል ተብለን ግዳጅ ወጥተን ነበር፤ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት እኛን እየመሩ ወሰዱንና ቦታው ስንደርስ ኦብነጎች ማምለጣቸውን ሰማን፤ ከዚያ በሁዋላ ህዝቡን ማሸበር ተጀመረ፣ እናቶች አትግደሉን እያሉ ተገደሉ፣ ህጻናት መሸሸጊያ ፍለጋ ሲራወጡ ፊት የተገኙት ሁሉ ተገደሉ፣ ወጣት የሚባል የለም፣ አሮጊቶችና ሴቶች ናቸው ታጨዱ፣ ምን ልበልህ፣ መፈጠርክን ትጠላለህ፤ ያየሁትን ለመግለጽ አልችልም፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከዚህ ሰራዊት ጋር መቀጠል አልፈልግም ፣ እነሱ ወደ ፊት ሲሄዱ እኔ ጠፍቼ መንገድ ጀምሬያለሁ።” መኮንኑ በስሜት ውስጥ ሆኖ ሲገልጸው የነበረው እና እኔ ከአመታት በሁዋላ ስጽፈው ያለውን ልዩነት እያስተዋልኩ ተናደድኩ። እንደ ዛሬ የደራሲነት ተሰጥዖ እንዲኖረኝ ተመኝቼ አላውቅም።

ስሜትን ዋጥ አደርኩና፣ ለመሆኑ የት ነው የምትሄደው አልኩት። “አላውቅም ኦጋዴንን ታውቀዋለህ፣ ምደረበዳ ነው፤ ከተሳካላኝ ጅቡቲ ወይም ሶማሊያ ልገባ እችላለሁ፤ ምናልባትም በኦብነግ ወይም አልሸባብ እጅ ልወድቅ እችላለሁ፣ የእኛ መከላከያዎች ካሉበት በተቀራኒ አቅጣጫ ነው የምጓዘው። እነሱ እንዲይዙኝ አልፈግልም፤ ከተያዝኩም ምን እንደሚያደርጉኝ አውቃለሁ፣ በእነዚህ ዘረኞች እጅ ላይ ከምወድቅ ኦብነግ ወይም አልሸባብ ቢገድለኝ እመርጣለሁ፤ አሁንማ አያተርፉኝም፤ የሚይዙኝ ከሆነ ግን እራሴን አጠፋለሁ።” ወንድሜ ስማኝ፣ “ አሁን ወደ ቦታህ ተመለስ፣ አሞኝ ነው ወደ ሁዋላ የቀረሁት በላቸው፣ ሌላ ጊዜ አዘናግተህ ትጠፋለህ፣ እኔ ራሴ መንገድህን አመቻችልሃለሁ፣ በፍጹም ወደማታውቀው ቦታ አትሂድ…” እያልኩ ላሳምነው ሞከርኩ። “አላደርገውም፣ የእኔ ነፍስ ካለቁት እናቶችና ህጻናት ነፍስ አይበልጥም። አሁን ባትሪዬን አትጨርሰው፤ የሆነ ቦታ ላይ በሰላም ከደረስኩ ቁጥርህን በቃሌ ስለያዝኩት እደውልልሃለሁ፤ መንገድ ላይ ከቀረሁም ቻው፤ በርታ፣ በጣም አከብርሃለሁ፤ ኦጋዴን ውስጥ የተፈጸመውን ታሪክ በዝርዝር የምናገርበት እድሜ እንዲሰጠኝ ጸልይለኝ ” ብሎኝ፣ እኔም እንደምንም ስሜቴን ዋጥ አድርጌ መልካሙን ሁሉ ተመኝቼ ስልኩን ዘጋሁት። ዛሬም ድረስ ያ ጀግና ወታደር ይደውል ይሆን እያልኩ ስልኩን በጉጉት እጠብቃለሁ። ከተለያየን ከ3 ዓመታት በሁዋላ ቁጥሬን የቀየርኩ በመሆኔ አዲሱ ቁጥሬ ላይኖረው ቢችልም፤ በ3 ዓመታት ውስጥ ለእሱ በሰጠሁት ቁጥር ደውሎልኝ አያውቅም።

ወዳጄ፣ በአንድ ወቅት በብሄራቸው የሚያስቡ አዛዦች የሞሉበት ሰራዊት ተቀይሮ ህዝባዊነትን ሲላበስ ቢያይ ኖሮ፣ ምንኛ ደስ ባለኝ፤ እሱና መሰሎቹ ይህ ቀን እንዲመጣ ስንትና ስንት መስዋትነት መክፈላቸውን አፍ ቢኖረው ኖሮ የውቅሮ እስር ቤት በዝርዝር ያጫውተን ነበር።

አገርቤት ጠቅልለው ስለገቡ አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅቶችና አመራሮች እየሰማሁት ያለሁት መረጃ ደስ አይልም። በጣም ደስ አይልም።(Ermias Legesse Wakjira ;)

Ermias Legesse Wakjira ; አገርቤት ጠቅልለው ስለገቡ አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅቶችና አመራሮች እየሰማሁት ያለሁት መረጃ ደስ አይልም። በጣም ደስ አይልም።

#ከገቡ ቀን ጀምሮ ሸራተን አዲስ ውሎና አዳራቸውን ያደረጉ እንዳሉ ይሰማል። የውሎና አዳሩን የአንዲት ቀን ሂሳብ ይሰራ ቢባል በትንሹ 5ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይሆናል። በአንድ ወር ውስጥ ለአንድ አመራር ብቻ ወደ 150ሺህ የኢትዮጵያ ብር ነው። እናም ይሄን ከፍተኛ ገንዘብ እየሸፈነ ያለው ማነው?

#አንዳንዶቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አዘውትረው የሚገናኙት እና የሚያመሹት ከህውሓት ከፍተኛ አማላይ (ሎቢስት) ከሆነው አቶ ቆስጠንጢኖስ በርሄ ጋር ነው። እንዴት ይሄ ሊሆን ቻለ? ህውሓት ለቆስጠንጢኖስ የሰጠው ተልእኮ ምንድነው? የሸራተን አስተናጋጆች እስኪታዘቧችሁ ድረስ ከቆስጢ ጋር የኮኛክ ብርጭቆ ማጋጨት ምን የሚሉት ነው?

#አንዳንዶቻችሁ እንደ ድርጅትም እንደ አመራርም አገር ቤት ከገባችሁ ወራት ተቆጥረዋል። የምንመለከታችሁ ኦህዴድ/ኢህአዴግ የራሱን በአላት እና ስብሰባ ሲጠራ በፊት መስመር ተሰልፋችሁ ከማየት ውጪ የተለየ ነገር መመልከት አልቻልንም። የኢህአዴግ ሊቀመንበሩ ዶክተር አቢይ የሶስት ወራት ፍጥነቱ “ማይክል ቦልት!” እያስባለው ነው። እናንተ ምን እያደረጋችሁ ነው?

በአንድ ወቅት የፌዴራል የስራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ የለውጥ አመራር አሰልጣኝ የነበረ አቶ አይችሎም የሚባል ሰው ነበር። ታዲያ አቶ አይችሎም በአንድ ቀን ውስጥ ሰላሳ ጊዜ የሚገልጣት አባባል ነበረችው። “የፈረንጅ ዘፋኝ?

#እናም እናንተ አገር ቤት የገባችሁ የፓለቲካ ድርጅቶችና አመራሮች የኢትዮጵያን ብርቅዬ አፈር ከረገጣችሁ በኃላ የሰራችሁትን ፓለቲካዊና ድርጅታዊ ስራ ንገሩን። በአደባባይ፣ ስቴዲዮም፣ አዳራሽ ምን ያህል ጊዜና ህዝብ ሰበሰባችሁ? መቼም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚባል ሰበብ አሁን እንደሌለ ለማንም ግልጥ ነው። …”ሕዝባችን!” በማለት የተናገራችሁት ወርዳችሁ አናግራችኃል? የት የት አካባቢ?… በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የሽግግር ሂደት ላይ ድርጅታዊ ተሳትፎአችሁ ምን ይመስላል?…

ለማንኛውም እንደ ” ማይክል ቦልት” መፍጠን፣ አሊያም እንደ “አሞራዋ” መብረር ቢያቅታችሁ እንኳን እንደ “ሰው!” ሁኑ።

ዛሬም ታሪካዊ ቀን (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ዛሬም ታሪካዊ ቀን

ፕ/ሮ መስፍን ወ/ማርያም በአንድ ወቅት “ከመለስ የኢሳያስ ኢትዮጵያዊነት ይበልጥብኛል” ማለታቸውን በተለያዩ ፅሁፎች ውስጥ አንብቤአለሁ:: በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ከአስመራ ለጀርመን ሬዲዮ ሲዘግብ የምናውቀው ጎይቶም ቢሆን ጀርመን ላይ በተገናኘንበት አጋጣሚ ያጫወተኝን አስታውሳለሁ:: “ኤርትራን የሚመሯት የመሀል ሀገር ሰዎች ናቸው:: ” የመሀል ሀገር ሲባል አዲስ አበባ ለማለት ነው::

እውነት ለመናገር አቶ ኢሳያስ ስለኢትዮጵያ ሲናገሩ የሰማ ሰው አንድ ጥያቄ በውስጡ ይመጣል- “እኚህ ሰው ስለምን የኢትዮጵያ ክፉ ተደርገው ይወሰዳሉ? እሳቸውስ በአደባባይ ይሄን ለምን አይገልፁትም? ስለኢትዮጵያ መልካም የሚያስቡት ለፖለቲካ ግብ ብቻ እንዳይሆን?” ብሎ ቢጠይቅ ተገቢነት አለው:: በኤርትራ በነበረን ቆይታ በተለያዩ ሁኔታዎች ከአቶ ኢሳያስ አፈውርቂ ጋር የመገናኘቱ አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር:: አቶ ኢሳያስ በዚህ ደረጃ ለኢትዮጵያ መልካም ስሜት ካላቸው ስማቸውን በክፉ እንዲነሳ ከሚያደርጏቸው የታሪክ ወለምታዎች ጋር መጠቀሱ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል::

ከመለስ ዜናዊ አንደበት በስህተት እንኳን ወጥቶ የማያውቅን ስለኢትዮጵያ መልካም ስሜት ከአቶ ኢሳያስ መስማት ሊያስደንቅ ይችላል::የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ጠላት ተደርገው በአእምሮአችን ውስጥ ከተቀረፁት ሰው ይወጣል ተብሎ የማይጠበቅ ነገር ሲሰማ በእርግጥም ያስገርማል:: ጥያቄም ይጭራል:: እንዴት ሆኖ? እንዴት እንመን? የማስታውሰው ከእኛ ጋር የሄደ የልዑካን ቡድን አንድ አባል ከአቶ ኢሳያስ የሚሰማውን ለማመን ተቸግሮ ” እንዲህ ከሆነ ለምን እርስዎ የኢትዮጵያ መሪ አልሆኑም ነበር?” የሚል ጥያቄ አንስቶባቸው ነበር:: ፈገግታቸውን ብልጭ በማድረግ ብቻ አለፉት::

በእርግጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ በተዘፈቅችባቸው የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ጋር በፊት ለፊት ከተሰለፉ ሰዎች አንዱ ናቸው:: ኢትዮጵያና ኤርትራ በተለያዩበት ጊዜ ፊት መሪ እሳቸው ነበሩ:: ኢትዮጵያውያን መቼም ከማይረሱት የመገፋትና የመከፋት ክስተቶች ጋር አቶ ኢሳያስ ይጠቀሳሉ:: ማስረጃ ካልተገኘለት “የ100ዓመት የቤት ስራ” ጀምሮ የሚጠቀሱ በርካታ ፀረ ኢትዮጵያ ንግግሮችና ድርጊቶች ጋር የአቶ ኢሳያስ ስም ጎልቶ ይነሳል:: እሳቸውን ከማይክ ውጭ ላናገረ ሰው ደግሞ የሚሰማው ነገር ፍፁም ተቃራኒውን ነው:: የቱን እንመን?

ኤርትራ በነበረን ቆይታ ከሰማኃቸውና ካየኃቸው አጋጣሚዎች የተወሰኑትን ልጥቀስ:: ከአቶ ኢሳያስ ጋር ከተገናኘንባቸው ሶስት አጋጣሚዎች በአንዱ ነው:: ስለአንድ አጋጣሚ እየነገሩን ነው:: ህወሀት አዲስ አበባን: ሻዕቢያም አስመራን በተቆጣጠሩ በኃላ ነው:: የየመን: ሱዳን: ኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች በካርቱም ስብሰባ ያደርጋሉ:: ሁሉም መሪዎች የመከላከያ አዛዦቻቸውን ይዘው የተለየ ምክክር ያደረጉበትን አንድ አጋጣሚ አቶ ኢሳያስ እንዲህ ያስታውሳሉ:

“ድንገት የየመኑ የመከላከያ ሚኒስትር ይነሳና ‘በምስራቅ አፍሪካ እንቅፋትና አደጋ የሆነችው ኢትዮጵያ ናት:: ኢትዮጵያን ካላጠፋን ሰላም አይኖርም:: ኢትዮጵያ መቃጠል አለባት’ አለ:: በወቅቱ ለዚህ አደገኛ ንግግር መለስ ዜናዊ መልስ አልሰጠም:: መከላከያውም ዝም አለ:: እኔ ተነሳሁና ‘ይህ ትክክል አይደለም:: ኢትዮጵያ እንደውም ተገቢውን ክብርና ቦታ አለማግኘቷ ቀጠናውን ወደቀውስ ሊወስደው ይችላል::’ ብዬ ተከራከርኩ”

አቶ ኢሳያስ ይህን ተናግረዋል:: ውሸት ከሆነ የማስተባበሉ ሃላፊነት መቀሌ የመሸገው የህወሀት ቡድን ነው:: በዚያ ኢትዮጵያ እንድትቃጠል ሀሳብ በቀረበበት የካርቱሙ ስብሰባ ላይ ከአቶ መለስ ጋር ነበሩ የተባሉት ስዬ አብረሃ ሊሆኑ ይችላል:: በወቅቱ የመከላከያው ሃላፊ ስዬ ይመስሉኛል:: እናም ይህ ሆኖ ከሆነ አቶ ስዬ በህይወት አሉና መልስ ይሰጡ ዘንድ ይጠበቃሉ:: የኢትዮጵያን ተዝካር ለማውጣት ሀሳብ የቀረበበትን ስብሰባ የኢትዮጵያ መሪ ነን ያሉ ሰዎች በዝምታ ማለፋቸው በኢትዮጵያ መጥፋት መስማማታቸውን የሚያረጋግጥ ነው:: የሆነው ትክክለኛ ክስተት ከሆነ ግን አቶ ኢሳያስ ባለውለታችን ናቸው ማለት ነው::

ሁለተኛው የህገመንግስቱ ጉዳይ ነው:: አቶ መለስ ኢትዮጵያ ላይ ማንኛውንም ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት ከአቶ ኢሳያስ ጋር ይማከራሉ:: መለስ ለኢሳያስ ያለው አመለካከት ወደ ማምለክ የተጠጋ ነበር ይባላል:: እናም የህወሀት ፕሮግራም የሆነውን ህገመንግስት እነዶ/ር ነጋሶ በህዝብ ስም እንዲፀድቅ ከማስደረጋቸው በፊት አቶ ኢሳያስ አይተውታል:: እንዲህ ይላሉ አቶ ኢሳያስ

“መለስ ህገመንግስቱን ይዞ አስመራ መጣ:: ሳየው ኢትዮጵያን በጎሳና ብሄር የሚሸነሽን አደገኛ የሆነ ህገመንግስት ነው:: መዘዙ ለእኛም የሚተርፍ በመሆኑ አጥብቄ ተቃወምኩት:: መለስ ግን ‘ ድርጅቴ ህወሀት በማዕከላዊ መንግስት ውስጥ ስልጣን ይዞ ለመቆየት ከዚህ ውጭ አማራጭ የለንም’ አለኝ::”

ይሄው ህገመንግስቱ እውቅና የሰጠው የብሄር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለአደጋ አጋልጧል:: እነዶ/ር አብይ በህገመንግስቱ ምክንያት የሚያሰቃየንን በሽታ ለማከም እየለፉ ቢሆንም አደጋው ግን አሁንም አለ:: ሰሞኑን ከሞያሌ መስመር የምንሰማው አሰቃቂ ነገር የህገመንግስቱ ውጤት ነው:: ገና በማለዳ የጅምላ ቀብር የሚፈፀምበት አንድ ቪዲዮ አይቼ ተረብሼአለሁ::

ኤርትራ ከኢትዮጵያ የመለያየቷንም የታሪክ ክስተት በተመለከተ ከተነገሩን የሚቃረኑ ነገሮችን ነው በኤርትራ ቆይታችን የሰማነውና ያየነው:: በአንዳንድ የሻዕቢያ ዶክመንቶችና የስብሰባ ቃለጉባዔዎች እንደሰፈረው መገንጠል ሶስተኛ እንጂ ብቸኛ አማራጭ አልነበረም:: አቶ ኢሳያስ ሲያጫውቱንም ከመለያየት በፊት ለ10ዓመታት አብሮ በመቆየት ሁኔታዎችን መፈተሽ የሚቻልበት አማራጭ ሀሳብ በሻዕቢያ በኩል ቀርቦ ነበር:: እነመለስ ፍቃደኛ አልነበሩም:: ከሌሎች የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናትም ተመሳሳይ ነገር ሰምቼአለሁ:: እነመለስ አጣድፈውና አክለፍልፈው ህዝበ ውሳኔ አስደርገዋል:: ይሄም በታሪክ ተመዝግቧል::

የኤርትራን የመገንጠል አጀንዳ ከሻዕቢያ ይልቅ ይገፋበትና ያቀነቅን የነበረው ህወሀት ስለመሆኑ ይነገራል:: አቶ ስብሃት ነጋም ያለሀፍረት ይሄንኑ መስክረዋል:: ከዓመታት በፊት ለድምፀ ወያኔ በሰጡት ቃለመጠይቅ “ሻዕቢያ በተደጋጋሚ የኤርትራን ነፃነት አደጋ ላይ ሲጥል እየደረስን ስናድን የነበርነው እኛ ነን::” ያሉበት ቃለመጠይቅ አርካይቭ ውስጥ አይጠፋምና ፈልጎ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል::

የዚህ ፅሁፍ ዓላማ አቶ ኢሳያስን ቅዱስ አድርጎ ለማሳየት አይደለም:: ይልቅስ የሰማናቸውን ይዘን አሁን በኤርትራ በኩል የሚቀርቡትን ትርክቶች ካገኘን ሚዛናዊ የሆነ የታሪክ ፍርድ ለመስጠት እንድንችል ለመቆስቆስ ያህል ነው:: ከአንድ ወገን የሰማነውን ሰምተናል:: ህወሀት የሚዲያ የበላይነቱን ተቆጣጥሮ: ከምዕራብያውያን ጋር በመሆን ስለአቶ ኢሳያስና በአጠቃላይም ስለኤርትራ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ስራ ሰርቷል:: በዚህም ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል:: ከኤርትራ ባለስልጣናት ሁኔታ እንደተረዳነው ራስን መሸጥ ላይ ደካማ ናቸው:: በየጊዜው በህወሀት በኩል የሚቀርብባቸውን ክስ መልስ መስጠት አይፈልጉም:: ዝምታቸው ጎድቷቸዋል:: ለህወሀት የፕሮፖጋንዳ የበላይነት እድሉን ሰጥተውት ቆይተዋል::

አሁን ወደ መድረኩ እየመጡ ነው:: እኛ ዘንድ ያለው እውነት ሌላ ነው እያሉ ናቸው:: ኢሳትን ጨምሮ በኤርትራ የገቡ የኢትዮጵያ ሃይሎች ስለኤርትራ ምስክርነት ሲሰጡ ተወግዘዋል:: አሁን ራሳቸው ይናገራሉ:: እውነት አርነት ያወጣል:: በኤርትራውያን የሚነገረውን ሰምቶ ማስረጃም ከቀረበለት አይቶ ፍርድ የሚሰጠው ህዝብ ነውና ያን በትዕግስት መጠበቅ ነው:: አሁን እየታየ ያለው የሁለቱ ሀገራት አስደናቂ ግንኙነት አንዱ ማስረጃ ነው:: ማን በጥባጭ: የትኛው ወገን የሰላም ጠንቅ ሆኖ እንደቆየ ያጋለጠ ግንኙነት ነውና::

የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ በአዲስ አበባና በሀዋሳ ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ያደረገው አቀባበልና ያሳየው ክብር በራሱ የሚነግረን ትልቅ መልዕክት አለ:: ከአራት ዓመት በፊት አቶ ኢሳያስ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለመጠየቅ ኢትዮጵያና ኤርትራ ብሎ መጥራት አልፈልግም ብለው ነበር:: ዛሬ ደገሙት:: “ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝብ አትበሉ ፣አንድ ህዝብ ነው በሉ ፣ አንድ ህዝብ ነን”

አንድ የኤርትራ ጉምቱ ባለስልጣን ያሉኝ መቼም አይረሳኝም:: ” ምን እንደናፈቀኝ ታውቃለህ?”
“ምንድን ነው እሱ?”
“ካሳንቺስ ሄዶ ማኪያቶ መጠጣት”
የካሳንቺስ ልጅ ነበሩ – በፊት:: የእኔ አባት ይሄው እንግዲህ ካሳንቺስ ይምጡና ማኪያቶውን ይላፉ::

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ይባርክ!!
ኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን

ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ታሪኳ እንመልሳት ሲባል ወደ ስኬት ታሪኳ እንጅ ወደ ውድቀት ታሪኳ እንመልሳት ማለት አይደለም። (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም)

ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ታሪኳ እንመልሳት ሲባል ወደ ስኬት ታሪኳ እንጅ ወደ ውድቀት ታሪኳ እንመልሳት ማለት አይደለም። ማንኛውም አገር የስኬትና የውድቀት ታሪክ እንዳለው ሁሉ ኢትዮጵያም የስኬትና የውደቀት ታሪክ አላት። የፋርሱ የጂኦግራፊ ሊቅ ማኒ በ5ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩት አራት ታላላቅ ሃያላን መንግስታት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች መስክሯል። ኢትዮጵያ ከደቡብ አረቢያ እስከ ደቡብ ግብጽ የሚደርስ ግዛት የነበራት፤ የአክሱም ሃውልትን፣ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የፋሲል ግንብን፣ የገዳን የእኩልነት ስርዓት ( ከግሪኮች ባልነተናነሰ) ያቆመች ፤ ጤፍንና ቡናን አላምዳ ለአለም ያበረከተች አገር ናት። ነብዩ ሙሃመድ “ ኢትዮጵያ የፍትህ አገር ናት” ብለው እውቅና የሰጡዋት የፍትህ ታሪክ ያላት አገር ናት። ኢትዮጵያ አውሮፓውያናንን ሲያማልል የነበረው “የፕሬስተር ጆን ኦፍ ዘ ኤንድስ” ታሪክ ባለቤት ፤ ነጭን ድል በማድረግ የአፍሪካ የነጻነትና የአልገዛም ባይነት ተምሳሌት ናት። ለጥቁር ህዝብ የነጻነት ትግል ፈር የቀደደች፣ እነ ማርክስ ጋርቬይ “ ኢትዮጵያ” ብለው የትግል መዝሙር ያዘመሩላት ብቸኛዋ የጥቁሮች አገር ኢትዮጵያ ናት።

ወደ ገናናው ታሪካችን እንመለስ ሲባል ወደ ዘመነ መሳፍንት የውድቀት ታሪካችን እንመለስ ማለት አይደለም። ታሪክን አለማወቅ ላያስነውር ይችላል፤ ታሪክን ሳያውቁ ስለታሪክ መናገር ግን ከነውርም በላይ ነውር ነው። ኢትዮጵያ ገናና ታሪክ እንደሌላትና ታሪኳ ሁሉ የውደቅት ታሪክ እንደሆነ በድፍረት የሚጽፉ የዚህ ዘመን ጉዶች፣ ለሃፍረታቸው መሸፈኛ የሚሆን ትንሽ ቅጠል ማጣታቸው ያሳዝናል። አባቱን የማያውቅ ሰው ስለአባቱ በድፍረት ሊናገር እንደማይችለው ሁሉ፣ ታሪክን የማያውቅ ሰውም ስለታሪክ በድፍረት ሊናገር አይችልም። ታሪክ አልባ ትውልድ ወደፊት አይራመድም፤ በውሃ ላይ እንደሚበቅል ተክል ስር አልባ ሆኖ እድሜ ልኩን እንደተንሳፈፈ ይኖራል እንጅ። ሌሎች አገሮች ዱቄት እያቦኩ አዲስ ታሪክ ለመጋገር በሚኳትኑበት በዚህ ዘመን፣ የተጋገረ ታሪክ ባለቤት የሆኑት የእኛ ዘመን ልጆች፣ እንጀራውን መብላት ሲሳናቸው ከማየት በላይ የሚያሳፍርም የሚያሳዝንም ሌላ ነገር የለም።

ሁላችንም የሚያኮራ ታሪክ አለን። አይናችን ገልጠን ማየት ከቻልን በየቤቱና በየሰፈሩ ተጽፎ እናገኘዋለን። አይናችንን ገልጠን መፈለግ ስላልቻልን ወይም ስለሰነፍን ብቻ ፣ “የሚያኮራ ታሪክ የለኝም” እያልን በማላዘን፣ ስንፍናችንን “ በታሪክ አልቦነት ለመሸፈን መሞከር፣ አያቶቻችን አርፈው እንዳይተኙ ማድረግ ማድረግ ብቻ ሳይሆን“ እኛ አቅቶናልና ከመቃብር ወጥታችሁ እንደገና ታሪክ ስሩልን” ብሎ እንደመጠየቅ የሚቆጠር አሳፋሪ ተግባር ነው። ችግራችን ከስንፍናና ከአላዋቂነት ጋር እንጅ ከታሪክ ልቦነት ጋር የሚዛመድ አይደለም። አብይ አህመድ ወደ ገናናው ታሪካችን እንመለስ ሲል “ ገናና ታሪክ የለንም ” ብለህ የምትከራከር ከሆነ፣ ያወቅህ መስሎህ የማታውቅ፣ የጠለቅህ መስሎህ የምትንሳፈፍ፣ ወደ ሁዋላ አይተህ ወደ ፊት መንዳት የማትችል፣ ማንነትክን መቀበል የከበደህና ከማንነት ቀውስ ያልወጣህ ሰው መሆንክን ማወቅ ይኖርብሃል። የማንነት ቀውስ መነሻው ታሪክ አልቦነት ነው። ከዚህ ቀውስ የምትድነውም ታሪክን በሃቅ መመርመር ስትችል ነው። ታሪክን ያማታውቅ ከሆነ፣ ከቻልክ በፍጥነት መርምረህ ከገናና ታሪካችን ጋር የሚደመር ታሪክ ለመስራት ሞክር ፣ ካልቻልክ ደግሞ “አመልክን በጉያህ” እንዲሉ ዝም በል።

እኛ ታሪካችንን የተቀበልን ኢትዮጵያውያን፣ ከውድቀት ታሪካችን እየተማርን ገናና ታሪካችን ለመመለስ እንታገላለን እንጅ ከታሪካችን በማፈግፈግ ማንነታችንን አንክድም አሳፋሪ ታሪክም አንጽፍም።

“ተቅማጥ ስለያዘኝ ORS ላኪልኝ። ብታገኝ 3 ብር ላኪልኝ።” ከድብቅ እስር ቤት የተላከ መልዕክት ( በጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው)

“ተቅማጥ ስለያዘኝ ORS ላኪልኝ። ብታገኝ 3 ብር ላኪልኝ።” ከድብቅ እስር ቤት የተላከ መልዕክት

ልብ የሚሰብር!

ከስር የሚመለከተው ትግራይ ውስጥ የሚገኝ ድብቅ እስር ቤት ታስረዋል ይገኛሉ የተባሉት ሊቅ መምህር እንደስራቸው አግማሴ ከ24 አመት በፊት ጎንደር የሚገኝ ድብቅ እስር ቤት ውስጥ ታስረው በነበሩበት ወቅት በሚስጥር ከእስር ቤት ለቤተሰባቸው የላኩት ደብዳቤ ነው።

የደብዳቤውን ይዘት እንደሚከተለው ሰፍሯል!

……………………………………………………

ለወይዘሮ ንግስት ተፈራ፣ እንደምን አድረሽ ውለሻል? በእውነት ሕይወትሽ ካለ ስለማንኛውም ሁኔታ በእጅሽ ፅፈሽ ላኪልኝ። ለመምሩ ላኪባቸው። ያልኩሽን አትርሽ። ቀበሌ 04 ከካሴ ዋለልኝ ቤት። ካለሽ ዋዛ አታድርጊው። ትርሲትን ላኪያት። አምኃ ነኝ(የክርስትና ስማቸው?) (የመስቀል ምልክት አለበት)። ዋናው ስማቸው Alemu Tasew በጣም ፀልይልኝ። እግዚያብሔር ይሰማሻል። በየሰዓቱ አባታችን ሆይ እያልሽ! ትንሽ ከብዶኛል ዘንድሮ!

የቁም ሳጥኑ የተሰበረችው አይነት ቁልፍ (የተሰረዘ) ንሽ ላኪልኝ። ከተቻለ።

(ህፃኑን) ልጁን ቅባቅዱስ አቅምሰሽው ከሆነ እያዘገምሽ 7 ቀን ጧት ጧት ከምታፈቅሪው ቤተ ክርስያን ደጅ ጥኝልኝ።

ተቅማጥ ስለያዘኝ ORS ላኪልኝ። ብታገኝ 3 ብር ላኪልኝ።

ግን በህይወት ያለሽ አይመስለኝም። አሰሙ እንዴት ነው?

ትኩረት ወደ አማራው ( Mesay Mekonnen)

ትኩረት ወደ አማራው

ህወሀት በቅርቡ በትግራይ ውስጥ አንድ ሚስጢራዊ ስብሰባ አድርጎ ነበር። በስብሰባው ላይ የህወሀት የጦር መኮንኖች ብቻ የተገኙ ሲሆን መድረኩን የሚመሩት አባይ ጸሀዬ፡ በረከት ስምዖንና የህወሀት ጄነራሎች ነበሩ። ዓላማው የዶ/ር አብይ አህመድን ስልጣንና አካሄድ ከህወሀት ጥቅምና ፍላጎት አንጻር መፈተሽ ነበር። የትግራይ ተወላጆች ከፌደራል መንግስቱ ቁልፍ ቦታዎች ተገፍትረው ወጥተዋል የሚል የከረረ ቅሬታ ከህወሀት የጦር ሹማምንቶች የተሰማ ሲሆን እነአባይ ጸሀዬ ”አሁንም ቁልፍ ቦታዎች በእጃችን ነው። መከላከያውን ከህወሀት መዳፍ ፈልቅቆ የሚነጥቅ በተአምር አይኖርም። ዋናዋናዎቹ የመከላከያ ክፍሎች ትግራይ ገብተዋል። የሚያሰጋን ነገር የለም” በሚል ለማረጋጋት መሞከራቸው ተሰምቷል።

የሚስጢራዊው ስብሰባ ዋና ዓላማ ከአማራው ህዝብ የሚመጣውን ቀጣይ አመጽ እንዴት እንመክተዋለን የሚል ነበር። ህወሀት ከአማራው ህዝብ ከፍተኛ አመጽ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በስጋት እየገለጸች ነው። እነበረከትም በሚስጢራዊው ስብሰባው ላይ እንዲታደሙ የተደረገውም ይህን አይቀሬ አመጽ እንዴት መመከት ይቻላል የሚለውን ለመምከር ነው። በረከት ስለህወሀት ጥቅም በአማራው ላይ የተጣበቀ አልቅት መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። ህወሀት አደጋ ውስጥ ስትገባ ከእነስብሃት ነጋ ጎን ተሰልፎ ምሽግ የሚይዝ መሆኑም ይታወቃል። አሁንም ይህን ‘ከህወሀቶች በላይ ህወህት’ መሆኑን እያሳየ ነው።

ሰሞኑን ብአዴን ቁርጡ ይለይለታል የተባለ ስብሰባ ተቀምጦ ከርሟል። እነበረከት የመስመር ክህደት ተፈጽሟል የሚል አጀንዳ ቀርጸው ህወሀት ላይ ያመጹ የድርጅቱን አመራሮች ለማሸማቀቅና ከተቻለ ለማሰር የጠሩት ስብሰባ መፈንቅለ አጀንዳ ተፈጽሞበታል። ለዓመታት የህወሀት ተላላኪ፡ አሽከር፡ ባሪያ እየተባለ ሲረገም የነበረው ብአዴን በተለይም መካከለኛና የታች አመራሩ ”ይለያል ዘንድሮ” ብሎ ተነስቷል። የለማ መገርሳን ድል በብ አዴን ውስጥ ለመድገም እድሉ ያለው ገዱ አንዳርጋቸው በመፈንቅለ አጀንዳው ተጠቅሞ ሊሰለቅጡት የተዘጋጁትን እነበረከትን አንገታቸውን አስደፍቷል። ለምሳ ሲያስቡት ቁርስ አደረጋቸው ነው የተባለው። የብአዴን አባላት እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው የእነበረከትን ጎራ ከፍ ዝቅ አድርገው ሲያንቆራጥጡ እንደነበር የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል። ስለመስመር ክህደት የተጠራው ስብሰባ የአማራውን ህዝብ ክደው ለህወሀት ያደሩ የብአዴን አመራሮች ላይ ውዕግዝ ከማዕርዮስ የወረደበት መድረክ ወደ መሆን ተቀይሯል።

የወልቃይት ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆኖ ተነስቷል። ራያ፡ መተከል፡ ከትላንት እስከዛሬ የአማራው መፈናቀል፡ የትግራይ የበላይነት፡ ያልተነሳ ጉዳይ የለም። ብአዴን ቆርጧል። አዲሱ ለገሰ፡ በረከት ስምዖን፡ ካሳ ጥንቅሹና የመሳሰሉ የህወሀት አደግዳጊዎች ሲቀሩ አብዛኛው አመራርና አባል ”በቃ!” ያለ መስሏል።

በሁኔታው የተደናገጡት በረከትና አዲሱ ለገሰ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ በረዋል። ስብሰባው ሳይስማሙ ተጠናቋል። ህወሀት በትግራዩ ሚስጢራዊ ስብሰባ የሰጋችው እውነት እየሆነ ይመስላል። በረከት የስብሰባውን ውጤትና የገጠመውን ብርቱ ፈተና ለህወሀት አለቆቹ ሪፖርት ሊያቀርብ ምሽቱን እንደበረረ ነው የውስጥ ምንጮች የሚገልጹት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳይነሳ የተደረገበት ዋናው ምክንያትም በአማራው ህዝብ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንቅልፍ የሚነሳ በመሆኑ ነው። ብአዴን ውስጥ የተነሳው ጸረ ህወሀት ስሜት ከአዳራሽ ወጥቶ ህዝቡ ዘንድ እንዳይሰማ እነበረከት ርብርብ ሲያደርጉ እንደነበርም ታውቋል። ከውስጥ ቆራጦቹ የብ አዴን አባላት የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዮን በቅርበት እንዲከታተል መልዕክት አድርሰዋል። ይሀው ደርሷል።

እነበረከት አዲስ አበባ ናቸው። ህወሀት አደጋ ውስጥ እንዳለች፡ ሊያስተነፍሱት ቃል ገብተው የጠሩት ስብሰባ እንደተቀለበሰ፡ አዝማሚያው ጥሩ እንዳልሆኑ ሪፖርታቸውን ያቀርባሉ። ከእንግዲህ የአማርው ህዝብ ወደ ኋላ አይመለስም። የብ አዴን አብዛኛው የብ አዴን አባላትም ከህዝቡ ጋር ለመቆም ወስነዋል። እናም ህወሀትን ምን ሊውጣት ነው? የኦህዴድ ማፈንገጥ ላይ ብ አዴን ሲጨመርበት የህወሀት ህልውና ያከትማል።

ህወሀት የመጣባትን አደጋ የምትወጣው ሃይል በመጠቀም እንደሆነ ታምናለች። አሁንም ሃይል ለመጠቀም እያሰበች እንደሆነ ሾልከው የሚወጡ መረጃዎች ያሳይሉ። የምዕራብ ዕዝ አዛዡ ሜ/ጄ ፍሰሀ ኪዳኑ ወደ አዲስ አበባ መጠራቱም እየተወራ ነው። የአማራውን ክልል በተለይም አመጽ ይነሳባቸዋል ተብለው በተለዩ አከባቢዎች ወታደሮችን ለማስፈር በህወሀት በኩል እቅድ እንዳለም ይነገራል። እንግዲህ የብ አዴን የመካከለኛና የታች አመራርሮችና መላው የብ አዴን አባላት ህዝባቸውን ሊክሱ የተዘጋጁ መስለዋል። ህዝቡ በንቃት እንዲከታተል ጠይቀዋል። ትኩረት ወደ አማራው ክልል ማድረጉ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው
Mesay Mekonnen

የበረሃው ዲፕሎማት ( ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የበረሃው ዲፕሎማት

ስለአንዳርጋቸው ጽጌ መጻፍ ከባድ ነው። ስብዕናውን፡ የተጓዘባቸውን የህይወት መስመሮች፡ ከልጅነት እስከዕውቀት የወጣባቸውንና የወረደባቸውን ዳገትና ቁልቁለት በብዕር ቀለም ወረቀት ላይ ለመግለጽ ቃላት አቅም ያላቸው አይመስለኝም። እሱ ልዩ ሰው ነው። አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ የአንዳርጋቸውን የተለየ ስብዕና ለመግለጽ የተጠቀመው ሀረግ ምናልባት የቀረበ መግለጫ ሊሆን ይችላል- ”አንዳርጋቸው- የኢትዮጵያ ልዩ አፈር”

በአካል አንድ ጊዜ ነው የተገናኘነው። በመንፈስ ግን ሁሌም አብሮኝ የሚኖር ነው። ዛሬ ከጨለማው እስር ቤት ውስጥ ቢሆንም ውስጣችን የተከለው የትግልና የጽናት መንፈስ ከልባችን ጓዳ ሁሌም እንዲኖር አድርጎታል። ለእኔ አንዳርጋቸው አንድ ሰው ብቻ አይደለም። እሱ ብዙ ነው። የትግል አጋር፡ አስተማሪ፡ መሪ፡ ሞዴል፡ የሙያ አማካሪ፡ ጸሀፊ፡ ገጣሚ፡ ዲፕሎማት… ዝርዝሩ ይቀጥላል።

ላንቺ ነው ሀገሬ የተሰኘው ዜማ መቼም ስለሀገር ፍቅር የሚንቦገቦግ ኢትዮጵያዊ ከልቡ እያነባ የሚያዜመው ነው። ይህን ዜማ ግጥሙን የጻፈው አንዳርጋቸው መሆኑን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? አንዳርጋቸው የደራሲነት ደም አለው። ለመጽሀፍ ያልበቁ ብዙ ጽሁፎች እንዳሉት አውቃለሁ። ቁጭ ካለ ይጽፋል። በረሃ ውስጥ አረፍም፡ ጋደምም ካለ ይሞነጫጭራል። ላንቺ ነው ኢትዮጵያ ‘’ብሄራዊ መዝሙር’’ የመሆን አቅም ካላቸው ግጥሞች ተረታ የምመድበው ነው። ትልቅ ስራ ነው። ጥልቅ የሀገር ፍቅር የተገለጸበት ነው። አንዳርጋቸው ስለእናት ሀገሩ እስከጥግ ያለውን ፍቅርና መንሰፍሰፍ ያሳየበት ግጥም ነው- ላንቺ ነው ኢትዮጵያ።

ስለአንዳርጋቸው ብዙ ማለት ይቻላል። ብዙም ተብሏል። ለሶስት ቀናት ለሚካሄደው የአንዳርጋቸው ይፈታ ዘመቻ የሚሆን አንድ ነገር ልጽፍ ተነሳሁ። ሰለምኑ ልጻፍ? ስለእሱ ምን የተለየ ነገር እኔ ዘንድ አለ? አንድ ቀን በተገናኘንበት አጋጣሚ ያለኝን ልጻፍ ይሆን? እሱም ቢሆን ለሌላው ከሆነው፡ የተለየ አይደለም። ነገር ግን ከተሰለፍኩበት ሙያ አንጻር ያካፈለኝ ምክሩ ነውና ልግለጸው። ለመጨረሻ ጊዜ ዋሽንግተን ዲሲ የመጣ ጊዜ ነው። በአካል ሳገኘውም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። የመጨረሻ እንዳልሆነ ደግሞ እርግጠኛ ነኝ። ሲናገር መቼም እንደጥዑም ዜማ ከጆሮ የሚንቆረቆር፡ አንደበቱ የሚጥም፡ ትህትናው የሚማርክ ሰው ነው። የሀሳቡ ጥልቀት፡ ያስደምማል። ከሚናገረው መሬት ጠብ የሚል ነገር የሚወጣው አይደለም። ልብ ሰርስሮ፡ አእምሮን በርብሮ ከህሊና ጓዳ የማይፋቅ ትልቅ መልዕክት ትቶ የሚያልፍ ነገር ነው ከአፉ የሚወጣው። ሲናገር ውሎ ቢያድር የማይሰለች ተአምረኛ ሰው ነው አንዳርጋቸው።

እናም እንዲህ አለኝ ‘’የእናንተ ሃላፊነት ትልቅ ነው። ሙያውን ለነጻነት መሳሪያ አድርጋችሁታል። ግን አደራ። መሬት ላይ ያለው ትግልና ፕሮፖጋንዳው እንዳይቀዳደሙ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ። ትግሉ ከኋላ ቀርቶ ፕሮፖጋንዳው ከቀደመ አደጋው ከባድ ነው። እኛንም ልታግዙን የምትችሉት በህዝቡ ዘንድ ታማኝነታችሁን በሚገባ መሰረት ካሲያዛችሁ ነው። ፕሮፖጋንዳው ከቀደመ መታመን ይርቃችኋል። ያን ጊዜ ትግሉም ይጎዳል።’’ ይህ የአንዳርጋቸው ምክር ነው። ከጆሮዬ ላይ ድምጽ አሁን ድረስ ያቃጭላል። በሀገር ፍቅር ስሜት፡ በወኔ፡ በነጻነት ጥማት የተሰለፍንበትን ሙያ እንዳከብረው፡ እንድጠብቀው ከልቤ ያስቀመጠው ድንቅ አባባል ነው።

የሙያ አማካሪ ያልኩትም ያለምክንያት አይደለም። የሙያው ምሶሶ የሆነውን የመታመን ዋጋ የሚያውቅና የሚያከብር የምር እውነተኛ ሰው ሆኖ ያገኘሁበት ምክር ነው። በተለምዶ የምናውቀው ፖለቲከኛ ሆኖ አላገኘሁትም። ፖለቲካ ቁማር ነው፡ አስቀያሚ ጨዋታ ነው፡ ማይክ ከያዘ ውሸት ተናግሮ ስልጣን ለመያዝ የሚፍጨረጨር ነው። ይህ አንዳርጋቸው ጋር አይሰራም። ፖለቲካ እሱ ዘንድ ቁማር አይደለም። ጨዋታም አይደለም። ለአንዳርጋቸው ፖለቲካ እውነት ነው። ለህዝብ ነጻነት የሚገለገልበት መሳሪያ።

ስለ አንዳርጋቸው ያልተጻፈ የለም። እሱን በግል ከሚያውቁት አንስቶ በታላቅነቱ የተዛመዱት በሚሊየን የሚቆጠሩ የመንፈስ ልጆቹ ስለእሱ ተናግረው አይጨርሱም። ይሀው አነገሱት። ታላቅነቱን መሰከሩ። ለጠላትም ለወዳጅም የአንዳርጋቸው ማንነት ከአጽናፍ እስከአጽናፍ ይታወቅ ዘንድ የመንፈስ ልጆቹ እንቅልፍ አጥተው እያደሩ ነው። ከዚህ በላይ ታላቅነት ከወዴት ይኖር ይሆን?
ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ወዳነሳሳኝ ጉዳይ ላምራ። የበረሃው ዲፕሎማት።

ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ኤርትራ አቅንቼ ነበር። እውነት ለመናገር ወደ ኤርትራ እንድሄድ በግሌ ውሳኔ ላይ የደረስኩት በአንዳርጋቸው ምክንያት ነው። ከእሱ መታፈን ወዲህ ውስጤ የተፈጠረው እልህና ቁጭት በቃላት የሚገለጽ አይደለም። በአረመኔዎች እጅ ላይ ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ሁል ጊዜ ራሴን እጠይቃለሁ። ‘’አንዳርጋቸው ከእኛ የተለየ ለኢትዮጵያ ምኗ ስለሆነ ነው ይህን ሁሉ ዋጋ የሚከፍለው?’’ በእሱ ጫማ መግባት የሚቻል አይደለም። የእሱን ያህል ጥንካሬ መላበስ ከእንደገና መፈጠር የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። ሰው እንዴት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለሀገሩ እንዲህ መከራውን ይበላል? ከትላንት እስከ ዛሬ ፡ ከኢህአፓ ዘመን እስከአሁን፡ እድሜውን በሙሉ ስለራሱ ሳይሆን ስለእኛ የኖረ ሰው እንዴት በእነዚህ የትውልድ ኩሶች ስቃይና መከራ ይፈጸምበታል? ለእኔ ከቁጭትም በላይ ውስጤን የሚንጠኝ ጉዳይ ነበር። በየትኛውም መለኪያ ከእግሩ በታች በሆኑ ሰዎች እጅ ላይ መውደቁ ያንገበግባል። ከአጥንት ድረስ በሚዘልቅ የቁጭት ስሜት ያማል።

እናም ቢያንስ የሄደበትን ያህል ርቀት መሄድ ባልችልም የተኛበትን አፈር ለማየት ውሳኔ ላይ ደርሼ ነው ወደ ኤርትራ ያቀናሁት። ኤርትራ የአቶ አንዳርጋቸው ሁለተኛ ቤቱ ናት። ከአስመራ አውሮፕላን ማረፊያ አንስቶ በመንገድ ላይ ስንጓዝ መንገድ ላይ የማየው ሁሉ የእሱ ዱካ የረገጠው እየመሰለኝ በስስት ነው እራመድ የነበረው። ስለእሱ የተለየ መሆን ከማውቀው በላይ የማላውቀው ብዙ ነገር እንዳለ የተረዳሁበት ቆይታ ነው- የኤርትራው። የሚያድርበትን፡ የሚለብሰውን፡ የሚጫማውን፡ የሚበላውን የሚጠጣውን ሁሉን አየሁት። ተአምር ነው። እነዚያ የትውልድ ጥቀርሻዎች ሀገሪቱን በአጥንቷ እስክትቀር ይግጧታል፡ አንዳርጋቸው ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሲል ስጋውን በሚበላ ትግል ውስጥ ለመግባት ይወስናል። የሁለት ዓለም ሰዎች። ሁለቱም የኢትዮጵያ ልጆች። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር።

አንዳርጋቸው የተለየ መሆኑ ኤርትራውያንም በሚገባ ይምሰክሩለታል። አንድ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ የሚሰራ ሰው ያጫወተኝን ብቻ ላካፍላችሁ። በኤርትራ በርካታ የኢትዮጵያ የነጻነት ድርጅቶች አሉ። በብሄር ከተደራጁት አንስቶ ከ10 በላይ ነጻ አውጪዎች ኤርትራ መሽገዋል። እናም የጋራ ስብሰባ ሲኖራቸው መሪዎቻቸው ከበረሃ መጥተው አስመራ ይገናኛሉ። ታዲያ ሁሉም የድርጅት መሪዎች የሚንቀሳቀሱበት መኪና አላቸው። ሹፌር አላቸው። ስብሰባ ሲመጡ በሹፌራቸው ታጀበው ነው። አንዳርጋቸው ግን አንዲት ሳይክል አለችው። ከአስመራ መኖሪያ ቦታው የስብሰባ አዳራሽ ሲመጣ በዚያች ሳይክል የአስመራን ዳገትና ቁልቁለት ወጥቶና ወርዶ ነው። በላብ ተነክሮ እያለከለከ ከስብሰባው እንደሚገባ ነው ኤርትራዊው ያጫወተኝ። ሳይክሏን አይቻታለሁ። ከሚያድርበት ክፍል ተንጠልጥላ ባየኋት ጊዜ አይኖቼ እምባ አረገዙ። የእግሩን አሻራ ከሳይክሉ መርገጫ ላይ ያየሁት መሰለኝ።

ወደ በረሃ አመራን። ከአስመራ ተነስቶ በስተደቡብ ከረን፡ ባረንቱንና ሰነዓፌን አልፎ ከታጋዮቹ መንደር እስኪደረስ ያለው በረሃ አይጣል ነው። ጸሀይ ያለ የሌለ ጉልበቷን የጨረሰችበት ቦታ ይመስላል። ፊት ያከስላል። የተረገመ ምድር፡ እግዜር ሲፈጥረው በኩርኩም የደቆሰው አከባቢ ነው። ሰው እንዴት በዚህ በረሃ አይደለም ለመኖር ሊያልፍበት ይመጣል? አይ አንዳርጋቸው?! ያንተ ነገር በምን ቃል ተነግሮ ይበቃ ይሆን? ወደ አንዳርጋቸው መኖሪያ አመራን። ስድስት ልጆችን ይዞ ትግሉን ወደጀመረበት ጭው ያለ በረሀ። የማየው ሁሉ የአንዳርጋቸው እጅ የነካው እየመሰለኝ እሳሳለሁ። ቀና ስል ከሰማይ ላይ የአንዳርጋቸው ምስል የማይ እየመሰለኝ ድንግጥ እላለሁ። ከርቀት ጉብ ያለ ነገር ላይ ተቀምጦ የማየውም ይመስለኛል። የአንዳርጋቸው ልጆች ስለአዳርጋቸው እየዘመሩ ተቀበሉን። የማየው ነገር የበረሀውን ጉዳት አስረሳኝ። የአንዳርጋቸው ልጆች ቲሸርቱን አድርገው በፍጹም የጽናት ስሜት ሳገኛቸው ሰውዬው ይበልጥ ገዘፈብኝ። እንዴት ያለ ድንቅ ሰው ነው ባካችሁ?!

በረሃው ስለአንዳርጋቸው ድካም ይመሰክራል። ጥሻው የአንዳርጋቸውን ጽናት ይናገራል። ያቺን የሚተኛባትን ሰሌን አየኋት። ጠረኑ እንዳለ ነው። የጀግና ጠረን። ልብ ያሸፍታል። የመጀመሪያ የቆረቆራትን የትግል ሰፈር በሚገባ ጎበኘኋት። አፈር ቁጥቋጦው ድንጋይ ጠጠሩ ስለአንዳርጋቸው የሚነግሩኝ እየመሰለኝ አዳምጣቸኋለሁ። ምሽት ላይ ፍየል ታርዶ ክሽን ያለ ጥብስ ተመገብን። የአንዳርጋቸው ልጆች የሰሩት ጥብስ ጣት ያስቆረጥማል። ሙያም ያስተማረን እሱ ነው። ሰው እንዳይመስልህ? እንደኛው አፈር ላይ ተንከባሎ፡ እንደኛው ሰርቶ ለፍቶ የሚኖር ሰው ነው። እንጨት ፈልጦ እሳት አንድዶ፡ ሽሮ ሰርቶ የሚያበላን፡በረሃውን ያስረሳን፡ በእውቀት ያነጸን፡ በጽናት ያቆመን፡ ታላቅ አባታችን መሪያችን ነው። የአንዳርጋቸው ልጆች ስለአንዳርጋቸው ሲናገሩ አመሹ። ልብ ይነካል። ከአእምሮዬ በላይ ሆነብኝ። እሱ ፊት መቆም ከባድ ነው። እሱ በእርግጥም ትልቅ ነው። ልዩ ነው።

ከሰማሁት አንዱን ላካፍላችሁ። አንዳርጋቸው የበረሀው ዲፕሎማት ነው። በኤርትራ በረሃ የመሸጉ የኢትዮጵያ የተለያዩ የነጻነት ቡድኖች የጎሪጥ የሚተያዩ፡ በአንድነት ለመስራት ዳገት የሆነባቸው፡ በየአጥራቸው ውስጥ ሆነው የብቻ ትግል ላይ የተጠመዱ፡ ነበሩ። የአንዳርጋቸው ኤርትራ መግባት ይህን ታሪክ እንደቀየረው ይነገራል። አንዳርጋቸው ከሁሉም ይግባባል። ከሁሉም ጋር ይሰራል። የተጣላን ያስታርቃል። የነጻነት ድርጅቶቹን ለማቀራረብ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። አንዳርጋቸው የስፖርት ውድድሮች በነጻነት ቡድኖቹ መሃል ያደርጋል። በእግር ኳስ፡ በእጅ ኳስና በሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች የእርስ በእርስ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር አድርጓል። በርቀት የሚተያዩ ቡድኖች በአንዳርጋቸው ተቀራርበዋል። የተኳረፉ ታርቀዋል።

አንዳጋቸው በአፋር ነጻ አውጪ መንደር ስሙ ትልቅ ነው። በደሚት ሰፈር የሄደ ሰው ስለአንዳርጋቸው መልካም ሰምቶ ይመልሳል። ከጋምቤላ፡ ቤንሻንጉሉ፡ ከሁሉም ዘንድ አንዳርጋቸው አንድ ነው። አስታራቂ፡ ዲፕሎማት። ድግሳቸው ላይ የክብር እንግዳ ነው። ወታደራዊ ምርቃት ሲኖር በክብር ተጥርቶ ሽልማት የሚሰጠው አንዳርጋቸው ነው። እንደመሪ በሁሉም ቦታ ስሙ ትልቅ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር የነበሩት ብ/ጄነራል ከማል ገልቹ አንድ ምሽት አስመራ ቢራ እየጠጣን ስለአንዳርጋቸው በነገሩኝ ልሰናበታችሁ።

‘’እዚህ ያሉት ሃይሎች አንድም ቀን ቁጭ ብለው አውርተው አያውቁም። እኔ እዚህ ከመጣሁ ስምንት ዓመት ሆነኝ። ለምሳሌ ከአርበኞች ግንባር መሪው ከቶ መዓዛው ጌጡ ጋር ተገናኝተን አናውቅም። ለዚህ ሁሉ ዓመታት እነሱም በዚያ እኛም በዚህ እንራመዳለን እንጂ ለሰላምታ እንኳን የሚበቃ ግንኙነት አልፈጠርንም። አንዳርጋቸው ከመጣ በኋላ ግን ከሰላምታ ባሻገር ስለጋራ ትግል ማውራት ጀመርን። አንዳርጋቸው አገናኝ ድልድይ ነበር። የእሱ በወያኔ እጅ መውደቅ የተፈጠረውን መልካም ግንኙነት እንዳያጠፋው እሰጋለሁ።’’

ይህ በኤርትራ የሁሉም መሪዎች ቃል ነው። አንዳርጋቸው የበረሃው ዲፕሎማት ነው። አንተ ሰው ድንቅ ነህ። ታላቅም ነህ። ከብረቱ ፍርግርግ ውስጥ ሆነህም ጠላትን የምታርበደብድ ጀግና ነህ። እዚያው አትቀርም። የለፋህላት፡ የገረጣህላት፡ የተንከራተትክላት ሀገርህ ላይ በነጻነት እንደምናይህ ተስፋ አለኝ።

“ለአንዳርጋቸው ፅጌ ከታገሉት መካከል ቀዳሚው! አሸናፊ አካሉ ይባላል”። ( በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው )

ለአንዳርጋቸው ፅጌ ከታገሉት መካከል ቀዳሚው!

አሸናፊ አካሉ ይባላል። በእነ ዘመነ ካሴ ክስ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ ነበር። በዚህ ክስ ስምንት አምት ከአምስት ወርም ተፈርዶበታል።

አሸናፊ አካሉ “ከአንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገናኝታችኋል” ተብለው ከተከሰሱት ወጣቶች መካከል ነው። ወቅቱ አንዳርጋቸው ታፍኖ ድምፁ የጠፋበት ወቅት ነበር።

እነ አሸናፊ አካሉ አንዳርጋቸውን ምስክር ጠርተው፣ ለሰብአዊ መብቱ ለመታገል ጥረዋል!

እነ አሸናፊ የመንግስት ጠበቃ ነበራቸው። በመሰረቱ ጠበቃ ነበር የመከላከያ ምስክር ዝርዝር ማቅረብ የነበረበት። እነ አሸናፊ 1ኛ ቁጥር ላይ አንዳርጋቸወረ ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት አስቀምጠው ሲመለከት ጠበቃው ደነገጠ። መንግስት የሌላ ሀገር ደህንነትን በሚሊዮን ዶላር ገዝቶ ያመጣውን አንዳርጋቸው ፅጌ የሚባል ሰው መከላከያ መቁጠር ለጠበቃው ቢያስፈራ አይገርምም። ጠበቃው ደንግጦ አልቀረም። “ይቅርባችሁ!” ብሎ ቢመክራቸው! አላመኑለትም። እነ አሸናፊ አንዳርጋቸውን በመከላከያ ምስክርነት የጠሩት በእሱ ምስክርነት ፍርድ ቤቱ ነፃ ይለቀናል ብለው አይደለም። እንዲያውም እንደሚብስባቸው አይጠፋቸውም!

ሕጉ በሚለው መሰረት ማንም ሰው በምስክርነት ከተቆጠረ ቀርቦ መመስከር አለበት። በታዕምር ይህ ህግ ከሰራ ደግሞ አንዳርጋቸው ፍርድ ቤት መቅረብ ይችላል። ሰው ያየዋል። እሱም ምስክርነቱን ሳይሆን ፍርድ ቤቱን ተጋፍቶ የደረሰበትን ሊናገር ይችላል በሚል ነው። በመሆኑም ጠበቃቸው “ይቅርባችሁ፣ ማንን እየጠራችሁ እንደሆነ አውቃችሁታል? አብዳችኋል……” ስላላቸው አልተውትም። ጠበቃው ምክሩን አልሰሙት ሲሉ የወሰደው አማራጭ “እኔ ከደሙ ነፃ ነኝ” ማለትን ነው። አይፈረድበትም! ” የምስክሩን ዝርዝር ራሳችሁ አቅርቡ” አላቸው።

በመሆኑም እነ አሸናፊ በፍትህ ስርዓቱ ባያምኑበትም አንዳርጋቸው ለሕዝብ እንዲታይ፣ ምን አልባትም ፍርድ ቤት ቀርቦ የደረሰበትን በደል እንዲናገር ጥረት አደረጉ። “ከአንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገናኝታችኋል ብላችሁ ክስ መስርታችሁብናል፣ ስለሆነም ለቀረበብን ክስ መከላከያ ምስክር ሊሆነን የሚችለው አቶ አንዳርጋቸው ነው። አቶ አንዳርጋቸው ቀርቦ ስለመገናኘት አለመገናኘታችን ይመስክር” ብለው መከላከያ ምስክር ጠሩት።

መከላከያ አስመዝግቡ ሲባሉ “1ኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ!” አሉ እነ አሸናፊ

መሃል ዳኛው ጀሮውን ያመነ አይመስልም። የቱ አንዳርጋቸው ስለመሆኑ ጠየቀ።

አሸናፊም ” የግንቦት 7 ዋና ፀሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገንኘታችኋል ተብለን ነው የተከሰስነው፣ አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር ይገኛል ተብሎ በመንግስት ቴሌቪዥን ተነግሯል። እሱን መከላከያ ምስክር አድርገመዋል”

መሃል ዳኛው ታረቀኝ “መከላከያ የሚሆን ሰው አጥታችሁ ነው?”

(እነ)አሸናፊ አካሉ:_ “ከእሱ ጋር ተገናኝታችኋል ስለተባልን ሊከላከልልን የሚችለው ብቸኛው ሰው እሱ ነው።”

ዳኞቹ ተወያይተው እንዲያስመዘግቡ ተፈቀደ!

በመጀመርያው የምስክርነት ቀን አልቀረበም። ፖሊስ መንግስት ዶክመንተሪ የሰራበትን አንዳርጋቸው ፅጌን “የት እንዳለ አላውቅም” አለ። ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው የሞትና የእድሜ ፍርደኛ ስለሆኑ ቃሊቲ ሊታሰር ስለሚችል ለቃሊቲ ትዕዛዝ አስፃፈ። በቀጣዩ ቀጠሮ ቃሊቲ ማዘዧ አልተፃፈልኝም ብሎ ቀጠሮ አራዘመባቸው። ደግመው ማዘዣ ላኩ። ቃሊቲም ቀጥሎ “እኔ ጋር የለም” አለ።

ይህ ሁሉ እነ አሸናፊ ተሰላችተው የአንዳርጋቸውን ምስክርነት እንዲተውት ነው። እንደማይተውት ሲታወቅ ዐቃቤ ሕግ ፍርድቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ምስክር ሆኖ እንዳይቀርብ ይታገድልኝ አለ። ታገደለት። እነ አሸናፊ አካሉ ይግባኝ ጠየቁ። አቶ አንዳርጋቸው ፍርድ ቤት ቀርቦ ይመስክር ተባለ። ቃሊቲ እንዲያቀርበው ትዕዛዝ ተፃፈ። ቃሊቲ እስር ቤት ተከታታይ ቀጠሮዎችን የማይረባ ምክንያት አቅርቦ አንዳርጋቸው ሳይቀርብ ቀረ።

እነ አሸናፊ ሲሰለቻቸው ይተውታል በሚል ነበር። እነ አሸናፊ አልሰለቹም። ዐቃቤ ሕግ ግን ይግባኝ “ቀርቦ ይመስክር” ባለበት ሌላ እግድ ጠየቀ። ምስክርነቱ ታገደ። እነ አሸናፊ ደግመው ይግባኝ አሉ። ተፈቀደላቸው። ቃሊቲ አላቀርብም አለ።………ከዛም ብዙ ሂደቶች ነበር። እነ አሸናፊ አንዳርጋቸው በሕዝብ እንዲታይ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። ድርጅቶች ከታገሉለት ባልተናነሰ እስረኞቹ ስለ አንዳርጋቸው ሰብአዊ መብት ታግለዋል። አልቀረበም እንጅ! ሕግ ባለመከበሩ!

አሸናፊ አካሉ የተሰማውን በግልፅ የሚናገር ሰው ነው። ስለ እሱ፣ ስለሌሎችና ስለ ሀገሩ በመናገሩ በእስር ቤቱ አስተዳደሮች ተጠመደ። የቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ ተገኘለት። ሸዋሮቢት ተወስዶ ተሰቃየ። በቂሊንጦ ቃጠሎ ክስ ተመሰረተበት። “በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ፍትህ አይገኝም” የሚለው አሸናፊ አካሉ በአሁኑ ክስ “ጠበቃ አያስፈልገኝም” ብሎ በግሉ ይሟገታል!

አሸናፊ ይህ ሁሉ በደል ደርሶበት አሁንም ብርታቱ የሚገርም ነው!

ብሄር ተኮር ፌደራሊዝሙ ሳይፈርስ ስለ አንድነት ማውራት ከንቱ ድካም ነው (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም)

ብሄር ተኮር ፌደራሊዝሙ ሳይፈርስ ስለ አንድነት ማውራት ከንቱ ድካም ነው

አሁን ባለው የፌደራሊዝም ስርዓት አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት አይቻልም። ላለፉት 26 ዓመታት ክልል ከአገር በልጦ እንዲታይ የተደረገው ቅስቀሳ፣ ቀላል የማይባል የአዲሱ ትውልድ አባላትና “ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ” ሲሉ የነበሩ ከእኔ በፊት የነበሩና የእኔ ትውልድ ሰዎች ሳይቀሩ “ከአገሬ በፊት ክልሌ” እያሉ ሲዘምሩ መስማት እንግዳ አይደለም። ትናንት ባንዲራዋን ታቅፈን ለአንዲት ኢትዮጵያ አብረን የዘመርን ሰዎች፣ ዛሬ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያላችሁ አታለቃቅሱ” ብለው ሲናገሩን ስንሰማ፣ እኛን ፖለቲካ የማይገባን ግትሮች ራሳቸውን ደግሞ ፖለቲካ የሚገባቸው ምጡቆች አድርገው ሲቆጥሩ ስናይ ከመገረም ውጭ ሌላ ምን ይባላል? ከወያኔ በሁዋላ በመጣው ትውልድ አልፈርድም። ከወያኔ በፊት የነበሩ ትውልዶች “ክልሌን ወይስ አገሬን?” የሚል አንዱን አስቀድሞ ሌላውን የማስከተል ምርጫ አልነበራቸውም፤ እያንዳንዱ ዜጋ ታማኝነቱ ሁሉ፣ አንድና አንድ፣ ለአገሩ ብቻ ነበር። በጊዜው የነበረው የክፍለ ሃገራት አደረጃጀት የተለያዩ ብሄረሰቦችን የሚያቅፍ በመሆኑ፣ በአንድ ክፍለሃገር ስር ይኖር የነበረ የአንድ ብሄረሰብ ተወላጅ “ከአገሬ በፊት ክፍለሃገሬ” የሚልበት አጋጣሚም ይሁን እድል አልነበረውም። ዛሬ ያለው የክልል አወቃቀር ከብሄር ማንነት ጋር በእጅጉ ተቆራኝቷል። “ክልል ይፍረስ” ብለህ ብትናገር “ብሄርህ ይጥፋ” እንዳልክ ተቆጥሮ ጦር ይሰበቅብሃል። ክልልን የብሄር ማንነት መገለጫ አድርገህ ደግሞ፣ በአንድ አገር ውስጥ “አድልዎ”ን ልታጠፋ አትችልም፤ ያለውን የክልል አስተዳደር እንደያዝክ አድልዎን አጠፋሁ ብለህ የፈለከውን አይነት እርምጃ ብትወስድ እንኳን “ ለብሄሩ አዳልቷል” ከሚል ትችት አታመልጥም ።

ህዝብ፣ ከክልሉ በፊት አገሩን እንዲያስቀድም ከፈለክ አሁን ያለውን ብሄር ተኮር የፌደራል አወቃቀር መቀየር የግድ ይኖርብሃል፤ ይህን ሳትቀይር ጠንካራ አገር እገነባለሁ ብለህ የምታልም ከሆነ ህልምህ ህልም ሆኖ ይቀራል እንጅ ለፍሬ አይበቃም። የፌደራል አወቃቀሩን ሳትቀይር የወልቃይት ጠገዴን፣ የራያን፣ የቁጫንና ሌሎችንም ከማንነትና ከመሬት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን፣ ጥያቄውን የሚያቀርቡትንና ጥያቄውን የሚቃወሙትን ዜጎች እኩል በሚያረካ መልኩ እፈታለሁ፣ ማለት ዘበት ነው። የአንድ ክልል መሬት የክልሉ ነዋሪዎች ሃብት ብቻ ተደርጎ እየተቆጠረ፣ ክልሎች በድንበር የተነሳ እርስ በርስ ቢጣሉ ሊገርመን አይገባም። የአንዱ ክልል መሬት የአገሪቱ ዜጎች መሬት እንደሆነ ሊታሰብ የሚችለው ከብሄር ማንነት ጋር የተያያዘውን የፌደራል አወቃቀር መለያየት ሲቻል ነው። ሁለቱ ሲለያዩ የሚፈጥረው አደጋ ቢኖርም፣ ከረጅም ጊዜ ጥቅም አንጻር ሲታይ ጉዳቱ አነስተኛና ህዝብን አስቀድሞ በማሳመንና ጥሩ አማራጭ የፌደራል አወቃቀር በማቅረብ የሚስተካከል ነው።

ብሄሮች፣ ሌሎች ብሄሮች የማይነኩባቸው የራሳቸው ብቻ የሆነ የተከለለ መሬት ካልተሰጣቸው በስተቀር መብታቸው አይከበርም የሚል እሳቤ ያለው ሰው፣ የሚያወራው ስለ ብሄሮች መብት ሳይሆን አንድ አዲስ የተለዬ አገር ስለመመስረት ነው። በኢትዮጵያ ድንበር ስር ያለው መሬት ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝብ የጋራ ሃብት ነው ብሎ፣ ሌሎች የሰው ልጅ የሚገባውን መብቶች ሁሉ መመለስ ይቻላል። የኢትዮጵያ መሬት ሁሉ የራሳቸው መሬት እንደሆነ እያሰቡ፣ ዜጎች ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ማድረግ ይቻላል።

መሰረታዊ የሚባሉት የሰው ልጅ መብቶችና አስተዳደራዊ አከላለሎች በቀጥታ የሚያገናኛቸው ነገር የለም። የኦሮምያ አርሶአደር “የኦሮምያ መሬት የኦሮሞ ብቻ ነው” ስለተባለ ከዚህ በፊት በሸዋ ክፍለ ሃገር ስር በነበረበት ጊዜ ከነበረው በተለዬ የሚጠቀመው ነገር የለም፣ እንዲያውም በህወሃት ዘመን ሲጎዳ እንጅ ሲጠቀም አላየንም ። የቦረናን ገበሬ የኦሮምያ ክልል መሬት ያንተ ብቻ ነው ስላልከው መሬቱ አይሰፋለትም፤ ድሮም በሲዳሞ አውራጃ ስር ስለነበረ መሬቱ አልጠበበትም። አሁንም ያለው ድሮ የነበረው ነው። መሬት ከጠበበትም በህዝብ ብዛት የተነሳ እንጅ በሌላ ክልል ስር ስለሆነ አይደለም። የአንድ የኦሮሞ አርሶአደር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብት ግለሰቡን በሸዋ ክፍለ ሃገር ስር አዋቅሮም ማክበር ይቻላል፤ በድሮዎቹ አወቃቀሮች የነበረው ዋናው ችግር የጋራ መሬት ባለቤትነት ሳይሆን የመብቶች ያለመከበር ችግር ነው። የመሬት ባለቤትነት ችግር ነበር ከተባለም ችግሩ የግል መሬት ችግር እንጅ የጋራ መሬት ችግር አልነበረም። የግል መሬት ችግር ደግሞ ከመንግስት የተበላሸ ፖሊሲ ጋር የሚያያዝ እንጅ ከጋራ መሬት ባለቤትነት ጋር የሚያያዝ አይደለም። ግለሰቦች በቀጥታ የሚጠቀሙት በግል መሬት እንጅ በጋራ መሬት አይደለም፤ የጋራ መሬት ህዝብ በድምር የሚጠቀምበት ሲሆን የግል መሬት ደግሞ አንድ ግለሰብ ብቻ የሚጠቀምበት ነው። “የአማራ ክልል መሬት የአማራ ብቻ ነው” ስለተባለ፣ ግለሰቦች እንደፈለጉ ያገኙታል ማለት አይደለም። አንድ ግለሰብ ከዚህ መሬት ውስጥ ተቆርሶ የሚሰጠው የተወሰነ ብቻ ነው። የተወሰነ መሬት የተሰጣቸውም ያልተሰጣቸውም ዜጎች ሲሰባሰቡ ነው ክልል ወይም አገር እየተባለ የሚሄደው፤ በግለሰብ ደረጃ ከታዬ የመሬት መብት ጥያቄ ተመለሰ የሚባለው መሬትን በፍትሃዊ መንገድ ማከፋፈል እንጅ የክልሉ ህዝብ የራሱ መሬት ተሰጠው እያሉ በመፎከር አይደለም።

ብሄርን ከክልል መሬት ጋር ማያያዙ ተዘዋውሮ በነጻነት የመስራት መብትንም የሚጋፋ ነው። አንድ አርሶአደር ኦሮምያ አካባቢ መኖር ቢሰለቸውና ወደ አማራ ክልለ ሄዶ አንዷን ቆንጆ አግብቶ ጎጆ ለመቀለስ ቢያምረው “ የአማራ መሬት የአማራው እንጅ የኦሮሞው አይደለም ” ተብሎ ይታገዳል፤ በአገሩ በነጻ ተዘዋውሮ ሰርቶና ተዝናንቶ የመኖር ነጻነቱ ተገደበ ማለት ነው። በመብት ማስከበር ስም ዋናውን መብቱን ገደብክበት ማለት ነው። ለሲዳማ ገበሬስ ደስ የሚለው ሳይሸማቀቅ በየተኛውም የአገሪቱ ቦታ ተዘዋውሮ እርሻም ይሁን ሌሎች ስራዎችን ቢሰራ ነው። በ21ኛው ክ/ዘመን የአለም ህዝብ በመሬት መኖር አልበቃው ብሎ ባህርና ህዋ ሲያስስ እየዋለ፣ የአገራችንን ዜጋ በክልል አጥሮ ማስቀመጥ የመብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው።

እኔ ሆላንድ ውስጥ መብቴ ተከብሮልኝ እኖራለሁ። ሌሎች ኢትዮጵያዊ ጓደኞቼም እንዲሁ፤ ከእነዚህ መካከል አማራዎች፣ ኦሮሞዎች ፣ ሲዳማዎች ወዘተ አሉ። ሆኖም የአማራ ልጆች ሆላንድ ውስጥ “ የአማራ ክልል” የሚባል መብት ተከልሎ ካልተሰጠን መብታችን ተከብሯል ብለን ልንል አንችልም ብለው አንድም ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ አላየሁም፤ ኦሮሞዎችም፣ ትግሬዎችም፣ አፋሮችም እንዲህ አይነት ጥያቄ ሲያቀርቡ አልሰማሁም። ጥያቄውን ቢያቀርቡና መሬት ተከልሎ ቢሰጣቸው ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት መብታቸው ስለሚገደብ በቅድሚያ የሚጎዱት እነሱ እንጅ ሌላው ህዝብ ሊሆን አይችልም። እነሱም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የመሄድ መብት የላችሁም፣ ባላችሁበት ብቻ ነው መኖር የምትችሉት ቢባሉ የመጀመሪያ ተቃውሞ የሚያሰሙት ራሳቸው ይሆናል። ታዲያ እኛ ሆላንድ ውስጥ እንደ ፌንጣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየዘለልን መኖር ሲፈቀድልን፣ ለምን አገር ቤት ያለው ወገናችን በተሰጠው አጥር ታጥሮ ይቀመጥ? ሆላንድ ውስጥ ሰው በተሰጠው አጥር ብቻ እንዲኖር ሲገደድ የመብት ጥሰት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጠር የመብት መከበር የሚሆነው በምን አመክንዮ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄሮች መብት ተከብሯል ለማለት ሰው ተሸንሽኖ በተሰጠው መሬት ውስጥ ተከልሎ መኖሩን እንደ ማሳያ ማቅረቡ ስለመብት አለማወቃችንን ማሳያ ነው። እውነት ለመናገር ለአንድ የወላይታ ገበሬ የደቡብ ክልል መሬት ያንተ ነው ከሚባልና መላው የኢትዮጵያ መሬት ያንተ ነው ከሚባል የትኛው የተሻለ እርካታ እንደሚሰጠው ለመገመት ፊደል መቁጠር አያስፈልግም።

ጽሁፌን የማጠቃልለው ስነሳ ባነሳሁት ሃሳብ ነው። ክልልን ከአገር በላይ አድርጎ እንዲያይ የተሰበከው ወጣት፣ “አንድ ስንዝር መሬት ለሌላ ክልል ተላልፎ እንዲሰጥ አልፈግልም” ብሎ ቢከራከር ሊፈረድበት አይገባም። አንድ የአማራ ወጣት “ወልቃይት የአማራ እንጅ የትግራይ አይደለም” ብሎ ቢከራከር፣ የትግራይም ወጣት በተመሳሳይ መንገድ ሙግት ውስጥ ቢገባ አይፈረድም። ሁለቱም መሬቱ የኢትዮጵያ መሬት እንደሆነ አልተነገራቸውም፤ ለትግሬው ወጣት የተነገረው የወልቃይት መሬት የትግራይ እንጅ የኢትዮጵያ መሬት እንዳልሆነ ነው፤ የአማራው ወጣትም የተነገረው በተመሳሳይ መንገድ ነው፤ በትግራይ መሬት ደግሞ አማራው እንደልቡ እንዲሰራ አይፈቀድለትም። ታዲያ ለክልሉ መሬት ቢሟገት ምን ይገርማል? ስልጣኑን የያዙት ሰዎች ከዘረኝነት አስተሳሰብ ወጥተው ኢትዮጵያዊነት ቢያቀነቅኑ ኖሮ፣ ትውልዱም በኢትዮጵያዊነት ስም ተቀርጾ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ብሄርን ማዕከል ያደረገ የድንበር ግጭት ባልተፈጠረ ነበር። አሁን ባለው እውነታ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማምጣት እጅግ ከባድ ነው። ለጊዜው ራሳችንን ልናታልል እንችላለን፣ መጨረሻችን ግን ላያምር ይችላል። ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? ፈርነጆች Back to the basics እንደሚሉት ወደ መሰረታዊው ነገር መመለስ ነው፤ ዜጎች ለኑሮ በሚመቻቸው መንገድ አስተዳደራዊ መዋቅሮችን እንዲዘረጉ መፍቀድ፣ ፍትሃዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲሰፍን ማድረግ ነው።

አገር በመልካም ንግግር ሊረጋ ይችላል፤ አንድነቱ የሚጸናው ግን ከንግግር ባለፈ ተጨባጭ እርምጃዎች ሲወሰዱ ብቻ ነው። ከእነዚህ እርምጃዎች አንዱ የከሸፈውን ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ተስማሚ በሆኑ ሌሎች መስፈርቶች እንደገና ማዋቀር ነው። አማራ እና አሮሞው፣ አማራና ሶማሊው፣ አማራና ትግሬው፣ አማራ እና ጋምቤላው ወዘተ በኢትዮጵያ ምድር እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ ሰርቶና ተዝናንቶ እንዲኖር የሚከልለውን አጥር መንቀል ነው። በአገራችን ውስጥ የድንበር አጥር እንዲኖር መፍቀድ ማለት በነጻነት ተንቀሳቅሰን የመኖር መብታችንን አሳልፈን መስጠት ማለት ነው። አንበሳን እንደልቡ ከሚፈነጭበት ጫካ አውጥተህ በጉሮኖ ( zoo) ውስጥ ስላኖርከው መብቱን አከበርክለት ማለት አይደለም፤ ለአንበሳውስ የሚሻለው አዲሱ የክልል አጥር ሳይሆን እንደፈለገ የሚቦርቅበት መላው ጫካ ነው፤ ለእኛም የሚሻለን መላው አገሩ የእኛ እንደሆነ ስናስብ እንጅ አስተሳሰባችን በክልል ደረጃ ሲታጠር አይደለም። በአንድ አገር ውስጥ ያለው መሬት የሁሉም ህዝብ ሃብት መሆኑን ሳናውጅ ስለአንድ አገርና ስለ አንድ ህዝብ መነጋገር አንችልም። እንደ አንድ አገር ተጠናክረን እንድንወጣ ከተፈለገ ሌሎች ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ ቢያንስ “የአገራችን መሬት የሁላችንም ሃብት ነው” በሚለው ላይ የጋራ መግባባት ሊኖረን ይገባል። ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ብሄርን ማዕከል አድርጎ የተዋቀረውን የክልል ፌደራሊዝም አፍርሶ በሌሎች መስፈርቶች አዲስ ፌደራሊዝም መመስረት ሲቻል ነው።

(ይህ ጽሁፍ በትንሳኤ ሬዲዮ ተላልፏል፣ ጤነኛ የሃሳብ ሙግት እናድርግበት)

“Wolqayit Factor! & Eritrean-Factor!” (Ermias Legesse Wakjira)

“Wolqayit Factor! & Eritrean-Factor!”

ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት ህዉሃት በብሔር ብሔረሰቦች ዲሞክራሲያዊ መብቶች እየማለና እየተገዛተ ዝህቡን ለማታለል ብሎም ለመለያየት ቢሞክርም ያሰበውን አላማ ሊያሳካ አልቻለም። ለሁሉም ግልጽ እንደሆነው በአገራችን የሰላም እጦት ከጫፍ እስከ ጫፍ እየታየ ነው። የስርአት ለውጥና የነፃነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ የትግል ስልቶች ተቀርፀው ወደ ትግባር ተቀይረዋል። እየተደረጉ ያሉት ትግሎች አስተሳስረን ስንመረምር አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ወደ መቃብር የወረደበት ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህ በኋላ ህዉሃት መንግስታዊ የበላይነትን ባገኘበት ሁኔታ የምርጫ ፖለቲካ አጀንዳው ተዘግቷል። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዳሉት በምርጫ ፖለቲካ መቃብር ላይ ጥቁር አበባ ተቀምጦበታል። መቃብር ፈንቅሎ ትንሳኤ ይፈፀም ይሆን ለወደፊት የምናየው ይሆናል።

ተስፋ አለኝ።

ህዉሃት መራሹ ድርጅት በየጊዜው የሚሰጠው ድርጅታዊ መግለጫና እሱን ተከትሎ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተስፋ የሚያስቆርጠው የአገሬው ህዝብና የአለም መንግስታትን ብቻ አይደለም። የስርአቱ መስራችና ባለቤት የነበሩ እንዲሁም በተለያየ ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ ስልጣን ላይ የነበሩትን ጭምር ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችን ያጨናነቁት ጄኔራል አበበ እና ጄኔራል ፃድቃን በስርአቱ ምላሽ ላይ ምን ያህል ተስፋ እንደ ቆረጡ መገመት ይቻላል። “የስርአት ችግር ስላለ፣ ኢህአዴግ የተቀባይነት ችግር ስላጋጠመው የስርአት ለውጥ መምጣት አለብት!” ብሎ የተናገረው አንደበታቸውና የከተበው ብዕራቸው ዞር ብለው ሲመለከቱ ማፈራቸው የሚቀር አይደለም። እነ ፃድቃን “ሀገሪቷ የመበታተን አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል” ቢሉም የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸውና የስልጣኑ ባለቤቶች “ህገ-መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት በጽኑ መሰረት ላይ ተገንብቷል” የሚል ዲስኩር ያሰማሉ።

እነ ጆቤ “ህዝቡ በተስፋ እጦት ውስጥ ገብቷል” ብለው ሲፅፉ በተቃራኒው እነ አባይ ፀሀዬ “የአገራችን ህዝቦች በኢትዮጵያ የፈነጠቀውን የልማትና የዲሞክራሲ ጮራ ተማምነው በለመለመ ተስፋ ወደፊት ይመለከታሉ” የሚል ዘመን ተሻጋሪ ማብራሪያ ይሰጣሉ። እነ ፃድቃን በቀኝ ሆነው የመቶ ፐርሰንት ምርጫ በህዝብ ማላገጥ ነው” በማለት ብዕራቸውን ሲያነሱ በግራ የተሰለፉት እነ በረከት “ኢህአዴግ ስራ በምርጫ ካርድ የተሰጠውን ሃላፊነት አደራ ለመወጣት ቆርጦ ተነስቷል” ይሉናሉ። አራንባና ቆቦ!!

እዚህ ላይ በሁለቱ የቀድሞ የጦር አዛዦችና የህዉሃት መራሹ መንግስት ሃይሎች መካከል በሁሉም ጉዳይ ተቃርኖ ውስጥ እንደገቡ የሚያስብ ካለ በደንብ ተሸውዷል። ሁለቱም ሃይሎች የህዉሃትን ብሎም የትግራይ ህዝብ ጥቅም ይነካል ብለው በገመቱት ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው። ከዚህ አንፃር በቅድሚያ ሊነሳ የሚችለው በቀድሞ በትግራይ አስተዳደር ስር ያልነበሩና ዛሬ የተካለሉት ወልቃይትን የመሳሰሉ ቦታዎች ናቸው። የጦር አዛዦቹም ሆነ የህዉሃት ታጋይ ባለስልጣናት መጀመሪያ ሰሞን የወልቃይትና ተመሳሳይ ቦታዎች ፈጽሞ አንዳይነሱ፤ የሚዲያ ትኩረት እንዳያገኙ አድርገው ነበር። በጽሑፎቻቸውም ሆነ በመግለጫዎቻቸው በየትኛውም ቦታ ከመግለጥ ተቆጥበው ነበር። የቅማንትን ጉዳይ አጉልቶ የገለጠው “ጆቤ” ወልቃይት ላይ ሲደርስ የብዕሩ ቀለም በሚያስፎግር ሁኔታ አልቆበት ነበር። በኦሮሚያ ጥያቄዎች ላይ በምናቡ ከፈጠራቸው የኦሮሞ ልጆች ጋር ማውራቱን ሊነግረን የፈለገው ጄነራል አበበ ጠገዴና ጠለምት ፀለምት(ጨለማ) ሆነውበት ግድግዳ ተስታኮና ተንፏቆ ሲያልፋቸው ተመልክተናል።

ሁኔታዎች እየገፋ ሲመጡና የትግሉ ማዕከሉ “ወልቃይት” መሆኑ ሲረጋገጥ እየተንፏቀቁም ቢሆን የወልቃይትን አጀንዳ ማንሳት ጀመሩ። ለምን ከዚህ በፊት ልታነሡት አልሞከራችሁም ሲባሉ “ይሔ ትልቅ ጉዳይ አይደለም:” የሚል ምላሽ ሰጡ። ቁምነገሩ እዚህ ጋር ነው። ለእነ ጄነራል ፃድቃን የቅማንት ጉዳይ ትልቅ እንደሆነ አድርገው ሊያገኑት ሲሞክሩ የማያቋርጥ የህዝብ ደም እየፈሰሰበት ያለውን ወልቃይት ንቀው እንደተውት ሊያሳዩ ሞከሩ። እነዚህ ሰዎች ይህን ምላሽ ሲሠጡ ወልቃይት “የትግል ማዕከል” እና “የኢፍትሃዊነት ማሳያ” መሆኑን ጠፍቷቸው አይደለም። ልክ አቶ መለስ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት ካድሬዎች “ለምን ባድመን ለመሰለ ቁራሽ መሬት የ10ሺዎች ደም ይፈሳል?” ብለን ሥንጠይቀው እጁን እየጠበጠበ “ባድመ የትግላችን ማዕከል የሆነችው የኢፍትሐዊነት ማሳያ ስለሆነች ነው” በማለት የንዴት ምላሽ ሰጥቷል። በመሆኑም ባድመ የኤርትራ መንግስት በሃይል ስለወሰዳት መጀመሪያ ወደቀድሞው ቦታዋ ትመለስና ህጋዊ ውሳኔ ይሰጥባት እንደተባለ ሁሉ የወልቃይትም ተመሳሳይ ነው። ወልቃይት “ኢፍትሃዊነት ማሳያ” ስለሆነች መጀመሪያ ወደቀድሞው ታሪካዊ ባለቤቷ ትመለስና ሌሎች የህዝብ ጥያቄዎች ቂም በቀል በማይፈጥሩና የጋራ ድል (Win_Win) በሚያረጋግጡ መልኩ ይፈቱ ማለት የአባት ነው። ይገባልም። ይህ ካልሆነ ግን ምንአልባት ከባድመው ባልተናነሰ በ100ሺዎች የሚጠጋ ህይወት የሚወድቅበትና ደም መቃባቱ የሚያባራ ሊሆን ይችላል።

በመቶ ሺዎች ሊገደሉ ይችላሉ የሚለውም ተራ ማስፈራራት አይደለም። ህዉሃት በተለይም የአማራ ተወላጆች ላይ የቋጠረው የቂም ቋጠሮ ከዚህ በላይ ሊገድል እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አሰፋ አቢዩ በዛን ሰሞን በሰጠው መግለጫ “99 ፐርሰንት ንፁህ ናቸው፣እርምጃ የምንወስደው በተቀሩት ላይ ነው” በማለት ይፋ አድርጓል። አሁን ባለው የአማራ ክልል ንቅናቄ ከ5 ሚሊዮን የአማራ ተወላጆች በቀጥተኛ እየተሳተፉ እንደሆነ ዝቅተኛ ግምት ቢወሰድ እንኳን በኮሚሽነር አሰፋ ስሌት መሠረት ከ50 ሺህ በላይ ሠዎች እርምጃ ይወሰድባቸዋል። ህዝባዊ ማዕበሉ እየሰፋ ሲሄድ በአስቸኳይ የስርአት ለውጥ ካልመጣ እርምጃ የሚወሰድበት የአማራ ተወላጅ ሁለትና ሶስት እጥፍ ይሆናል። ለህዉሃት “የትግል ማዕከል” የሆኑትን ቦታዎች አሳልፎ መስጠት መቃብሩን በጥልቀት የመቆፈር ያህል ስለሚመለከተው በጅምላ ከመግደል የሚመለስ አይሆንም።

በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀጣጠለው ህዝባዊ ማዕበል ከህዉሃት ህልውና አንጻር በርካታ ዋልታዎች (Multi- Polar) ያሉት ቢሆንም፣ የዋልታዎቹ ምሰሶ ወልቃይት (Wolqayit Factor) ተደርጎ የሚወሰድ ነው። የኦሮሚያ፣ አማራ፣ጋምቤላ፣ ኮንሶ ፣ ጉራጌ የተነሱት እምቢተኝነቶች ትላልቅ ዋልታዎች ቢሆኑም ህዉሃት ልቦና ገዝቶ በህይወት መቆየት ከፈለገ ወደ ምሶሶነት ሳያድጉ በተራዘመ ሂደት ሊያዳፍናቸው ይችላል። ለምሳሌ ህዉሃት ኤርትራ ላይ የሚያስበው (Eritrian-Factor፡ ኤርትራ በጦርነት ማሸነፍና አስመራ ላይ አሻንጉሊት መንግስት መመስረት) ከተሳካና ህዉሃት ኢትዮጵያን መምራት ከተነሳው የኦሮሚያን ጥያቄ እስከ መጨረሻው ጫፍ ሊወስደው ይችላል። ይህም በኦሮሞ ጉዳይ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና አክቲቪስቶችን የመከፋፈል እድሉ ሰፊ መሆኑ አይቀርም። ህዉሃት እስከ ጫፍ የሚወስደውን ፍላጎት ለመቀበል አዳዲስ ሃይሎች (Emerging Powers) የሚፈልቁበት ሁኔታ ይፈጠራል። በመሆኑም ህዉሃት በሚቀደው ሀገር የማፍረስ ቦይ የሚፈሱ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ሰዎች ይኖራሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለቱ የህዉሃት የቀድሞ ጦር አዛዦች በተለይም ሌ/ጄነራል ፃድቃን ወልቃይትና ሌሎች “የኢፍትሐዊነት ማሳያ” ቦታዎችና “የትግል ማዕከሎች” በተመለከተ ያስቀመጡት ምላሽ ህዝባዊ እምቢተኝነቱን የበለጠ ነዳጅ የሚጨምር ነው። ጄነራል ፃድቃን መጀመሪያ አካባቢ ባቀረባቸው ጽሁፎች በብልጣብልጥነት ሊያልፈው ቢፈልግም ቦታዎች ይበልጥ “የትግሉ ማዕከሎች” መሆናቸውን በህዝባዊ ማዕበሉ ሲመለከት ከድርቅና በተሻገረ አይን አውጣነት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ እርስ በራስ የተምታታ ምላሽ ሰጠ። ይህ የጦር መኮንኑ ምላሽ የአማራ ህዝብ ትግልና መነቃቃት ከደረሰበት ደረጃ ጋር ፍፁም የማይመጥን ነው። የአሁኑ የአማራ ትግል የደረሰበት ደረጃ ፍልሚያው ተጧጡፎ አድማሱን በመስፋት ቅኝቱ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል። ከአስር አመት በፊት ሃሰን ዑመር አብደላ በመጣጥፋቸው እንደገለጡት ቅኝትና ምቱ ከተቀየረ እስክታውም መቀየር አለበት። በመሃመድ አህመድ የትዝታ ቅኝትና ምት ጥላሁን ገሠሠን “አንቺን ነው! ሰማሽ ወይ” የሚለው አይደነስም። በ “እምበር ተጋዳላይ” አጨፋፈር ስልት የይሁኔ “ሰከን በል” አይጨፈርም። እንደዚህ ከሆነ በአራዳ ቋንቋ ሽወዳ ይሆናል። አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ ደግሞ ውሽልሽል ምክንያት ሸውዶ ማለፍ የሚችልበት ወቅት ላይ አይደለንም። አለበለዚያም እውነት መድፈር ካልተቻለና የሚያስፈራ ከሆነ (ኮንስቲትወንሲያቸውን እንደሚያጡ ይገባኛል) ምላሽ አለመስጠት ይቻል ነበር። ፃድቃን ሊጠቀምበት የፈለገው “የሽወዳ ፖለቲካ” ህዝባዊ እምቢተኝነቱን አቀጣጥሎ መስዋዕትነቱን ከመጨመሩ ባሻገር በሌሎች ያቀረባቸው የመፍትሄ ሃሳቦችም ላይ በጥርጣሬ እንዲታይ ያደረገ ነው።

ለማንኛውም ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ “የትግሉ ማዕከል” በሆነው ወልቃይት ዙሪያ ለአዲስ አድማሱ ጋዜጣ የሰጠውን መግለጫ በመመልከት ፍርዱን እንስጥ። አዲስ አድማስ ጋዜጣ “በሰሜን ጎንደር አካባቢ ያለው ተቃውሞ በተለይ ከ “ወልቃይት አማራነት” ጋር የተያያዘ ነው። የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጉዳይ በምን አግባብ ነው መፈታት ያለበት?” ለሚለው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።

“እኔ የወልቃይት ጉዳይ ለአንዳንድ ፖለቲካዊ አላማዎች ሽፋን ነው ብዬ ነው የማምነው። እንዴት ነው የሚፈታው ላልከው እኔ የሚታየኝ ህገ- መንግስቱን መሠረት አድርጎ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ይሔ ትልቅ ጉዳይ መደረግ አልነበረበትም። ህዉሃትና ብአኤን ተመካክረው መፍታት የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረስ ነበረባቸው።…. በህጋዊ መንገድ ስንሄድም ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርጎ መፍታት ያስፈልጋል ነገር ግን ክልሎች በሚወሰኑበት ወቅት ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪ አካል ውስጥ ነበርኩ። በወቅቱ ቋንቋና የህዝብ አሰፋፈርን መሰረት አድርገን እንወሰን በሚል ነው የወሰነው። በዚህ መሰረት ደግሞ የተወሰነው ተወስኗል።”

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቀጥሎ የጠየቀው “በወቅቱ ወልቃይት እንዴት ነው ወደ ትግራይ የተላከው?” በማለት ነበር። ሌ/ጄነራሉ እንዲህ በማለት አስገራሚ፣ አሳዛኝና እርስ በራሱ የሚደባደብ ምላሽ ሰጠ።

“አሁን እየጠየከኝ ያለኸው መረጃ ነው። ይሄን መረጃ አሁን አላስታውሰውም። እንደዚህ ሆኖ ነበር ብዬ ለማለት አልችልም። የተጠቀምንበት አቅጣጫ ግን የፌደራሊዝሙን መነሻ ነው። የህዝቦች ቋንቋና ባህልን መነሻ አድርገን ነው የከለከልነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ እዚያ አካባቢ ያለው አብዛኛው ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ነው። ባህሉ የትግራይ ነው። በትግራይ ውስጥ ሊካተት የሚችል ህዝብ ነው። የሆነውም በዚህ አግባብ ነው።”

በመሆኑም እነዚህ የህዉሃት ጦር ጄነራሎች “ህዉሃት አደጋ ላይ መውደቁን ሲያዩ ሊታደጉት መጡ” የሚለውን አባባል ለጊዜው እንተወውና የጎደላቸውን ነገር በጨዋ ቋንቋ እንንገራቸው።

ከጄኔራል ፃድቃን አስተያየት ሳልወጣ አድናቆቴን መግለጽ የምፈልግበት አንድ አረፍተ ነገር አለ። ጄኔራሉ በሌሎች የህዉሃት ታጋዮች ባልተለመደ መልኩ አሁን ያለውን ሁኔታ ሲገመግሙ “የትግራይ ህዝብ በተለይም በከተሞች አካባቢ በሌሎች ማህበረሰቦች የመገለል ሁኔታ አጋጥሞታል። መተማመኛውንም የስልጣን የበላይነት አስጠብቆ ማቆየትና በመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ተከልሎ መኖር” እንደሆነ ገልጧል። ይሄንን ግምገማ ሙሉ በሙሉ የምቀበለው ነው። ለረጅም ጊዜያቶች ይሄ ችግር እየመጣ እንደሆነ ደጋግመን ስንለፈልፍ በህዉሃት ጎራ ያሉ ሰዎች “ዘረኞች” የሚል ታፔላ ተለጥፎልን ነበር። ዛሬ የጦር መኮንኑ በግላጭ ሲያወጣው በህዉሃት መንደር የተፈጠረ ብዙም መንጫጫት አይታይም። ታዲያ! ጄኔራል ፃድቃን በዚህ ጉዳይ ላይ ይሄን ያህል ርቀት መጓዝ ከቻለ ከጥያቄው ጋር አብረው ለሚነሱት ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ቢሰጥበት እኛንም ከስድብና ውርጅብኝ ያድነናል። ጥያቄው የትግራይ ህዝብ በተለይ በከተሞች ውስጥ በሌላው ማህበረሰብ እየተገለለ መሄዱ እውነት ሆኖ ሲያበቃ፤ የመገለሉ መንስ ኤና መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? መገለሉስ ከመቼ ጀምሮ የተፈጠረ ነው? ተጠያቂው ማነው?…. ወዘተ የሚሉ ናቸው። ይህንን ቁልፍ ጉዳይ መመለስ ከተቻለ ወደ ቁልፍ መፍትሄው የምንሄድበት መንገድ አልጋ በአልጋ ይሆናል።

የትግራይ ኤሊቶች፣ የህዉሃት የቀድሞ የጦር ጄኔራሎችም ሆነ የቀድሞ ታጋይ ባላስልጣናት ከህዉሃት በፍጥነት ተፋተው ለአዲስ የስርአት ለውጥ ዝግጁ የማይሆኑባቸው ሌሎች ተጨማሪ መሰረታዊ ምክንያቶች አሏቸው። ከዚህ ውስጥ የቅድሚያ መስመር የምትይዘው ኤርትራ ናት (Eriteria-Factor)። ህዉሃት ከኢርትራ ጋር የገባበት ጦርነት ፍፃሜ የረጅም ጊዜ የመጠባበቂያ ህልሙን ያጨለመ ነው።

ለሁሉም ግልጽ እንደሆነው ከጦርነቱ በፊት ከኤርትራ መንግስት ጋር ለአመታት የተካሄደው ድርድርም ሆነ የጦርነት ውሳኔ የተወሰነው በህውሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ነው። ወደ ጦርነት ከተገባም በኋላ የመሪነቱን ሚና የጨበጡት ህዉሃቶች ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት የአገሪቱ ካዝና በተራገፈና ሙጥጥ ባለ ሰዓት መንግስት ከሶስት ቢሊዮን ብር ያላነሰ የተበደረው ከህዉሃት የኢኮኖሚ ኢምፓወ ከሆነው ኤፈርት (ትእምት) ነበር። ለጦርነቱ የሚሆነውን የጦር መሳሪያ (ታንክ፣ ሮኬት፣ ሚሳየል፣ የውጊያ አውሮፕላኖች…) በየአህጉራቱ የተሽከረከሩ የሚገዙት የህዉሃት አመራሮችና የጦር አዛዦች ናቸው።

(በነገራችን ላይ በአውሮፕላን ግዢ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ከነበራቸው የጦር አዛዦች ግንባር ቀደሙን የሚይዘው የቀድሞ አየር ሃይል አዛዥ የነበረው ሜ/ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት ነው። አበበ የክፍፍሉ መጀመሪያ ወቅት እንቡር እንቡር ቢልም የአንጃዎቹ መጨረሻ ኩምሽሽ አድርጎታል። “አይተነው ጊዜ ወደሚያደላው” አይነት ባህሪ ያለው አበበ ገልብጦ የመለስን ቡድን ይቅርታ ቢጠይቅም የመለስን የቃሪያ ጥፊ ከማግኘት አልታቀበም። ከአዛዥነቱ በንፋስ ፍጥነት ተባረረ። ከዛ በኋላ ጆቦ በሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከኪሱ በማውጣት አሜሪካን ሀገር ተማረ። በትምህርቱም “የአሰብ ኢትዮጵያዊነት” ተገለጠለት። መገለጡ ቀልብ ይስባልና በኢትዮጵያ አየር ሃይል ላይ በተነው። ጆቤ! ዛሬ በወር 150ሺህ ብር የሚከራይ ቪላ አለው። ያውም በአዱገነት እምብርት! ለ100 አመት ይዞ ቢቆይና ከደሞዙ ሰባራ ሳንቲም ባያወጣ አሁን ያለውን ሀብት ሩብ አይኖረውም። እርግጥ ከርቀት እንደሰማነው ባለቤቱ ብቸኛዋ ሴት ጄኔራል ሆናለች።)

እዚህ ላይ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ውጤት ለህዉሃት የበላይነት መምጣትና የትግራይ ተጠቃሚነት ዋስትና የፈጠረው አደጋ ለህዉሃት መሰንጠቅ መሰረታዊ ምክንያት ቢሆንም ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች አሉት። እነዚህ አደጋዎች ከህዉሃት አፈጣጠር፣ የዘረጋው ስርአት ባህሪና ውስጠ- ድርጅት ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ህውሃት የበላይነቱን ያረጋገጠባት ኢትዮጵያ ካልቀጠለችና የአገር መበተን ካጋጠመ “የትግራይ ሪፐብሊክ” ነፃ ሀገር ፈጥሮ መኖር እንደ መጨረሻ ግብ ያስቀመጠ ቢሆንም ከኤርትራ ጋር የገባበት ቁርሾና ደም መፋሰስ ይህን ፍላጎቱን ከሞላ ጎደል ዝግ አድርጎታል። Eriteria-Factor የተባለው አንዱ ገፅታ ይሄ ነው። የጎንደር፣ አፋር፣ ወሎ ህዝብ ከታች ኤርትራ ከላይ ሆነው ትግራይን ሳንድዊች የሚያደርጉበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ከዚህ በኋላ “የትግራይ ሪፐብሊክ” ከህልም የዘለለ አይሆንም። ትግራይን ገንጥለን በሰላም እንኖራለን የሚባል ህልም ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣……ወዘተ ወደ ትግራይ የተከለሉ ሰአትና የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተነሳ ሰአት ወደ መቃብር ወርዷል።

የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት አጨራረስ በአንድ በኩል ነፃ ሀገር ለመመስረት ህልም የነበረችውን የህዉሃት አመራሮች ወሽመጥ የቆረጠ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነቱን አጥብቆ ለሚፈልገው የትግራይ ህዝብ ትልቅ ብስራት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። በአጭሩ ኢትዮጵያን ወዳድ ለሆነው የትግራይ ህዝብ የጦርነቱ አጨራረስ በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ የሚፈጠር ጥሩ አጋጣሚ ነው። Blessing in disguise!!

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አጨራረስ ህዉሃትን ለሁለት ሰንጥቋል የሚባልበት መሰረታዊ ምክንያት ይሄ ነው። የስዬ አብርሃ ቡድን የኢትዮጵያን ህዝብ ሀብትና ደም መከታ አድርጎ ኤርትራ በመደምሰስ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት ሲያስብ ሌሎች አላማዎችን ለማሳካትም ጭምር ነበር። ህዳጣኑ ህዉሃት ከትግራይ ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ መግዛት ካቃተውና ህዝባዊ ማዕበሉ ካናወጠው ያለ ኤርትራ ስጋት “ነፃ የትግራይ ሪፐብሊክ” መመስረት ይችላል። የስዬ ቡድን ኤርትራ ላይ ለራሱ ተጠሪ የሆነ አሻንጉሊት መንግስት መመስረት አለመቻሉ በክፉ ጊዜ መጠጊያ የምትሆነውን “ሪፐብሊክ ትግራይ” የመመስረት ራዕይ ተጨናገፈበት። በተለይ በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹን በመገብሩ ቁጭት ላይ የወደቀ መሆኑና ከዚህ በኋላ ጋሻነቱ ባከተመበት ሁኔታ ከኤርትራ ጋር ጦርነት መግጠም ማለት የህዉሃት ፍፃሜ መሆኑ አይቀርም።

በሌላ በኩል ጓድ መለስ በስልጣን ለመቆየት ካለው ጥማት በመነሳት ጦርነቱ ሊገፋበት አለመቻሉ እዛው ሳለ የትግራይን ነፃ መንግስት ህልም ባጭሩ የቀጨ ሆኗል። ይህ በመሆኑ ምክንያት በህዉሃት/ኤህአዴግ ህገ-መንግስት ውስጥ የሰፈረው አንቀጽ 39 ከህዉሃትና ትግራይ ህዝብ አኳያ ከወረቀት አንበሳነት የዘለለ አይሆንም። የህዉሃት አፈጣጠር መነሻ የሆነው “የትግራይ ነፃ ሪፐብሊክ” መመስረት እውን ሊሆን የሚችለው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ሲሟሉ ብቻ ነው። አንደኛው ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት….. የመሳሰሉ መሬቶችን ለባለቤታቸው ሲመልሱ ይሆናል።ሁለተኛው ኤርትራ ላይ (Eriteria-Factor) ዳግም ጦርነት በመክፈትና ኤርትራን ወደ ዳግም ሱማሊያ መውሰድ፤ ከተቻለም ለህዉሃት ተጠሪ የሆነ አሻንጉሊት መንግስት በመመስረት በተራዘመ ጊዜ በኮንፌደሬሽን መዋሃድ። የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሌሎች ቀድሞ በትግራይ ክልል ያልነበሩ ቦታዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ይመለሳል የሚለው ጥያቄ “በህዉሃት መቃብር” ላይ ብቻ የሚፈፀም ነው። ለዚህም ነው ከየትኛውም የኢትዮጵያ ቦታዎች በበለጠ ሁኔታ እነዚህ አካባቢዎች “የትግሉ ማዕከል” ናቸው የተባለበት ምክንያት። ኤርትራን በጦር ገጥሞ ለህዉሃት ተገዢ የሆነ አሻንጉሊት መንግስት በአስመራ እናቋቁማለን የሚለውም ፍላጎት ያለቀና የደቀቀ ተደርጎ ባይወሰድም ወደ ዜሮ የቀረበ እድል (Probability) ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

እርግጥ ሌሎች ህዉሃትን ለሁለት የሰነጠቁ እንጭፍጫፊ ምክንያቶች እዚህ ላይ ሊጨመሩ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነው። የህዉሃት የፍጥረቱ የመጨረሻ ግብ ከመኮላሸቱ ጎ ለጎን የዘረጋው ስርአት ባህሪና የውስጠ- ድርጅቱ ሁኔታ ለመሰነጣጠቁ ምክንያት ነው። ህውሃት የዘረጋው ስርአት የፓርቲውን የበላይነትና የትግራይን የተለየ ተጠቃሚነት ዝርፊያ (ሙስና) አንዱ መለያ ባህሪው ነው። መንግስት እንደመሆኑ መጠን ወረራና ዝርፊያው “መንግስታዊ” መሆኑ አይቀርም። “መንግስታዊ ሌብነት” “መንግስታዊ ዝርፊያ” “መንግስታዊ ሙስና” “መንግስታዊ ውንብድና!”…. በመሆኑም የህዉሃት አንዱ መሰረታዊ መለያ ባህሪ በአዋጅ፣ በህግ፣ በመመሪያ የሚፈፅም የቡድን ዝርፊያ (“መንግስታዊ ሙስና”) ነው። ህዉሃት ገና ከጠዋቱ ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የመንግስትና ድርጅታዊ የስልጣን ቦታዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለው በዚህ ምክንያት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ውጭ ጉዳይ፣ መከላከያ፣ ደህንነት፣ ፖሊስ፣ ሚዲያ፣ የድርጅት ቢሮ፣ የክልሎች ሞግዚት በመሆን አይናቸውን በጨው ያጠቡት ለዚህ ነው።

ይህም ሆኖ የህዉሃት ስርአት በትግራይ ህዝብና ልሂቃን ዘንድ ያለው አረዳድ ከሌላው አካባቢ ጋር ተመሳሳይ አይደለም። አሁን ባለው ነባራዊ እውነታ ከትግራይ ህዝብ የወጡት ህዉሓቶች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፈላጭ ቆራጭ በሆኑበት፤ ገዳዩ አሳሪው ገራፊውና መርማሪው እነሱ በሆኑበት፤ የመንግስት ስልጣንን በመጠቀም ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም በገነቡበት፤ በትግራይ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅና ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እልፍ አእላፍ ፋብሪካና የኢኮኖሚ አውታሮች በተገነቡበት፤ በጠብታ ኢኮኖሚ መልኩ በትግራይ ክልል ማህበራዊ ፍትህ ማምጫ ተቋማት በተገነቡበት….. ወዘተ በፍጥነት ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ሊቀላቀላቸው አይችልም። ራሳችንን ማሞኘት ካልፈለግን በስተቀር የትግራይ ህዝብ በህዉሃት አገዛዝና አፈና ተማሮ ሊሆን ይችላል እንጂ “አዲስ ስርአት” ለመቀበል ዝግጁነቱ አይታይም። የህዉሃት አገዛዝ በፓርቲ መዋቅሩ አማካኝነት የሚፈጥረው ጭቆና፣ የዘመድ አዝማድ አድሎአዊ አሰራር፣ ኋላቀርነት፣ “አህያ ቢራገጥ” የሚመስል አይነት ቂም በቀል፣ እንዲሁም አሰልቺ ስብሰባዎች እና መዋጮ….. ወዘተ የትግራይን ህዝብ ሊያስመረምረው ይችል ይሆናል እንጂ ለስር-ነቀል ለውጥ አልተዘጋጀም። ግፋ ቢል ከአጭር ጊዜ አኳያ “ላም እሳት ወለደች” ከሚለው ብሂል የሚርቅ አይደለም። ይህ የብዙሃኑ የትግራይ ተወላጅ ፍላጎት አድርገን ልንወስደው የምንችል ይመስለኛል።
…//…

( ማስታወሻ: ይሄ መጣጥፍ የተዘጋጀው የዛሬ ሁለት አመት ጥቅምት 2016 ነበር። ያቀረብኩት ደግሞ በሂውስተን ቴክሳስ ለህዝብ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ነው። ከአሁኑ ወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ጋር ይሄዳል ብዬ ስላሰብኩ በፌስቡኬ ላይ ለጥፌዋለሁ። እንደ አባዱላ ” ፌስቡክ አልመለከትም” ብሎ ዶክተር አቢይ እንዳያሳፍረን እንጂ እድል አግኝቶ ቢመለከተው አይጐዳውም።ከዚህ በተጨማሪ ይህ ፅሁፍ ከራሴ ውጭ የማንንም አቋም አያንፀባርቅም።)

”ቢቢሲ ሃርድ ቶክ” ቆይታ ህወሓት እና “የብሄራዊ ጥቅም” (ነአምን ዘለቀ)

”ቢቢሲ ሃርድ ቶክ” ቆይታ ህወሓት እና “የብሄራዊ ጥቅም”

በቅድሚያ ምስጋና፦
ባለፈው ሳምንት በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆነው የቢቢሲ ሃርድ ቶክ/BBC Hardtalk ጋር ቆይታ ማድረጌ ይታወቃል። የፕሮግራሙ ይዘት ጠንከር ያሉ ሙግቶችን ተሞርኩዞ ምላሽ የሚሰጥበት በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ የሚደፈር አለመሆኑም ይተወቃል። ወደ ኋላ ሔዶ ለማስታወስ ያህል የፕሮግራሙ አዘጋጆች ከወያኔ ቁንጮ ከነበረው ሟቹ መለስ ዜናዊና የቅንጅት ሊ/መንበር ከነበሩት ኢንጂነር ሐይሉ ሻወል ጋር እንደዚህ አይነት ፖለቲካዊ ሙግት ያደረገው የዛሬ 12 አመት በምርጫ 97 ማግስት ነበር። ከዛ ወዲህ በአገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚዲያው ቀርቦ ሙግት የገጠመው ኢትዮጵያዊ አላስታወስም።

ይህን በመመልከት ይመስላል የንቅናቄያችን አመራሮች አባላትና ደጋፊዎች፤ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶት ውስጥ ያላችሁ አመራሮችና አባላት፤ የስርአት ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያንና በርካታ ምሁራ ስሜታችሁን ገልጻችሁልኛል። በአካል፣ በስልክ በማህበራዊ ድረ-ገጽና አስተያየቶች ደርሰውኛል። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትኩረት የሚሰጡ ድረ-ገጾች እንዲሁም እንደ ኢሳት ያሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት “የቢቢሲ ሃርድ ቶክ” ፕሮግራሙን ተመስርተው ውይይትም በማድርግ በተለያየ ምልከታዎችን እንዳይ ስላደረጋችሁኝ በድጋሚ ለድረ-ገጾቹም ሆነ ለሚዲያ ተቋማቱ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። ለሰጣችሁኝ አበረታች ግብረ-መልስ ላቅ ያለ ምስጋናዬን ከወዲሁ ማቅረብ እወዳለሁ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አክብሮታችሁን የላካችሁልኝ የንቅናቄያችን አባላትም ሆነ የተቀራችሁ ኢትዮጵያውያን አንድ ነገር አስምሬ ልነግራችሁ የምፈልገው ጉዳይ አለኝ። ኣኔ ብዙሃን ወደማይደፍሩት የቢቢሲ ሞጋች ፕሮግራም ላይ ለመቅረብ ፍቃደኛ የሆንኩት ዋነኛ ምክንያት በመኖሩ ነው። ይኸውም አመራር የሆንኩት አርበኞች ግንቦት ሰባት ነድፎ የሚታገልባቸው የማታገያ ነጥቦች መዳረሻ ግልጽ ስለሆኑ ነው። ለሁሉም ግልጽ ኣንደሆነው ንቅናቄያችን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ አንድነት፣ እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅም ለድርድር የሚያቀርብ አይደለም።
ንቅናቄያችን የኢትዮጵያ መኖር ከማንኛውም ጉዳይ በላይ ወሳኝ መሆኑን በማመን የንቅናቄያችን ታጋዮች የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፣እየከፈሉም ይገኛሉ። ንቅናቄያችን አገር ለማዳን በሚደረገው የሞት ሽረት ትግል ከሌሎች የነጻነትና የዴሞክራሲ ሐይሎች ጋር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከዘለቄታው ሃገራዊ ጥቅም ጋር ለማስከበር በጋራ መርሆዎች ላይ በመተባበር በጽናት የሚሰራ ነው። በንቅናቄያችን ውስጥ ያለን አመራሮችም ሆነ አባላት የጥንካሬ ምንጭ የሚቀዳው ከዚህ እውነታ ነው። አይደለም በአገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ታዋቂ በሆኑ በሚሊዮኖች በሚከተሏቸው የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ፊት ለፊት ወጥተን መሟገት የቻልነው ንቅናቄያችን ትክክለኛ አላማና ግብ በማንገቡ ነው። የምንከተለው የትግል ስትራቴጂና ስልትም መዳረሻችንን እንደ መስታወት አቅርቦ የሚያሳየን ነው።

ህወሓት፣ እና “የብሄራዊ ጥቅም”-

በሌላ በኩል የቢቢሲ ሞጋች ፕሮግራም መቅረቤን ተከትሎ የትግራይ ነጻ አውጪ አባላትና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው የተለመደና የነተበ የቅጥፈት ፕሮፖጋዳ ዘመቻቸውን በአዲስ መልኩ ጀምረዋል። ለጠባብና ዘረኛ ቡድናቸው የፖለቲካ ማስጠበቂያ ይሆናል የሚሉትን በተዛባ ሁኔታ በመውሰድ አይናቸውን በጨው አጥበው መጥተዋል። ትላንት ለጋራ ጥቅምና ፍላጎት በቂ ውይይትና ድርድር ማድረግ ተስኗቸው የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ መጣላቸው የተረሳ ይመስላቸዋል፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም“national interest”ፍላጎት ዋና አስጠባቂ ለመምሰል የቀበሮ ባህታዊ ሆነዋል።
እነዚህ ጠባብ የትግራይ ጎጠኞች ጸረ-ኢትዮጵያዊ ባንዳነታቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ የረሳላቸው መስሎአቸው የሰሩት ታሪክ፣ “ሚኒሊክ በሳንጃ የሰበሰባትን እኛ ለመጠበቅ ሃላፊነት የለብንም” በማለት ኢትዮጵያን የወጉ ናቸው። ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ወቅት ሙዋቹ መለስ ዜናዊና ሌሎቹ የወያኔ መሪዎች ከጠላት ጎን በመሰለፍ በሶማሊያ ፓስፓርት ሞቃድሾ በመመላለስ ኢትዮጵያ በባእድ ጦር ስትወረር ለመበታተን የተባበሩ ናቸው። ከውስጣቸው የመነጨው ዶክተር አብይ ምስጋና ይግባውና ትላንትና ከወራሪው ሱማሊያ ጦር ጋር ሲፋለም በካራማራ፣ ሀረርጌ ላይ ከሶማሌያው ሲያድ ባሬ ጦር ጋር ሲዋጋ የተሰዋውን ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች የቀድሞ ሰራዊት አባላትና እነ አሊ በርኬን የመሳሰልይ የላቁ ጀግኖች ያፈራውን የሚሊሽያ ሰራዊት ታሪክ እንዲታወስ አድርጓል።
የትግራይ ነጻ አውጪዎች በጠመንጃ ስልጣን ከያዙም በኋላ “አክሱም ለወላይታው ምኑ ነው? ላሊበላስ ለጉራጌው?” በማለት ከፋፋይና ዘረኛ ፖሊሲያቸውን በግልጭ ሲያራምዱ እንደነበር በአደባባይ የተሰጣ እውነት ነው። ለኤርትራም ከኤርትራውያን በላይ የተዋጋን፣ የታገልን ነን፣ እያሉ አረፋ እየደፈቁ ሲጎማለሉ የነበሩት የህወሓት የጡት አባት እነ ስብሀት ነጋ አይደሉም ወይ?
የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበረው አምባሳድር ሔርማን ኮሂን እንደመሰከረው አሰብ ከኤርትራውያን ጋር መደራደር ሲችል ፣ ኢትዮጵያን የባህር በር እና ወደብ አልባ ያደረገት ፣ በኋላም ይህን የወያኔዎች ስትራቴጂካዊ ድድብና የሚያረጋግጥ ግዙፍ ወንጀል ለመደበቅ ለኢትዮጵያ “ብሄራዊ ጥቅም “ወደብ ሸቀጥ ነው፣ ቀይ ባህርንም ግመሉን ያጠጣበት” በማለት ሲመጻደቅብን ከርሞ ህይወቱ ያለፈው የወያኔው መሪ መለስ ዜናዊና ህወሓት ነበሩ።
የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝብ አከብራለሁ። የወያኔ ሰለባ ነው ብለን እናምናለን። ወያኔዎች እንደሚሰብኩት የትግራይ ህዝብና ወያኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታም እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ወያኔዎች ይህን በየጊዜው በመለፈፍ ሊያሳምኑ ቢሞክሩም። ሆኖም ወያኔዎች 60 ሺ የትግራይ ልጆች መስዋእትነት ከፈልን በማለት ነጋ ጠባ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያቅራሩትበት መነሻ አላማ ለትግራይ ሪፑብሊክ፣ ለ”አባይ ትግራይ” ግንጠላና ምስረታ እንጂ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የተከፈል መስዋእትነት አለመሆኑ ሊታወስ፣ ሊሰመርበትም ይገባል። ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለፍትህ ፣ ለመብት፣ ለእኩልነት ተሰውተው ቢሆን እንኳን እሰየው ባልን ነበር። እነሱ ግን እኛ ስለተሰዋን በእሳት የተፈተንን“ወርቅ ነን”፣ ስለዚህም ሌላው ኢትዮጵያዊ –ኦሮሞው፣ አማራው፣ ጉራጌው፣ ጋምቤላው፣አፋሩ ፣ ወዘተ– ጨርቅ ስለሆነ የወርቅ ዘውድ በመሆን አናቱ ላይ ተፈናጠን እያዋረድነው፣ እየዘረፍን፣ እየገደልን፣ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራና የበታችነት የህወሃት ትግራውያንን የበላይነት በኢትዮጵያ ምድር ላይ እናስቀጥላላን ብለው 27 አመታት በላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው የኢትዮጵያን ህዝብ ደምና አንጡራ ሃብት የሚመጠምጡ የህወሓት ትግራዮች ናቸው።

ይህን አስከፊና ዘግናኝ የሆነ ጸሃይ የሞቀውን የህወሓት ትግራዮች የበላይነት ካላስቀጠልን ደግሞ ኢትዮጵያን ብትፈራርስ ቁብም እንደማይሰጣቸው በአደባባይ የሚነግሩን አሁን እነሱ ናቸው። ኪዚያም አልፈው ኢትዮጵያን እናፈርሳለን በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ የአገር የመበታተን አደጋ ስጋት ወስጥ ለመጨመር ያለ ቅንጣት ሀፍረትና ይሉኝታ በአደባባይ እነአባይ ጸሃይና ስዩም መስፍንን ጨምሮ የሚናገሩ የነሱ መሪዎች ናቸው።

የጦር ፖሊሲን እንደ የውስጥ ጭቆና ማዳፈኛ የሚጠቀሙበት ህዉሃቶች 1998 በፈረንጆቹ አቆጣጠር “ሉዓላዊነትህ ተደፈረ፤ ሻዕቢያ ባድመን ወረረ” በሚል ሲያንኩዋስሱትና ሲያጥላሉት የነበሩትን የኢትዮጵያዊነት ካባ የለሀፍረት ደርበው ህዝቡን ቀሰቀሱት። 21ኛው ክፍለ-ዘመን ላይ ያለን በማይመስል መልኩ አለም ጉድ እስኪል ድረስ ወጣት ኢትዮጵያውያን የፈንጂ እራት ተደረጉ። በወቅቱ የኤታማጆር ሹም የነበረውን ጄ/ል ጻድቃን ወ/ተንሳይን እንባ አውጥቶ ያሰለቀሰ በደናቁርት የህወሓት ትግራይ ጀነራሎች አዝማችነት በተደረጉ በርካታ የመጀመሪያ ዙር ውጊያዎች በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ልጆች ህወታቸው ተቀጠፈ። ፈንጂ ረጋጭ ያደረጉት ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች- የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የጉራጌ፣ የጋምቤላ የሌሎች ብሄር ልጆች– እንዲሁም ለውርደትና ለልመና የዳረጉትን የቅድሞ ሰራዊት አባላትና ጀነራሎች በአስርቱ ሺዎች በድረሱልን ልመና አምጥተው አዘመቱ። እናም በ11ኛ ሰአትም በቀድሞዎቹ የሰራዊት አባላት፣ አዛዦችና የኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ብርታትና መስዋእትነት ውጤቱ ወደ ኢትዮጵያ ሊያዘም ቻለ። በወቅቱ ውያኔ ከኤርትራ ጋር ባደረገው ጦርነት ከ96 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ የጦርነት አላማ፣ “ባድመ” የማን ለማንስ “ብሄራዊ ጥቅም” መሆኑን በማያውቁት ጦርነት ህይወታቸውን ገበሩ፣ እካለ ጎዶሎም ሆኑ። ለዚያውም ከጦርነቱ በሁኋላ ሟቹ የውያኔ መሪ “ ኣባታቸውን የሞተባቸውን ማን ያመጣቸው” በማለት የቀድሞ ሰራዊት አባላትና የወታደራዊ አዛዦች በድጋሚ እንዲባረሩ ማድረጉ ይታወሳል። ይህን ዳግም የተፈጸመ ክህደትና ጭካኔ ለማይረሱ ፣ የወጋ ቢረሳ… ነውና ።
በሌላ በኩል የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት እልባት ለመስጠት የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአሜሪካ መንግስት…… ወዘተ ባደረጉት ጥረት የባድመን የባለቤትነት ጉዳይ ለመዳኘት ወደ አለም አቀፍ ፍርድቤት ለመሄድ ስምምነት ተደረሰ። የትግራይ ነጻ አውጪ መንግስት መሪዎች የአለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይግባኝ የሌለው እንዲሆን ከኤርትራ መንግስት ጋር ተፈራረሙ። እናም በሔግ በተደረገው ክርክርና ብይን ባድመ ለኤርትራ ተብላ በድንበር ኮሚሽኑ ተወሰነች። ወያኔዎች በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበረው ስዩም መስፍን በአደባባይ ነጭ ውሸት የኢትዮጵያን ህዝብ አሳስቶ “የጦርነቱ ድል በፍርድ ቤትም ተደገመ” በሚል በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ እስከማስወጣት ደረሰ። በውሸታሞች እውነት ተደብቃ አትቀርምና የትግራይ ነጻ አውጪ ቅጥፈት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጋለጠ። እንግዲህ ሐቁ ይሄ ነው።
ሁላችንም በቅርበት እንደተከታተልነው የኤርትራ መንግስት በሁለቱ አገሮች መካከል ውይይትም ሆነ ድርድር የሚጀመረው “የሕግ የበላይነት” ሲከበር ብቻ እንደሆነ ደጋግሞ አሳውቋል። ይግባኝ በሌለበት የአለም አቀፍ ፍርድ ቤት የተወሰነው ውሳኔ ወደ ተግባር እንዲቀየር የአለም መንግስታትን አሳስቧል። እኔም በቢቢሲው ሞጋች ፕሮግራም የተናገርኩት ይሄንን ነበር። ታዲያ ወያኔዎችና የነሱ ጋሻ ጃግሬ ቱቦዎች የ”ኢትዮጵያ ብሂራዊ ጥቅም” ዘብ እና ዋና ጠበቃ ሆነው ለመቅረብ ያዙኝ ልቀቁኝ ይወራጫሉ።

የኢትዮጵያ “ብርሄራዊ ጥቅም”በእርግጠኝነት የሚጠበቀው በኢትዮጵያ ላይ የተጣበቀው የህወሓት ደም መጣጭ መዥገር ስንላቀቅ ብቻ ነው። ከጎንደር፣ ከወሎ መሬት የዘረፉ እነሱ፣ ለባእዳን ለህንዱ፡ ለአረቡ፣ ለሱዳን መሬት ቆርጠው የሚሰጡ፣ የሚቸበችቡ ፣ ህዝባችንን በማፈናቀል ደም እንባ በምድረ ኢትዮጵያ እንዲጎርፍ ያደረጉትም እንሱ ናቸው። እኛ እይደለንም። ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያን ህዝብ ሲረግጡ፣ ሲያደሙ፣ ሲዘርፉ፣ ሲደፍሩ ፣የንጹሃንን ደም እንደጎርፍ በምደረ ኢትዮጵያ ሲፈሱ የኖሩ ጉዶች ዛሬ ስለኢትዮጵያ “ብሄራዊ ጥቅም” ዋነኛ ጠበቃ ለመሆን ምንስ የሞራል፡ የታሪክና የፓለቲካ መነሻ ሊኖራቸው ይችላል? የውቅሮ ብልጣ ብልጦችና የነሱ ጋሻ ጃግሬዎች ቱሪስት መብላት ይቻላሉ።
ነአምን ዘለቀ

ጠ/ሚኒስትሩና የመቀሌ ቆይታቸው (ኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ጠ/ሚኒስትሩና የመቀሌ ቆይታቸው

ሰኞ ሶስተኛ ሳምንታቸውን ይጀምራሉ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጉዞ፡ በስብሰባ፡ በጉብኝት፡ ተጠምደው ቆይተዋል። ጂጂጋ ሄደው፡ አምቦ ደርሰው ከመቀሌ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። በመሃል በቤተመንግስት ”ተፎካካሪ” በሚል ከሚጠሯቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፡ ሲቪክ ማህበራት፡ ታዋቂ ሰዎች ጋር እራት በልተዋል። ነገ 25ሺህ የሀገሪቱን ወጣቶች ይሰበስባሉ።

በዚሁ ከቀጠለ ወደ ባህርዳር ጎራ ብለው የአማራውን ህዝብ መጎብኘታቸው ይጠበቃል። አንዱ ጋር መጥተው ሌላው ጋር መቅረት ችግር አለውና ወደ ሀዋሳ አቅንተው፡ አሶሳ ደርሰው፡ ከሰመራ ጎራ ብለው፡ ከጋምቤላ አርፈው፡ ከሀረር ጆጎል ሄደው፡ ድሬ ከዚራን ብለው ከሸገር አዱ ገነትም ህዝቡን ሰብስበው ኢትዮጵያዊነትን ሰብከው፡ በጣፋጭ ንግግሮች አረስርሰው የጫጉላ ጌዜያቸው እስኪያበቃ እረፍት ባጣ ጉዞ መሰንበታቸው የሚጠበቅ ነው።

ነጋዴዎችን መሰብሰባቸው አይቀርም። ከአራቱም አቅጣጫዎች ሴቶችን ጠርተው ሊያነጋግሩ ይችላሉ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም ለብቻቸው ውይይት ያስፈልጋቸዋል። ከ1ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ መምህራን እንዳሉም መዘንጋት አይገባም። አርሶ አደሮች የልማታዊው መንግስት አንቀሳቃሽ ሞተር መሆናቸው ይታወቃል። አርብቶ አደሮችም የኢህአዴግ የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በጫጉላው ሽርሽር ወቅት ቢገናኙ መልካም ነው።😛

ለዚህ ጫጉላ ሽርሽር ሁለት ወርም የሚበቃ አይመስልም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መቀሌ ላይ ከጣሏቸው አንዳንድ ነጥቦች በቀር በኦህዴድ ስብሰባዎች ላይ የነገሩንን፡ ባለፉት ወራት በተለያዩ በቃለመጥይቆቻቸው የሰበኩንን፡ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ከፍ አድርገው ያሳዩንን የተከበረችና ታላቅ የሆነችውን ኢትዮጵያን ይዘው ቀጥለዋል።

በአንጻሩ የሀገሪቱ ችግር እንደዛው ነው። መታሰሩ ቀጥሏል። የንጹሃን ግድያ አልቆመም። የእርስ በእርስ ግጭቶች በመጠነም፡ ጉዳት ስፋትም ቀጥለዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳለ ነው። እነአንዳርጋቸው አልተፈቱም። እነ ታዬ ደንደአ እዚያው እስር ቤት ናቸው። የህወሀቶች ስግብግብነት ልጓም አጥቶ እየገሰገሰ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ይሰጣቸው የሚለው ድምጽ በርክቶ ይሰማል። እስከመቼ? ምን ሲያደርጉ እንመዝናቸው? ለሚለው ተያያዥ ጥያቄ ሾላ በድፍን እንጂ መልስ የሚሰጥ የለም። ካለም አልተሰማም። የጫጉላው ወቅት በዝቷል። ሸልፋቸው ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ተቆልለው እሳቸው ጉብኝቱ ላይ ብቻ ማተኮራቸው ለትዝብት ዳርጓቸዋል። ዛሬ ከደቡብ ኢትዮጵያ እንደምንሰማው በግጭት የሰነበቱት ጉጂዎችና ጌዲዮዎች ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። መንደሮች እየተቃጠሉ ነው። ሰዎች እያለቁ ነው። ሺዎች እየተሰደዱ ነው። አንድ መሪ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ሲከሰት መደበኛ ስራዎችን አቁመው ግብረሃይል አቋቁመው ቀውሱን ለማርገብ ይጥራል እንጂ በዙረት አይጠመድም።

መቀሌ ምን ተፈጠረ?

የዶ/ር አብይ የመቀሌው ቆይታቸው ብዥታን የፈጠረ፡ ደጋፊዎቻቸውን ሳይቀር ትካዜ ውስጥ የከተተ ሆኗል።በእርግጥ የእሳቸው መመረጥ በህወሀት መንደር ድንጋጤን ፈጥሯል። የትግራይ ተወላጆች ሁሉም ማለት ባይቻልም አብዛኛው ደስተኛ እንዳልነበር በተለያዩ መልኩ መረዳት ይቻላል። ለአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ቃላቸውን የሰጡ ሁለት የትግራይ ምሁራን የተናገሩትን ወስደን የትግራይ ህዝብን የልብ ትርታ ከለካነው የዶ/ር አብይ መመረጥ ምቾት የሚሰጥ አይደለም። እናም የትግራይን ህዝብ ይሁንታ ማግኘት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት የተሰጠው ይመስላል። ይህን ማድረጋቸው ችግር አይሆንም። ያኮረፈን ማነጋገር ይገባቸዋል። መሪነታቸው ለትግራይ ህዝብ ጭምር በመሆኑ ቀርበው ሊያነጋግሩት እንደሚገባ ይታመናል። በዚህ ተቃውሞ የሚያቀርብ ያለ አይመስለኝም። ጉዳዩ እዛ ሄደው ምን ይላሉ የሚለው ነበር።

እንደመለስ ዜናዊ ”ወርቅ ህዝብ ናችሁ፡ በእሳት የተፈተናችሁ” የሚል ቃል ይወጣቸው ይሆን? ብሎ የሰጋ ቢኖር አያስገርምም። እንደሃይለማርያም ደሳለኝ ” ለትግራይ ህዝብ ከፍለን የማንጨርሰው የ100 ዓመት እዳ አለብን” ብለው ቢያስደነግጡንስ? የሚል ፍራቻ ያደረበት ሰውም ሊኖር ይችላል። ሰውዬው እንደሃይለማርያም የሚጃጃሉ አይሆኑም፡ ለራሳቸው ክብር ያላቸው፡ ደፋር ሰው በመሆናቸው ነጥብ ጥለው አይወጡም በሚል እርግጠኛ ሆነው የተናገሩም ነበሩ።

ለእኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመቀሌው ጉብኝት የትግራይን ህዝብ መከፋት በመጠኑ ያስታገሰና የህወሀት መሪዎችን ድንጋጤ በትንሹ ያበረደ ከመሆን ያለፈ ብዙም ትርጉም አልነበረውም። በትግርኛ መናገራቸውን አድንቄዋለሁ። መቀሌዎችም ከልባቸው ሲያጨበጭቡላቸው የነበረውም አንድም በአፋቸው ስላናገሯቸው ነው። የቋንቋ ሃያልነቱም ይሄው ነው። ዋናው ጉዳይ ከሆነውና ካደረጉት በላይ በዚህን ወቅት ምን ሊያደርጉ ይችሉ ነበር? የሚለው ነው።

በእርግጥ በመጡበት መንገድ አላገኘኋቸውም፡፡ ባስለመዱን የንግግር ቅኝት ከጆሮዬ አልገቡም። ይልቅስ ከመለስና ከሃይለማርያም ንግግሮች የተጣቀሱ፡ እርስ በእርስ በሚጋጩ አስተሳሰቦችና አቋሞች የተሞሉ፡ ግማሽ እውነት፡ ከፊል ሽንገላ የሞላበት፡ ከምናውቃቸው ጥልቅ አስተሳሰብ ወጥተው እንደአንድ ተራ የኢህአዴግ አመራር ባዶ የቃላት ጋጋታ ያጠላበት ንግግር ነው የሰማሁት። በእነዚያ ቃለመጠይቆችና የመድረክ ንግግሮች የምናውቃቸው፡ በፓርላማው የሰማናቸው፡ አብይ መቀሌ ላይ ጠፍተውብኛል።

በወረቀት የሰፈረውና የተዘጋጁበት የ18 ደቂቃ ንግግር ነጭ ከጥቁር የተደባለቀበት፡ ሽንገላና እውነት የተፈራረቁበት፡ ሴጣንና መላዕክ የተጠሩበት፡ ግማሽ እውነት ከፊል ተረት ያጠላበት ነው ማለት ይቻላል። መለስ ዜናዊን ጨምሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር የሚጠሉና ሀገር ያጠፉ ክፉ ሰዎችን ስም እየጠሩ ማወደሳቸው ግን የፖለቲካ ጨዋታ ሊሆን ይችላል ብለን ይቅር ብለናቸዋል። አጼ ሚኒሊክን ከአድዋ ጋር አንስተው ባወደሱበት አንደበታቸው፡ ከመንደሩ ርቆ ማየት ሳይችል ይህቺን አለም የተሰናበተውን መለስ ዜናዊን ማንቆለጳጰሳቸው ለጆሮ ይቀፋል። ይጋጫልም። በአንድ ሰው ውስጥ እንዚህ ሁለት ግለሰቦች እኩል ቦታ ካላቸው ችግር አለ ማለት ነው። በበዓለ ሲመታቸው አንድም ቦታ ስሙን ያልጠሩትን መለስ ዜናዊን መቀሌ ላይ ”ብጻይ መለስ” እያሉ ማወደስ የእውነት አምነውበት ወይስ የህወሀትን አመራሮች ለማስደሰት? ፖለቲካ አስቀያሚነቱ እዚህ ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህወሀትን ሰማዕታት አወድሰዋል። ዘላለማዊ ክብርንም ተመኝተዋል። ከምንም በላይ የጎረበጠኝ ይህ ንግግራቸው ነው።መሰረታዊ ጥያቄ ላንሳ። ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ አመራር እስከመሆናቸው እንድንዘነጋ ያደረገን የትኛው ተግባራቸው ነው? እስከአሁን በተግባር የተለካ ምን ሰርተው ነው ቀልባችን የወደዳቸው? ንግግር… ንግግር… ንግግር ነው። ጥልቅ አመለካከታቸው ነው። ስለኢትዮጵያ ያላቸው ፍጹም ያልተዛነፈ ስሜት ነው። በእርግጥ ከዚያ ያለፈ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን አውቀን፡ በምን ለክተን ወደድናቸው? ታዲያ ብቸኛው ፍቅርን የሸመቱበት፡ ተወዳጅነትን ያገኙበት ንግግራቸው ሆኖ ሳለ እሱም እርስ በእርሱ ሲጋጭ፡ ሀሳባቸው ከቀደመው ጋር ሲላተም፡ ከእሳቸው ምን ቀረን ብንል – ማን ነው ጥፋተኛ የሚለን?

ለትግራይ ሰማዕታት አክብሮት መስጠቱ አይከፋም። አምነውበትም ይሁን ሳያምኑ፡ ተገፍተውም ይሁን ገፍተው በዚያ ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ ክብር ይገባቸዋል። ሆኖም ሰማዕት የሆኑለትን ዓላማ ማወደስ ትልቅ ፋወል ነው። የሌላውን የሚመሩትን ህዝብ ማስቀየም ነው። የህወሀት ዓላማ የተቀደሰ አልነበረም። ኢትዮጵያን ለማጥፋት ተማምለው ጫካ የገቡና ባለፉት 40ዓመታት በበረሃና በቤተመንግስት የኢትዮጵያን አንድነት ሲገዘግዙ እድሜአቸውን የጨረሱና የሸበቱ ህወሀቶችን ቅዱስና የተባረኩ አድርጎ ከማሳየት የከፋ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያስቀየም፡የሚያበሳጭ ምን ይኖር ይሆን?

ዶ/ር አብይ ሁሉንም ማስደሰት አይችሉም። ሀርነት የምታወጣቸው እውነት ብቻ ናት። ሽንገላን የፖለቲካ መስመራቸው ቅኝት ማድረግ የለባቸውም። ህወሀቶችን ለማስደሰት የኢትዮጵያን ህዝብ ማስቀየም አይገባቸውም። ያ መቀሌ መሃል የቆመው ሀውልት ለኢትዮጵያ አንድነት፡ ዳር ድንበሯ እንዲከበር ደም አጥንታቸውን የከሰከሱ፡ በኤርትራ በረሃ፡ በትግራይ አፈር ውስጥ ተቀብረው የቀሩ የኢትዮጵያ ልጆችን ወቃሽ፡ ተሸናፊ አድርጎ የሚያሳይ ሀውልት ነው። ከቀድሞ መንግስት ጎን ተሰልፈው የሞቱ ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮጵያ እንጂ ስለመንግስቱ ሃይለማርያም አለነበረም። የደርግ ጭቆና አንገሽግሾን ነው በረሃ የወረድነው የሚለው ተረት ተረት አይሰራም። ደርግ ገና ስልጣን ከመያዙ በረሃ የገቡ ሰዎች ጭቆናውን የት አይተውት እንደሆነ ለመጠየቅ እንወዳለን። ከህወሀት ማኒፌስቶ ላይ የተጻፈው የደርግ ጭቆና አይደለም። ህወሀት ደርግም ባይኖር በወቅቱ ሊኖር የሚችል የትኛውም የኢትዮጵያ መንግስት መውጋቱ የማይቀር ነው። ዓላማው የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ነበርና።

እናም ዶ/ር አብይ በመቀሌ የመገንጠል አጀንዳ ቀርጾ፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማፈራርስ እኩይ ዓላማ ሰንቆ የኢትዮጵያ ጠላት ከሆኑ ሀገራት በሚሰጥ እርጥባንና የመሳሪያ ድጋፍ ወደ ቤተመንግስት የገሰገሰን ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅት የሆነውን ህወሀትን ሲያወድሱ ትዝ ያለኝ ያ ታሪካዊ ንግግራቸው ነው። ካራማራ አፈር ውስጥ አጽሙ ስለተቀበረው የአማራ ልጅ የነገሩን፡ ከአድዋ አፈር ጋር ደም አጥንቱ ስለተቀላቀለው የኦሮሞ ጀግና ያወሱን፡ በመተማ ለኢትዮጵያን ነጻነት ሲል አንገቱን ለሰይፍ ስለሰጠው የትግራይ ንጉስ የተረኩልን አንድ በአንድ ከጆሮዬ ጓዳ አቃጨለ። እንዴት ይሆናል?

ዶ/ር አብይ ከመቀሌ ነዋሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ላይ ሌላ ሰው መስለው ነው የቀረቡት። ሁሉን ነገር በቅንነት መመልከት የሚመርጡት ዶ/ር አብይ፡ የትኛውንም ሃይል በፍቅርና በአክብሮት በመጥራት ቀልብን የሚሰርቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፡ ችክ ካለውና ከጠነዛው የኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ትርክት ወጥተው ሊበራል አስተሳሰብ ይዘው ብቅ ያሉት ኮሎኔል አብይ–በመቀሌው ስብሰባ ላይ ቅኝታቸውን ቀይረው፡የኢህአዲግነት ጭምላቸውን አጥልቀው፡ በአጭሩ መለስ ዜናዊን መስለው ሳያቸው በልቤ ያሳደርኩትን ተስፋ አዳመጥኩት። በእሳቸው አሻግሬ የተመለከትኩትን መልካም ጊዜ እንዳላጣ ሰጋሁ። ምነው ዶክተር?

ዶ/ር አብይ ወደ መቀሌ ከማምራታቸው በፊት በቤተመንግስት በነበረው የእራት ግብዣ ላይ ስለተፎካካሪ ፓርቲዎች የተናገሩትም ከቀደሙት የኢህአዴግ መሪዎች በቋንቋ እንጂ በስትራቴጂ የተለየ አልነበረም። አማራጭ አቅርቡ የሚለው የኢህ አዴግ ድርቅ ያለ አቋምን አንጸባርቀዋል። በ1997ቱ ምርጫ የኢህ አዴግ ተቃዋሚዎችን የማሳነስና በህዝብ ዘንድ ደካማ አድርጎ የማሳጣት አቅጣጫው አማራጭ እንደሌላቸው ደጋግሞ መግለጽ ነበር። ቅንጅት ዳጎስ ያለ፡ አዳዲስ ሀሳቦችን የሰነቀ፡ ሀገሪቱን በተሻለ አቅጣጫ የሚወስድ አማራጭ ይዞ ነበር። መለስ ዜናዊ የቅንጅትን መሪዎች በሙሉ እስር ቤት አስገብቶ፡ የቅንጅት ቢሮ እንዲሰበር አድርጎ በቅንጅት የተዘጋጀውን ሰነድ በመዝረፍ የራሳቸው አድርገው መጠቀማቸውውን በቅርበት ለምናውቅ የ ”አማራጭ አቅርቡ” አንድ ዓይነት ዜማ ለምን ደጋግማ እንደምትሰማ እንረዳለን። ዶ/ር አብይ ይህንኑ ዜማ በቤተመንግስት ሲያቀነቅኑ ስሰማ ስለእሳቸው ጥያቄዎች ውስጤ መነሳት ጀምረዋል።

ወደ መቀሌ እንመለስ። የትግራይን ህዝብ ወርቅ ነው ብለዋል። በእሳት የተፈተነ ወርቅ መሆኑን ተናግረዋል። ከአቶ መለስ የ1985ቱ ንግግር ”እንኳን ከእናንተ ተፈጠርኩ።” የሚለው ሲቀር ሌላውን ብለውታል። በእርግጥ መለስ ዜናዊ ሲናገረው ለሌላው ህዝብ ካለው ጥላቻ መሆኑ ይገባናል። ዶ/ር አብይን በዚያ ደረጃ መለካት ተገቢ አይደለም። ስለየትኛውም ህዝብ ጥላቻ እንደሌላቸው እንገነዘባለን። እንደመለስ ዜናዊ አንዱን ህዝብ ከላይ ሰቅለው ሌላውን ለመደፍጠጥ በለው የተናገሩት ነው ለማለት ፈጽሞ የሚቻል አይደለም። በመሰረቱ ወርቅ ብሎ አንድን አካል መግለጹ ችግር አይደለም። መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን አገላለጽ ችግር እንዲኖረው በማድረጉ እንጂ። እናምበአቶ መለስ ያ ንግግር ለተጎዳ ሌላው ኢትዮጵያዊ የዶ/ር አብይ መድገም ጥሩ ስሜት አይሰጥም። ቃል ከባድ ነው። በቃል የተነገረ መቼም አይጠፋም።

ዶ/ር አብይ በኦሮሚያ ክልል ስለታሰሩት የትግራይ ተወላጆች የተናገሩትም ጥያቄ የሚጭር ነው። የህግ የበላይነትን ለማስፈን የሰውዬውን ቁርጠኝነት አደጋ ውስጥ የሚከት ነው። ያለወንጀላቸው፡ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁ፡ በህወሀት ገራፊዎች ስጋቸው የተተለተሉ ኢትዮጵያውያንን ነጻ እንዲወጡ ያደርጋሉ ተብለው ሲጠበቁ ህዝብን ለመጨረስ እጅ ከፍንጅ ተይዘው የታሰሩትን የህወሀት አባላትን ለትግራይ ህዝብ ስንል እንፈታቸዋለን ማለታቸው አስደንግጦኛል። ከህግ አንጻር ግዙፍ ስህተት ነው። የሚያስተላልፈው መልዕክትም አደገኛ ነው። የትግራይን ህዝብ ቁጣ ለማብረድ ይህን ያህል ርቀት መሄዳቸው ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው።

ዲያስፖራውን የገልጹበት ንግግራቸው ስለወልቃይት ምን እንደሚያስቡ ፍንጭ የሰጡበት ነው ማለት የሚቻል ነው። ዲያስፖራውን መረጃ የሚያገኘው ከፌስ ቡክ ነው የሚለው ድምዳሜአችው ግልብ ነው። ምናልባት የህወሀቶችን ትርክት በመድገም ከጎናቸው የተቀመጡትን ዶ/ር ደብረጺዮንን ለማስደሰት ይሆናል። ዶ/ር አብይ ቅንነት ያጣሁባቸው፡ ሙልጭ ያለ የኢህአዴግ ካድሬ መስለው በቀረቡበት በዚህ ንግግራቸው የዲያስፖራውን የመረጃ ምንጭ ፌስቡክ ብቻ እንደሆነ ሲናገሩ የእሳቸው አንደበት ስለመሆኑ እስከመጠራጠር የሚያደርስ ነው። ዲያስፖራው እዛ ኢትዮጵያ ካለው ኢትዮጵያዊ በላይ ስለኢትዮጵያ የየዕለት ክስተት መረጃ እንዳለው አጥተውት አይደለም። ኢህአዴጋዊ ባህሪያቸው አሸንፎአቸው እንጂ። የሰሜን ጎንደር ህዝብ ጥያቄው ልማት ነው፡ ውሃ ነው፡ መብራት ነው የሚለው ደረቅ ትርክታቸውን የሰማ አንድ ወዳጄ የመቀሌ ውሃ ስትጠጣ የምትናገረው እንዲህ ነው ብሎኝ አረፈ። አጃኢብ ነው። የወልቃይት የማንነት ጥያቄ፡ የሰሜን ጎንደር ህዝብ የነጻነት ረሃብ በእርግጥ ከመቀሌ ቁጭ ብሎ በኢህ አዴግ መነጽር ለሚመለከት ላይገለጽለት ይችላል። ወይም እንደዚያ ማሰብና መቀበል አይፈልግም።

ባልተለመደ መልኩ፡ ነጋዴዎች ናቸው፡ ለእንጀራቸው ሲሉ ህዝብን ያጋጫሉ፡ ከሚለው አንስቶ አንዳንድ የተጠቀሟቸው ቃላትና ሀሳቦች የዶ/ሩን ስብዕና ዝቅ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። ይህ መሆኑ ዶ/ር አብይ ከህወሀት ተጽዕኖ ለመላቀቅ የመቻላቸውን ነገር አሳሳቢ ያደርገዋል። ህወሀቶች በቀጣይም ፈላጭ ቆራጭ እንዳይሆኑ በዶ/ር አብይ በኩል ተስፋ ላደረጉ ሚሊዮኖች የመጀመሪያው የአደጋ መብራት ብልጭ ያለባቸው ይመስላል።

ዶ/ር አብይ የምር ስልጣን እንዲኖራቸው ከሚመኙትና ከሚናፍቁት አንዱ ነኝ። የጫሩት ተስፋ ወደ እውነተኛ ለውጥ እንዲቀየር ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አምናለሁ። ጊዜ ይሰጣቸው ከሚሉት ጋር ጸብ የለኝም። ነገር ግን እጃችንን አጣጥፈን ከእሳቸው ተአምር ለመጠብቅ ብቻ በሚል ጊዜ የምንሰጥ መሆኑ ላይ ግን ልዩነት አለኝ። ትግሉን እንዳያስተኙት እሰጋለሁ። ለትግሉ የተላኩ ህመም ማስታገሻ መድሃኒት እንደማይሆኑ ምን ዋስትና አለን? አንዳንድ ምልክቶችን እያሳዩን ከንግግራቸው ባለፈ ዋስትና የሚሆን ነገር እያደረጉ ለዋናው ስር ነቀል ለውጥ ጊዜ እንዲወስዱ ቢደረግ አንድ ነገር ነው። አንጋጦ መና መጠበቅ ላይ ያተኮረው አካሄዳችን ግን አደጋ አለውና እናስብበት።

ተፎካካሪ ወይስ ተቃዋሚ ? ( ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)

ተፎካካሪ ወይስ ተቃዋሚ ?

ዶ/ር አብይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃዋሚ ሳይሆን ተፎካካሪ ተብለው እንደሚጠሩ ከተናገሩ በሁዋላ ብዙዎቻችን ሃሳቡን ደግፈነዋል። ቃሉ ተቃዋሚዎችን ለማቅረብ ተብሎ በቅንነት የቀረበ እንደሆነ እረዳለሁ። ሃሳቡ በቅንነት ቢቀርብም ተቃዋሚዎችን ሁሉ ተፎካካሪ ብሎ መጥራቱ ግን ትክክል አይመስለኝም። በኢትዮጵያ ሁኔታ ከኢህአዴግ በተቃራኒ የቆሙትን ፓርቲዎች በሁለት መክፈል ይቻላል። ከኢህአዴግ ጋር በግብ ሳይሆን በተወሰኑ የአፈጻጸም ልዩነት “ታቃዋሚ” የተባሉት ፓርቲዎች ተፎካካሪ ሊባሉ ይችላሉ፤ ከኢህአዴግ ጋር ሰፊ የግብ ልዩነት ያላቸው ፓርቲዎች ግን ተቃዋሚ እንጅ ተፎካካሪ ተብለው ሊጠሩ አይችሉም።

እኔ እስከሚገባኝ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ( competitive parties) የሚባሉት የመጨረሻ ግባቸው አንድ ሆኖ በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ብቻ ልዩነት ያላቸው ናቸው። የአየለ ጫሚሶን ወይም የተወሰኑ ብሄር ተኮር ፓርቲዎችን ተፎካካሪ ልትላቸው ትችላለህ፤ ሰማያዊ ፓርቲን ወይም አርበኞች ግንቦት7 ትን ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ልትላቸው አትችልም፤ ተቃዋሚ እንጅ። ግባቸው ከኢህአዴግ በተቃራኒ የቆመ ነው። ሰማያዊዎች አዲሱ ስያሜ ከተስማማቸው አላውቅም፣ “ተቃዋሚ” ተብለው መጠራታቸው ግን ሲጠቅማቸው እንጅ ሲጎዳቸው አይታየኝም። እነዚህ ፓርቲዎች “ተፎካካሪ” ተብለው ለመጠራት ከኢህአዴግ ጋር መሰረታዊ በሚባሉ የዲሞክራሲና የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ስምምነት ማድረግ አለባቸው። ያን ደግሞ እስካሁን አላደረጉም። ልዩነታቸው የብርቱካንና የአፕል ያክል ነው፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ ተፎካካሪ ብሎ መጥራት “ሹፈት” ወይም የሁለቱን ቃላት ትረጉም ካለመረዳት የመጣ ይመስለኛል። እስኪ እንከራከርበት።

ስለ ዶክተር ዓብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒትር ሆኖ በመመረጥ ከአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ የወጣ መግልጫ

የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ መግልጫ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትህና እኩልነት የናፈቀው በመሆኑ በኣዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መመረጥ ደስታውን እየገልጸ ይገኛል።

የኣፋር ነጻ አውጭ ግንባር ፓርቲ በዶክተር ዓብይ አህመድ መመረጥ የኢህአደግ የተለመደ ድራማ ወይስ ለወጥ ፈላጊ ድርጅቶች የህውሃት የበላይነት የመረራችው በአንድነት አዲሲቱን የአጋራ ኢትዮጵያን ሰላም የሰፈነባት ፍትህ የተረጋገጠባት የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተከበረባት ሃገር ለማየት ባደረጉት ቁርተኝነት ከሆነ እሰየው እንላለን።

የተለመደው ድራማ ከሆነ በአሁኑ ሰአት የተነሳው የለውጥ ፈላጊ ትውልድ ትግል ለመግታት እና የእፎይታ ግዜ ለመውሰድ ታስቦ ከሆነ የለውጥ ፈላጊውን ትውልድ ትግል ማንም ሊገታው የማይችል አንድ ግዜ የተቀጣጠለ ሰደድ መሆኑን በመግለጽ በአገሪቷ ለረጅም አመታት በጉጉት ይጠብቅ የነበረውን እውነተኛ የፌደራል ስርዓት እውን እይዲሆን እንጠይቃለን። ይህም ዕውን እንዲሆን ከ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲፈጸሙ የምንፈልጋቸውን ዋና ዋናና ወቅታዊ ጉዳዮች እንድሚከተለው እናቀርባለን።

የአስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁን ማንሳት የፖሊቲካ፤ የሃይማኖትና የሰበዓዊ መብት ታጋዮችን ያለቅድመ ሁኔታ መፍታት ከተቃዋሚ የፖሊቲካ ሃይሎች ጋር ግልጽና እውነተኝነት በተሞላበት መንገድ የውይይት መድረክ መክፈት፤ እንዲሁም የፖሊቲካና የዲሞክራሲውን ምህዳር በማስፍት የመጻፍና የመሰብሰብ መብትን ማስከበር።

የፌደራል ፖሊስ፤ የሴኩሪቲና የመከላከያን የበላይነት ከክልሎች በማስወገድ፤ በነጻነት የራሳቸውን ክልል እንዲያስተዳድሩና የሕዝቦቻቸውን ጥያቄወች በዲሞክራሲያዊ መንግድ እንዲፈቱ ማድረግ።

በልማት ምክኒይት ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ እና በኣስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጎዱ የሞያሌና አካባቢዋ ኑዋሪውውች የመልሶ ማቋቋም ስራ እንዲስራ እንጥይቃለን።

የኣፋር ነጻ አውጭ ግንባር ፓርቲ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኣገራችንና ለሕዝባችን አዲስ ሞእራፍ በመክፈት፤ በነጻ መድርክ ውይይትና ግልጽነት የተሞላበት መግባባት በምፍጠር፤ ውድ ኢትዮጵያችን አብረን መገንባት እንድንችል፤ እድገትና ብልጽግናዋን ለማስፋትና ለማሳደግ፤ ይህን መልካም አጋጣሚውን እንዲጠቀምበት እናሳስባለን።

ቀጣዬ 100 ቀናት! (በኤርሚያስ ለገሰ)

ቀጣዬ 100 ቀናት!

በኤርሚያስ ለገሰ

መንደርደሪያ

የትግራይ ነፃ አውጪ በገጠመው ሕዝባዊ ማእበል፣ እንዲሁም የሕዝቡን ተቃዉሞ በተከተለበት ጫና ዶክተር አቢይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አምጥቷል። የዶክተር አቢይ ወደ ፊት መምጣት በብዙ መልኩ የተደበላለቀ ስሜቶችን ፈጥሯል። በህውሓት ደጃፍ ከፍተኛ ቁዘማና ንዴት የፈጠረ ሲሆን በለውጥ ፈላጊው ዘንድ የተከፋፈለ አስተያየቶች በመስተናገድ ላይ ናቸው። በተለይም ዶክተሩ በበአለ ሲመቱ እለት ያቀረበው ንግግር የብዙ ኢትዬጲያውያንን አንጀት ቅቤ ያጠጣ ነበር። በታሪካዊነቱም ተመዝግቧል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በስልጣን ኮርቻው ላይ የወጣው ዶክተር አቢይ እጅግ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ መንፈሱ የተበታተነው

ን የኢትዬጲያ ህዝብ ለማረጋጋት፣ ኢትዬጲያን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ሁሉንም ኃይሎች ለማስተባበር፣ የኢኮኖሚ እና ፓለቲካ እቅዶችን ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጓል።

ይህንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ቀናት ወደ ተግባር ሊመነዝራቸው ይገባል የተባሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸዉ ድርጊቶች መዘርገፍ ጀምረዋል። ሰውየው ለወደፊቱ ያለበትን ተልእኮ የሚያሳስበውም ብዙ ነው። እኔም እንደ አንድ ኢትዬጲያዊ ዶክተር አቢይ በኦሮሚያ የጀመረውን ስራ ሳይጨርስ ወደ ፌዴራል መምጣቱ ልቤ አልተቀበለውም። ተቃውሞዬን በአደባባይ ገልጫለሁ። በጠላቶቹ ሜዳ ላይ ከመጫወቱ በፊት የራሱን ሜዳ በብረት እንዲያጥረው ፍላጐቴ ነበር።

አሁንም ቢሆን ከትላንት አቋሜ የተለወጠ ነገር የለኝም። በስልጣን ላይ ያለው ሽፍታ አገዛዝ አሁንም የስለላና ወታደራዊ መዋቅሩን የተቆጣጠረው ነው። ወደድነውም ጠላነውም የኢኮኖሚ መዋቅሩን የተቆጣጠረው ይህ ከፋፋይ ቡድን ነው። ሌላው ቀርቶ የአሁኖቹ የዶክተር አቢይ የግልና የቤተመንግስት ጠባቂዎች የሟቹ መለስ ዜናዊ ጠባቂዎች ናቸው።

በመሆኑም ሰውየው በአምባገነኖች፣ በዘረኞች፣ በማይማን፣ ኢትዬጲያን በሚጠሉና በሚያሳፍሩ ሰዎች መዳፍ ውስጥ መግባቱን ስመለከት መንፈሴ ይረበሻል። የትግራይ ነፃ አውጪ ካድሬዎች እና ባለሟሎች እንዳይሰራ መውጪያ መግቢያውን እንደሚዘጉበት ሳውቅ ልቤ ይደማል። በፈላ ውሃ እንደምትቀቀለው እንቁራሪት እየሆኑ ያሉት ህውሓቶች የተካኑበትን አጥፍቶ መጥፋት ፓሊሲ እንዳይፈፅሙበት እሰጋለሁ።

በሌላ በኩል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኢትዬጲያ ህዝብ ያቀረበው ራዕይ አስደስቶኛል። የኢትዬጲያ ተስፋና የኢትዬጲያችን መቀጠል ሲያስጨንቀው አብሬ ተጨንቄያለሁ። ዶክተር አቢይ የሕዝብ አሽከር ሆኖ ሕዝብን ለማገልገል ቆርጦ መነሳቱን ሳይ በምን ልደግፈው እችል ይሆን የሚል ጥያቄ አንስቻለሁ። የጠላት ሜዳ ላይ አሸንፎ ለመውጣት እንዴት ቢጫወት ያዋጣዋል የሚለውን አስቤያለሁ።

እናም ዶክተር አቢይ የኢትዬጲያ ህዝብ ትግልና እምቢተኝነትን እንደ ነዳጅ እየወሰደ የተቆጠረ ግቦችን በተቆጠረ ጊዜ ቢፈፅም አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ ይችላል። ባለፈው መጣጥፌ በተራዘመ ጊዜ ሊፈፅማቸው የሚችሉትን አላማዎች ጠቆም አድርጌ ነበር። ለዛሬው በመቶ ቀናት ሊፈፅማቸው ይገባል ያልኳቸውን የአደረጃጀትና የፓለቲካ ግቦች ጠቁሜያለሁ። እነዚህ አራት ግቦችና በስራቸው ያሉ የተቆጠሩ ተግባራት ከአረጃጀት፣ በመንግስትና በፓርቲ መካከል መኖር ስለሚገባው ግንኙነት፣ ስልጣንን እና ሌብነትን እንዲሁም የዲሞክራሲ እሴቶችን ለመገንባት የተዘረዘሩ ናቸው። ግቦቹና ዝርዝር ተግባራቱ ያለቀላቸው ሳይሆኑ ለውይይት መነሻ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው።
***

##ግብ አንድ:-

በሕገ መንግስቱ መሰረት በኢትዬጲያ ህዝብ አመኔታ እና ተቀባይነት የላቸውን በመለየት የሚኒስትሮች ምክር ቤትና ሌሎች ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ማዋቀር።
*

#የግብ አንድ ተግባር አንድ:-

ሕገ መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት አባላት እና ከምክር ቤት አባላት ውጪ ሚኒስትሮችን በመመልመል በፓርላማው ያፀድቃል በሚለው መሰረት እጩዎችን ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መመልመል።
*

#የግብ አንድ ተግባር ሁለት፣

ከተመለመሉት ውስጥ በብቃታቸው፣ በስነምግባራቸውና ተቀባይነታቸው የላቁትን ለሽግግር ጊዜው በሚኒስትርነት መመደብ። በዚህ መሰረት የሚከተሉት ግለሰቦች ለሽግግር ጊዜው ለእጩነት ቢቀርቡ በምክረ ሃሳብ የቀረቡ ናቸው፣

° ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት: አቶ ደመቀ መኮንን
° ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት: ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
° ኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር: አቶ ስዩም ተሾመ
° ፍትሕ ሚኒስትር: አቶ ተማም አባቡልጋ
° ደህንነት ሚኒስትር: አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
° ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር: አቶ ንጉሱ ጥላሁን
°የአገር ደህንነት ሚኒስትር: አቶ አንዷለም አራጌ
° ገቢዎች ሚኒስትር: – አቶ አስራት አብርሃም
° አርብቶ አደር ሚኒስትር: ዶክተር አብርሃ ተከስተ
° መገናኛ ሚኒስትር: አቶ የሺዋስ አሰፋ
° መከላከያ ሚኒስትር : አቶ በቀለ ገርባ
° ትምህርት ሚኒስትር:- አቶ ሬድዋን ሁሴን
° አሳ ሐብት ሚኒስትር: ወ/ት ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር
° የጡረታ ሚኒስትር: አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ( አባይ ነብሶ)
° ቱሪዝም ሚኒስትር:- ዶክተር አዲሳለም ባሌማ
° የኢንቨስትመንት ሚኒስትር:- አቶ ግርማ ሰይፉ
° ወጣቶች ሚኒስትር: – አብርሃ ደስታ
° ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር: – አርቲስት አስቴር በዳኔ
° ኤታማዦር ሹም: – ጄነራል ተፈራ ማሞ
° ፌዴራል ፓሊስ ሹም:- ኮረኔል ደመቀ ዘውዴ
° ሴቶችና ህፃናት ሚኒስትር:- ወይዘሮ የትነበርሽ
° የጽህፈት ቤቱ ሚኒስትር:- አቶ ደግፌ ቡላ
° የንግድ ሚኒስትር:- ተስፋዬ በጅጋ
° የግብርና ሚኒስትር: – አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ
*

#ግብ አንድ ተግባር ሁለት፣

የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ኮርፓሬሽን፣ ባለስልጣናት እና ተቋማት ስራ አስኪያጅ፣ ዋና ስራ አስፈፃሚና ዴሬክተሮች ሹመት የየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባላት ካልሆኑ ኢትዬጲያውያን ውስጥ ብቃት ያላቸውን መሾም። መመዘኛዎቹ በሚዲያ ተቋማት በግልፅ እንዲነገሩ ማድረግ። ሂደቱን ሕዝቡ በቀጥታ በሚከታተለው መልኩ እና ተወዳዳሪዎች ተቋማቱን እንዴት እንደሚመሩ እና የት ማድረስ እንደሚፈልጉ በሚገልፁበት ሁኔታ እንዲፈፀም ማድረግ። በውጭ የሚኖሩ ከፍተኛ ሙያተኛ የሆኑ ኢትዬጲያውያን እና ትውልደ ኢትዬጲያውያን የውድድሩ አካል እንዲሆኑ ማድረግ።

ከእነዚህ የስልጣን ቦታዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ይሆናሉ፣

• የብሔራዊ ባንክ ገዥ
• የልማት ባንክና ንግድ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ
• የኢትዬጲያ መድን ድርጅት
• የኢትዬጲያ አየር መንገድ
• የኢትዬጲያ ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን
• የመንግስት ሆቴሎች
• የኢትዬጲያ ቴሌቪዥን እና ሬዲዬ
• የመንገዶች ባለስልጣን
• ምርት ገበያ ( ECX)
• ዋና ኦዲተር ጄኔራል
• ሁሉም የአምባሳደርነት ቦታዎች
• አደጋና ዝግጁነት ዴሬክተር ( አመዝኮ)

*
#የግብ አንድ ተግባር ሶስት:-
በመንግስት በጀት የሚተዳደሩ አላስፈላጊ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች፣ ባለስልጣናት ፣ ተቋማት እና የሐላፊነት ቦታዎችን ማፍረስ። ከእነዚህ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣
• ፌዴራል ጉዳዬች ሚኒስትር
• የመንግስት ዋና ተጠሪ ፅህፈት ቤት
• የብሮድካስት ባለስልጣን
• የኢትዬጲያ ዜና አገልግሎት እና ፕሬስ ድርጅት
• የእምባ ጠባቂ ኮሚሽን
• የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
• ምርጫ ቦርድ
• የብረታ ብረት ኮርፓሬሽን ( ሜቴክ)
• ብሔራዊ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ(ኢንሳ)
• የፓሊሲ ምርምር፣ ጥናትና አማካሪ ቢሮ

*
#የግብ አንድ ተግባር አራት፣

ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቋሚነት የሚያሟክሩ በኢትዬጲያ ሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው ከ25 እስከ 30 የሚጠጉ ምስጉን የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና አገራችንን በአለም ደረጃ ያስተዋወቁ አባላት የያዘ “ አማካሪ ምክር ቤት” ማቋቋም።
• አማካሪ ምክርቤቱ በሁለት ሳምንት አንዴ ( ቅዳሜ ከሰአት) ለግማሽ ቀን የሚሰበሰብ ይሆናል።
• አማካሪ ምክር ቤቱ ዋነኛው ተልእኮ የሽግግር ሂደቱን ለማፋጠን ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል። የፓለቲካ ፓርቲዎችን ድርድር በይፋና በሚስጥር ያደርጋል። ፓርቲዎቹ የሚያቀርቡትን የሽግግር ሰነድ እየመረመረ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል። የዲሞክራሲ ተቋማት ተአማኒነት ባለው መልኩ የሚዋቀሩበትን ሐሳቦች በማመንጨት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል።

• የአማካሪ ምክር ቤት አባላት የገዥው ፓርቲ አባላትም ሆነ ደጋፊዎች መሆን የለባቸውም።

• ለአማካሪ ምክር ቤት አባልነት ለመነሻ እንዲሆን አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፋ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ክቡር ገና፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ ገብረየስ ቤኛ፣ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፣ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፣ አቶ አርአያ ገ/ እግዚአብሔር፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶክተር ያዕቆብ ሐይለማርያም፣ ዶክተር በፍቃዱ ደግፌ፣ አርቲስት አሊ ቢራ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፣አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ፣ አትሌት ሐይሌ ገብረስላሴ፣ አቶ አስገደ ገ/ ስላሴ፣ አቶ ገብሩ ገብረማሪያም፣ አቶ ቆስጠንጢኖስ በርሄ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የመሳሰሉት አባል የሚሆኑበት ይሆናል።
*

#የግብ አንድ ተግባር አምስት፣

የቀድሞ የሕውሓት/ ኢህአዴግ ባለስልጣናትን በሶስት ዙር በጡረታ ማሰናበት። ከጡረታ በኃላ በየትኛውም የሚዲያ ተቋም ፣ብሔራዊና ድርጅታዊ በአላት፣ ስብሰባዎች፣ ምርቃቶች እንዳይገኙ ማድረግ። አቶ ተፈራ ዋልዋ ልምዱን እንዲያካፍላቸው መድረክ ማዘጋጀት። በመጀመሪያው ዙር የሚሰናበቱት አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ በረኸት ስምኦን፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ አባይ ፀሀዬ፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ ዶክተር ካሱ ኢላላ ፣ ኩማ ደመቅሳ ፣ አዲሱ ለገሰ፣ ሳሞራ የኑስ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ አለማየሁ ተገኑ ይሆናሉ።
***

#ግብ ሁለት፣
የመንግስት እና ፓርቲ ስራ እንዲለያዩ ማድረግ። ፓርቲ መንግስትን ተክቶ አመራር አይሰጥም። መንግስት በቀጥታ በፓርቲው እየተመራ አመራር አይቀበልም።
*

#የግብ ሁለት ተግባር አንድ፣

የመንግስት አካላት የሚከተሉትን አጠቃላይ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ፓሊሲዎች የሚቀየሱት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ብቻ ይሆናል።
*

#የግብ ሁለት ተግባር ሁለት፣

በሕዝብ ምርጫ ከሚደራጁ ምክር ቤቶችና ካቢኔዎች ( እስከ ቀበሌ) ውጭ የሚሞሉ የመንግስት ሐላፊነት ቦታዎች የየትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ ኢትዬጲያውያን እንዲያዝ ማድረግ።
*

#የግብ ሁለት ተግባር ሶስት፣

በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችም ሆነ በቀጣይ የሚቀጠሩ ሰራተኞች የትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ማድረግ። በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ እየሰሩ አስቀድሞ አባል የሆኑ ሲቪል ሰርቫንቶች ለነበሩበት ፓርቲ በይፋ መልቀቂያ እንዲያስገቡ ማድረግ። የፓርቲ መልቀቂያ ለማስገባት ፍቃደኛ ያልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች በፍቃደኝነት ስራቸውን እንዲለቁ ማድረግ።
*

#የግብ ሁለት ተግባር አራት፣

በመንግስት የስራ ሰአት፣ በመንግስት ፅህፈት ቤት ውስጥ የየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት የፓለቲካ ስራ( ማደራጀት፣ መሰብሰብ፣ ካድሬ መመልመል) እንዳይካሄድ ማድረግ። የመንግስት ንብረት ለመንግስት ስራ ብቻ ማዋል። ይሄን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ሰራተኛ ከስራ እንዲሰናበት እና የትኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት በድጋሚ እንዳይቀጠር ማድረግ።

*
#የግብ ሁለት ተግባር አምስት፣

በዩንቨርስቲዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲ በይፋም ሆነ በግልፅ የድርጅት ስራ ( ምልመላ፣ ማደራጀት፣ ስብሰባ፣ መሰረታዊ ድርጅት) የመሳሰሉትን እንዳይሰራ ማድረግ። የትምህርት ተቋማቱ አመራሮች ምደባ የፓለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆንን እንደ ቅድመ ሁኔታ በመውሰድ መመዘኛው ብቃት እና ብቃት ብቻ እንዲሆን ማድረግ። በየትኛውም ደረጃ ያሉ መምህራት እንደ ሲቪል ሰርቪስ ሰራተኝነታቸው ከየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባል አይሆኑም። ህሊናቸው ካልፈቀደ በፍቃደኝነት ስራቸውን እንዲለቁ ይደረጋል።
***

# ግብ ሶስት፣
ስልጣን የሐብት ምንጭ የማይሆንበት ሁኔታ መፍጠር።
*

#የግብ ሶስት ተግባር አንድ፣

ሚኒስትሮች፣ ምክትል ሚኒስትሮች፣ ዋናና ምክትል ስራ አስፈፃሚዎች፣ ስራ አስኪያጆች፣ ዴሬክተሮች፣ መምሪያ ሐላፊዎች፣አምባሳዳሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ከኮረኔል እስከ ጄኔራል ባለ ማእረግ የጦር አዛዦች ንብረታቸውን በመመዝገብ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ። የወር የገቢና ወጪ መጠናቸውን፣ የልጆች ትምህርት ቤት ወጪ ወዘተ በምዝገባው እንዲካተት ማድረግ። ለምዝገባ ፍቃደኛ የሆኑትን እና ለመደበቅ ጥረት የሚያደርጉትን ለሕዝብ በማጋለጥ ለህግ ማቅረብ። በአርአያነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የካቢኔው አባላት በአንድ ወር ውስጥ ንብረታቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ማድረግ።
*

#የግብ ሶስት ተግባር ሁለት፣

በግብ ሶስት ተግባር ሁለት የተገለጡት ባለስልጣናት ከአንድ በላይ የቦርድ አመራርም ሆነ የቦርድ አባል እንዳይሆኑ ማድረግ። በቦርድ የሚተዳደሩ ተቋማት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ከተፎካካሪ ፓርቲ፣ አንድ ከባለስልጣንም ሆነ ከሲቪል ሰራተኛ ውጭ ማድረግ። በቦርድ ውስጥ የማገልገል ስራ በፍላጐትና ያለምንም ክፍያ እንዲሆን ማድረግ።
*

#የግብ ሶስት ተግባር ሶስት፣

በግብ ሶስት ተግባር ሁለት የተጠቀሱት ባለስልጣናት የቅርብ ዘመዶች ባለቤት የሆኑበት ቢዝነስ ከባለስልጣኑ ስራ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኝ ከሆነ ባለስልጣኑ ሐላፊነቱን በፍቃደኝነት እንዲለቅ አሊያም ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ እንዲያገለግል ማድረግ። በተጨማሪም ባለስልጣናቱ ከመንግስት ተቋማት ውጪ ባሉ ድርጅቶች የቦርድ አባልነትም ሆነ የአማካሪነት ስራ መስራት አይችሉም።
*

#የግብ ሶስት ተግባር አራት፣

የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚያስተዳድሩት ንብረትም ሆነ ቢዝነስ እንደማይኖራቸው በሕጉ የተገለፀውም ተፈፃሚ ማድረግ። በዚህ ሕግ መሰረት የኤፈርት፣ የትልማ፣ ረስት፣ ጥረት፣ ዲንሾ፣ ወንዶ ንብረቶች ለግል ባለሀብት እንዲሸጡ ማድረግ። ከሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለአንደኛ ፣ሁለተኛና ዩንቨርስቲዎች ማከፋፈል።
*

#የግብ ሶስት ተግባር አምስት፣

የግሉ ዘርፍ በነፃ ገበያው መርህ እየተመራ በኢኮኖሚው ላይ የበላይነቱን እንዲያረጋግጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር። በመንግስት የተያዙ ተቋማት በነፃ ገበያ ህግጋት መሰረት በሂደት ወደ ግል የሚዞሩበት ጥናቶችን ሰርቶ ማጠናቀቅ።
***

#ግብ አራት፣
በኢትዬጲያ ህዝብ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ባህልና እሴቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ።
*

#የግብ አራት ተግባር አንድ፣

የፀረ ሽብርተኝነት ፣ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የፕሬስ ህጉን በገለልተኛ ወገን እንዲጠና ማድረግ። የሚኒስትሮች ምክርቤት እና የአማካሪ ምክር ቤት አባላት በጋራ በመሆን በገለልተኝነት አጥንተው የሚያመጡ ሙያተኞችን በስምምነት እንዲመድቡ ማድረግ። ጥናቱ ተጠናቆ እስኪመጣ ድረስ አዋጆቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ እንዲታገዱ ማድረግ። በህውሓት ፓርላማ “ ሽብርተኛ!” ተብለው የተፈረጁ አገራዊ ድርጅቶች በአስቸኳይ እንዲሰረዙ ማድረግ።
*

#የግብ አራት ተግባር ሁለት፣

በሕግ መልኩ በፓርላማ ሊወጣ የተዘጋጀውን “ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሕግ” ሙሉ ለሙሉ ሂደቱ እንዲቋረጥ ማድረግ። እንደዚህ አይነት ከፀረ ሽብርተኝነት የባሰ ጨቋኝ ህግ እንዲወጣ በመታሰቡ ለወጣው የሕዝብ ገንዘብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠይቀው እንደማይደገም ቃል መግባት።
*

#የግብ አራት ተግባር ሶስት፣

ሬዲዬ ፋና፣ ዋልታ፣ ENN ፣ ድምፀ ወያኔ የመሳሰሉ የፓርቲ ሚዲያዎችን ማገድ። በግልፅ ጨረታ ወደ ግል ይዞታ የሚዞሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት። ሂደቱ በሚኒስትሮች ምክርቤትና በአማካሪ ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ እየቀረበ አበረታች ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ።
*

#የግብ አራት ተግባር ሶስት፣

የሽግግር ሰነድ ካዘጋጁ ተፎካካሪ የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ሚኒስትሮች ምክር ቤትና አማካሪ ምክር ቤቱ ይፋዊ ውይይቱን መጀመር። ውስጣዊ ድርድሮቹ ካለቁ በኃላ ለህዝብ ይፋ በሆነ መንገድ ውይይቱን መጀመር።
—–//—-

አቶ ለማ መገርሳም በፈገግታ ተሞልተው ይህንኑ ሲሉት ነበር። …….”በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ሰላማዊ የሰልጣን ሽግግር” (መሳይ መኮንን)

ሰሞኑን አንድ አባባል ጎላ ብሎ እየተሰማ ነው። በአገዛዙ ሚዲያዎች በሚቀርቡ እንግዶች፡ በጋዜጠኞቹም እየተደጋገመ ይጠራል። ከውጭ ወደ ሀገር ቤት በሚተላለፉ ሚዲያዎች ላይ በተለያዩ እንግዶች እየተነሳ ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም በመጀመሪያው ቀን አፋቸውን ሞልተው”ለአፍሪካ ተምሳሌት” ሲሉት ሰማሁ። የህወሀት መሪዎች በቤተመንግስት በተደረገ የእራት ግብዣ ላይ በሰልፍ ሆነው ”የመጀመሪያው” እያሉ ሲጠሩት ሰምቼ በሀፍረት ጥፍሬ ውስጥ መደበቅ ነበር የቀረኝ። አቶ ለማ መገርሳም በፈገግታ ተሞልተው ይህንኑ ሲሉት ነበር። …….”በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ሰላማዊ የሰልጣን ሽግግር” 🤔😋

የህወሀት ሚዲያዎች ዘንግተውት ነው እንጂ በ1985 አቶ መለስ ዜናዊ ዋናውን የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ዙፋን ሲቆናጠጡ: ትልቁ ስልጣን እንግዳ መቀበልና መሸኘት የሆነውን የፕሬዝዳንትነቱን ወንበር ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ያስረከቡ ጊዜ ”በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር” እያሉ ሲያደነቁሩን ነበር። አሁንም ”የመጀመሪያው……” እያሉ ነው። ደጋግመው ሲጠሩት የእውነት አስመሰሉት። ወግ መቼም አይቀርም። በሌለ ነገር መጃጃል:: አጉል መንጠራራት:: ሲሉ ሰምታ ዶሮ ምን ሆነች ነው የተባለው?

የሆነው በአጭሩ እንዲህ ነው። እንደ ህወሀት ሁለት መጥፎ ምርጫዎች ቀረቡለት። በአጭር ጊዜ ጠራርጎ የሚያጠፋውን የህዝብ ማዕበል መጠበቅ ወይስ ለዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መስጠት። ሁለቱም ለህወሀት መጥፎ ምርጫዎች ነበሩ። ከበጣም መጥፎ፡ የተሻለ መጥፎን ይመርጥ ዘንድ ግድ ሆነበት።

የዶ/ር አብይን ጠቅላይ ሚኒስትርነት መቀበል የተሻለ መጥፎ ምርጫ ነበር። ቢያንስ ትንፋሽ ይሰጣል። ያኛው ማዕበሉ ግን አስፈሪ ነው። ጊዜ አይሰጥም:: ምንም ሳያስቀር ጠራርጎ ያጠፋል። ለህውሀት የዶ/ር አብይ መምጣትም ቢሆን ጊዜያዊ እፎይታን እንጂ ዘላቂ መረጋጋትን አያመጣለትም። ህወሀት አከርካሪው ተሰብሯል። እያቃሰተ ትንሽ ጊዜ ይቆይ እንደሁ እንጂ ዕድሜም የለውም። ቢያንስ ግን የተሻለ መጥፎ በመምረጥ ለጊዜው ከአስፈሪው ማዕበል ተርፏል።

እናም ምን ለማለት ነው?! ሽግሽግ እንጂ ሽግግር የለም!!!😋😋

የዶክተር አብይ አህመድ ሲመተ ንግግርና የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ፍላጎት

የዶክተር አብይ አህመድ ሲመተ ንግግርና የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ፍላጎት

ከአርበኞች ግንቦት 7 (ልዩ ርዕስ አንቀጽ)

ዶክተር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ሲቀበሉ ያደረጉትን ንግግር አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በአንክሮ አዳምጧል፤ አጢኗል።

ከህወሓት/ኢህአዴግ ድርጅታዊ ባህል ውጭ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአገራችን ኢትዮጵያን ዝናና ክብር ከፍ የሚያደርጉ፤ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ፤ ፍቅርና ስምምነትን የሚሰብኩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። “ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ እድልኦ ለመላው ዜጎች ይደረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ፤ ይደክማሉ” በማለት ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ መስማት የናፈቀውን አባባል ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ንግግር ባለተሰማበት ፓርላማ ውስጥ ተናግረዋል።
“አባቶቻችን በመተማ፣ በማይጨውና በካራ ማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆይዋት አገር አለችን። እኛ እድለኞች ነን። ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንን እናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ህዝብ ነን“ ሲሉ የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ አኩሪ ታሪክ አስታውሰዋል። በአገራችን ውስጥ ያለውን በጎ የማኅበረሰብ ትስስር ምሳሌዎችን በማንሳት አወድሰዋል። ”ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!” በማለትም በህወሓት አገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያዊያን የተራቡትን የእኩልነት ዜግነት መብት ሊከበር የሚችል መሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል። ከዚህም በላይ የሀሳብ ልዪነቶች መኖር ለቁልፍ ችግሮቻችን የተሻሉ የመትፍሄ ሀሳቦች መገኘት መሠረት ሊሆኑ እንደሚችሉ በመግለጽ “በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ።ስንደመር እንጠነክራለን” የሚል አዎንታዊ ኃይለ ላት ተናግረዋል። ዲሞክራሲን በሚመለከትም “እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም !” ብለዋል።
እነዚህን ተስፋ ሰጪ ንግግሮች ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት መስማት አጅግ በጣም የሚያበረታታ ነዉ። ሆኖም እነዚህ ተስፋዎች በንግግር ብቻ የምንሰማቸዉ ሳይሆኑ በቶሎ በተግባርም መተርጎም አለባቸዉና በቅርቡ አብረን የምናያቸዉ ይሆናሉ።
ዶ/ር አቢይ በፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸው ለተቀጠፉ ወገኖቻችን የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልፀዋል፤ ይቅርታም ጠይቀዋል። ለወደፊቱም ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንዳይፈፀም ስለእርቅ ተናግረዋል፤ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እንደሚደረግ፤ በአጠቃላይ በህገመንግሥቱ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ መብቶች ሁሉ መከበር እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ባለፈዉ የካቲት ወር አጋማሽ የታወጀዉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የዜጎችን መሠረታዊ መብትና ነጻነት የሚቀማና በተወሰነ መልኩ ህገ መንግስቱንም የሚያግድ ነዉ፥ ስለዚህ ጠ/ሚኒስትር አቢይ “ህገ መንግስታችንን በአግባቡ መተግበር” አለብን ብለዋልና አርበኞች ግንቦት ሰባት አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የዜጎች መሰረታዊ መብትና ነጻነት እንዲከበር ለማድረግ የሚያስችሏቸዉን ዕርምጃዎች በአጭር ግዜ ዉስጥ ይወስዳሉ ብሎ ተስፋ ያደርጋል።
“ዲሞክራሲ ያለነጻነት አይታሰብም። ነጻነት ከመንግስት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንዱ ሰው የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ” በማለት ዶክተር አቢይ አህመድ የገለጹት ሰፊ ተቀባይነት ያለው ጽንሰ ሀሳብ እንዴት ተግባራዊ ሊደረግ እንደታሰበ አርበኞች ግንቦት 7 ማወቅ ይሻል። ዲሞክራሲ ያለነፃነት የማይታሰብ መሆኑ የአርበኞች ግንቦት 7 እምነትም ነው፤ የሚታገለውም ይህ እምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ነው። እነዚህን ነጻነቶች ሲረግጥ የኖረው አገዛዝ እና የፓለቲካ ድርጅት ነጻነትን በማስከበር ሂደት ውስጥ ምን ዓይነት አስተዎጽኦ ሊያደርግ እንዳቀደ እና ለዚህ ስላደረገው ድርጅታዊ ዝግጅትም በቂ መረጃ ሊኖረው ይሻል።
ዶ/ር አቢይ አህመድ “ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን” ያሉት በምን መንገድና በማን ለመፈጸም እንዳሰቡ በሚወስዷቸው ተከታታይ እርምጃዎች ማየት እንሻለን።
በሰላም፣ ማኅበራዊ መግባባትና ፍትህ ረገድ የተናገሯቸው ቁምነገሮች ኢትዮጵያዊያን መስማት የሚልጓቸው ነገሮች ናቸው። በአጠቃላይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያን ችግሮች በጥሩ ሁኔት ዘርዝረዋል። በቀጣይ ንግግሮችና በተለይም በተግባር በሚሰሩ ስራዎች የእነዚህ ችግሮች መፍትሄና በአጠቃላይ አገራችን በሳቸዉ አመራር የምትሄድበትን አቅጣጫ ያሳያሉ ብለን እንጠብቃለን።
አርበኞች ግንቦት ግንቦት 7 ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምላሽ ይሻል
1. ለመሆኑ ዶ/ር አቢይ አህመድ እያሰቡት ያለው ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ ነው ወይስ ጊዜዓዊ ማስታገሻዎችን ነው?
2. የዶ/ር አቢይ ለውጥ የመጨረሻ ግብ ምንድነው? የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ማድረግ ወይስ ኢህአዴግን ከቀውስ ማዳን?
3. በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የህወሓት/ኢህአዴግ ሚና ምንድነው? የችግሮቹ ፈጣሪ የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ እንደምን የመፍትሄ አካል መሆን ይቻለዋል?
4. በለውጡ ሂደት ውስጥ ከህወሓት/ ኢህአደግ ውጭ ያሉት አካላት ሚና ምንድነው? በለውጡ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ያላቸው መተማመኛስ ምንድነው?
5. የኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጡ ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው እንዴት ነው?
በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት የለውጡ ግብ መሆን ያለበት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ የተከበረበት ሀገር እንዲኖረው ማስቻል፤ ማለትም የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ማድረግ መሆን ይኖርበታል። አርበኞች ግንቦት 7 ወደዚህ ግብ የሚወስዱን ጥረቶች ሁሉ ይደግፋል።
የዶ/ር አቢይና ባልደረቦቻቸው ጥረት የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ከሆነ አርበኞች ግንቦት 7 አጋራቸው ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ፍትህ ማስፈን የአርበኞች ግንቦት 7 ግብ ነው። ወደዚህ ግብ የሚያቀርቡ ጥረቶች ሁሉ የአርበኞች ግንቦት 7 ትግል አካላት ናቸው። ይሁን እንጂ ከፍላጎቶች ባለፈ ተጨባጭ የተግባር ጥረቶችን ማየት ይሻል።
በዚህም መሠረት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኔያቸውን እንዳቋቋሙ
1. ኢትዮጵያ ዉስጥ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መብቶችና ነጻነቶች በሙሉ መከበራቸዉንና ባጠቃላይ ህገ መንግስቱ መከበሩን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ ይህ ደግሞ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለበትና ሀገሪቱን በሙስና የተጨማለቁት ወታደራዊ መሪዎችና የደህንነት አካላት ሙሉ ለሙሉ በሚቆጣጠሩት ሀገር የሚሆን አይደለምና የመጀመሪያ ስራቸው የሚሆነው ይህንን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት ነው። የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ሲባል ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ያጠቃልላልና ጓዳችን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ሊለቀቁ ይገባል፤ ለወደፊቱ ሰዎች በአመለካከቸው ምክንያት እንደማይታሰሩና ስቃይ እንደማይደርስባቸው ተቃማዊ ዋስትና ሊሰጥ ይገባል፣ ይህ እርምጃ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በንግግራቸው የተናገሩትን በተግባር ለማዋል ያላቸውን ቁርጠኝነትና እንዲሁም ሕዝባዊ ትግልም ወደ ለውጥን ተግባራዊ ወደማድረግ አቅምም ለመቀየር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያጠቃልላል።
2. ከህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነን ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር መመራት በሚኖርባቸው መንገዶች ላይ በህጋዊ መንገድም ሆነ ከአገዛዙ ህጎች ውጭ እየተንቀሳቀሱ ካሉ የፓለቲካና የሲቪል ማኅበራት ጋር መምከር መጀመር ይኖርባቸዋል፣
3. አርበኞች ግንቦት 7፣ የዶ/ር አብይ የመጀመሪያ ንግግር የተለያዩ ጥቅምና ፍላጎት ያላቸውን ኃይሎች (ለውጥ ፈላጊውን ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጥሩና ቢያንስ ሀገሪቱን ለማተራመስ ጊዜያዊም ቢሆን አቅም ያላቸውን በድርጅታቸው በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ኃይሎችና ከነኝህ ጋር በመተባበር ሀገሪቱን ሲግጡ የቆዩ ዘራፊዎች) ለማማለል ተብሎ የቀረበ ጥቅል አቅጣጫ አመላካች ንግግር መሆኑን ይገነዘባል። ስለዚህም በዚህ አይነት ንግግር ሁሉንም ያገሪቱን ችግርና ይህንን የሚቀርፉበትን ተጨባጭ የፖሊሲ እርምጃዎች ይዘረዝራሉ ብለን አልጠበቅንም። ዶ/ር አቢይ በንግግራቸዉ ላይ ብዙ ነገሮችን አሳይተዉናል፥ ሆኖም አንድን ሀሳብ በንግግር ማቅረብና በተግባር መተርጎም አንዳንዴ በተለይም በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ሊሆን ይችላልና አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የተናገሯቸዉን ንግግሮችና ያቀረቧቸዉን ሀሳቦች በተግባር ለመተርጎም ያላቸዉ ቁርጠኝነት የወደፊቱን አቅጣጫ ያሳያል የሚል እምነት አለን። ዶ/ር አብይ የለውጡን ኃይል ይዘው ለመራመድ ከፈለጉ ያላቸውን አጭር ግዜ ከአሁኑ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህንን ካላደረጉ ወይም ግዜ በወሰዱ ቁጥር ለውጡን ለመጎተትና ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎችን ጉልበት ነው የሚያጠናክሩት። ከዚህ በተጨማሪ ተግባር በዘገየ ቁጥር የለውጥ ፈላጊውን ኃይል ትዕግስት ተሟጥጦ ያልቅና ለዚህ ያደረሳቸውንና በእርግጥም ለሚወስዱት የለውጥ እርምጃ ጉልበት ሊሆናቸው የሚችለውን ኃይል ያጣሉ። ይህ ደግሞ ለሳቸውም፤ ለሀገሪቱም አይበጅም።

አንድነት ኃይል ነው!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!